የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 8/15 ገጽ 26-29
  • የምትከፍለውን ዋጋ አስልተኸዋልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የምትከፍለውን ዋጋ አስልተኸዋልን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተፈጥሮ ስሜት አይበቃም
  • ሚዛናዊ አመለካከት
  • እውነተኛ ጥበብ መከላከያ ነው
  • መንፈሳዊ ነገሮችን መከታተል የሚያስገኘው ጥቅም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • በአምላክ የምትተማመነው ምን ያህል ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ጥበብ የታከለበት ውሳኔ አድርግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • “ይሖዋ ጥበብን ይሰጣል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 8/15 ገጽ 26-29

የምትከፍለውን ዋጋ አስልተኸዋልን?

“ምን! ይህን ግሩም የዕድገት ዕድል አልቀበልም ነው የምትዪው?” ሱፐርቫይዘሯ የሰማችውን ማመን አቃታት። የበታች ሠራተኛዋ የሆነችና በጥሩ ችሎታዋና መልካም ጠባይዋ የተመሰገነች አንዲት ሴት በኩባንያው ወጪ ባሕር ማዶ ሄዳ ለሁለት ዓመት እንድትማር የቀረበላትን የትምህርት ዕድል ይኸውና አልቀበልም አለች። ግን ለምን እምቢ አለች?

ሴቲቱ ምክንያቱን ስታስረዳ ዕድገቱን መቀበል ማለት ከባሏና ከሁለት ልጆቿ ለሁለት ዓመት ተለይታ መቆየት ማለት እንደሆነ ተናገረች። በጣም ትናፍቃቸዋለች። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ የተሰጣትን የሚስትነትና የእናትነት ድርሻ ችላ ማለት ሊሆንባት ነው። ዕድገቱን መቀበል በስሜታዊና በመንፈሳዊ በጣም ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ሆነባት። በመሆኑም ኪሳራውን ከቆጠረች በኋላ የዕድገት ዕድሉን ላለመቀበል ወሰነች።

እናንተ በእርሷ ቦታ ብትሆኑ ኖሮ ምን ታደርጉ ነበር? ሁሉም ሰው ይህች ክርስቲያን ሴት ባደረገችው ውሳኔ እንደማይስማማ ግልጽ ነው። የሥራ ባልደረቦቿን የመሳሰሉ አንዳንዶች ሙያዋን ለማሻሻል የቀረበላትን ወርቅ የሆነ አጋጣሚ እንዳባከነች ይሰማቸው ይሆናል። ሁለት ዓመት ቶሎ ስለሚያልፍ ለወደፊቱ የቤተሰቧ ሁኔታ አላሰበችም ብለው የሚወቅሷት ሌሎች ሰዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም ውሳኔዋ በችኮላ ወይም በግል ስሜት ገፋፊነት የተደረገ አልነበረም። በጥሩ ማመዛዘንና የአርቆ አስተዋይነት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ነበር። እነዚህ መመሪያዎች ምንድን ናቸው?

የተፈጥሮ ስሜት አይበቃም

በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ጥበበኛ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ከምሳሌዎቹ በአንዱ ላይ ይህን መመሪያ ሰጥቷል፦ “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቆጥር ማን ነው?” በማለት ኢየሱስ ጠየቀ። “ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት ሊደመድመውም ቢያቅተው ያዩት ሁሉ ‘ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው’ ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።”​—ሉቃስ 14:28-30

ማንኛውንም ከፍተኛ ጉዳይ ለመሥራት ከመወሰን በፊት አስቀድሞ ኪሳራውን መቁጠር አስፈላጊ መሆኑን ማንም ሰው ይስማማል። ለምሳሌ አንድ ሰው ቤት ሊገዛ ቢፈልግ ዋጋውን ጠይቆ ሳያረጋግጥና የሚጠየቀውን ገንዘብ ከፍሎ ለመጨረስ የሚያስችል የገንዘብ አቅም መኖር አለመኖሩን ሳያረጋግጥ ቸኩሎ ውሉን ይፈራረማልን? እንዲህ ካደረገ በእርግጥም ሞኝ ሰው መሆኑን ያሳያል። አዎን፣ አንድ ሰው አንድ ውጥን ከመጀመሩ በፊት ኪሳራውን መቁጠር ማንም በተፈጥሮ ወይም የሚሰማው ነገር ነው።

የሆነ ሆኖ ኢየሱስ በዚያ ምሳሌ ላይ ያስተላለፈው ፍሬ ነገር በእርግጥ ምንድን ነው? ምሳሌውን ከመናገሩ ቀደም ብሎ “ማንም መስቀሉን [የመከራ እንጨቱን አዓት] ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 14:27) ስለዚህ ኢየሱስ ለተራና ለዕለት ተዕለት ውጥኖቻችን የሚሠራ ማንም ሰው በተፈጥሮ የሚያውቀውን ምክር መስጠቱ እንዳልነበር ያመለክታል። ከዚህ ይልቅ የእርሱ ደቀ መዝሙር ከመሆን አኳያ ኪሳራን ስለመቁጠር እየተናገረ ነበር።

ኢየሱስ በምሳሌው አማካኝነት የእርሱ ደቀ መዝሙር መሆን ለውጦችንና መስዋዕቶችንም እንደሚጠይቅ አመልክቷል። ለምን? ምክንያቱም የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት የሚያዘነብለው ወደ ሥጋዊ ነገሮች ብቻ ስለሆነና በራስ ወዳድነት ፍላጎት የሚነዳ ስለሆነ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ወይም ከአምላክ ጋር ላላቸው ዝምድና ምንም ትኩረት ባለመስጠት የሚያሳስባቸው ዋና ነገር ሥጋዊ ምኞቶቻቸውን ማርካት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) ይሁን እንጂ ይህ ዝንባሌ ወይም መንፈስ በኢየሱስ ክርስቶስ ከታየው ዝንባሌ ወይም መንፈስ ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው። ኢየሱስ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ብሏል። “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም” ባለ ጊዜ ከሥጋዊ ነገሮች ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ግምት ሰጥቷል።​—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 6:63

በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለመሆን ለሚፈልጉ ሰዎች የሚከፍሉት ዋጋ እንዲያስቡት ሲመክራቸው በመሠረቱ የተናገረው ስለ ሥጋዊ ነገር ሳይሆን ስለ መንፈሳዊ ነበር። ለእነርሱ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር የትኛው ነው? ዓለም የሚሰጠው ሥጋዊ ጥቅም ነው ወይስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚሰጠው ጥቅም? ኢየሱስ ምሳሌውንና ከዚያ ጋር የሚዛመደውን ነገር ከተናገረ በኋላ “እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” ያለው ለዚህ ነበር። (ሉቃስ 14:33) የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን የሚያስበው ሰው እንዲህ ዓይነቱን መስዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛና ዝግጁ ነውን ወይስ ይህን ማድረግ ሊከፍለው የማይችል ከአቅም በላይ የሆነ ዋጋ ነው?

ሚዛናዊ አመለካከት

ሥጋዊ ነገሮች ይበልጥ ጉልህና የሚታዩ ጥቅሞችን ወዲያው የሚያመጡ ቢሆኑም እንኳን መንፈሳዊ ነገሮችን ከመከታተል የሚገኙ ጥቅሞች ይበልጡን ዘላቂና የሚያረኩ ናቸው። ኢየሱስ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ” በማለት በሚገባ አስረድቷል። (ማቴዎስ 6:19, 20) በዘመናችን የገንዘብ ዋጋ ማጣት፣ የገበያ ምንዛሪ ማሽቆልቆል፣ የባንክ ውድቀትና የመሳሰሉት ሁኔታዎች እምነታቸውን በሥጋዊ ሀብት ብቻ ላይ የጣሉ ብዙ ሰዎችን ውድቀት ላይ ጥለዋል። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ “የማይታየውን እንጂ የሚታየውን አንመልከት። የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው” በማለት አጥብቆ አሳስቦናል። (2 ቆሮንቶስ 4:18) ታዲያ ይህን አመለካከት ልንኮተኩት የምንችለው እንዴት ነው?

እንዲህ ልናደርግ የምንችለው አርአያችንና ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ አንዳንድ ጊዜ በሠርግ ድግስና በግብዣዎች ላይ መካፈሉ የሚገልጸው በጭራሽ ባሕታዊ ወይም መናኝ እንዳልነበረ ነው። ይሁን እንጂ በግልጽ እንደሚታየው ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ሰጥቷል። የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል ለሕይወት አስፈላጊ እንደሆኑ የሚቆጠሩትን መሠረታዊ ነገሮች እንኳን ለመተው ፈቃደኛ ነበር። አንድ ጊዜ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይ ወፎችም መሳፈሪያ አላቸው፣ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” ብሏል። (ሉቃስ 9:58) የአባቱን ፈቃድ መፈጸም በጣም አስፈላጊና የሚያስደስት ነገር እንደሆነ ከመረዳቱ የተነሳ ከልብ በመነጨ ቅንነት “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል።​—ዮሐንስ 4:34

ኢየሱስ የሰይጣንን መደለያዎች አልቀበልም ብሎ እምቢ በማለቱ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ አሳይቷል። ኢየሱስ ከአምላክ የተሰጠውን ኃይል ራሱን ለመጥቀም፣ የተፈጥሮ ፍላጎቶቹን ለማርካትና ዓለማዊ ዝናና ታዋቂነት ለማግኘት እንዲጠቀምበት ለማድረግ ዲያብሎስ ጥሯል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቶቹ ያልተያዙ ጥቅሞች ሊገኙ የሚችሉት በጣም ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎባቸው መሆኑን አሳምሮ አውቋል። ይህም ከፍተኛ ዋጋ የአምላክን ሞገስ ማጣት ሲሆን ኢየሱስ ሊከፍል የማይፈቅደው በጣም ከፍ ያለ ዋጋ ነበር፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የነበረውን ጥሩ ዝምድና ከምንም ነገር በላይ ያፈቅር ስለነበር ነው። ኢየሱስ ያለምንም ማወላወል ቁርጥ አድርጎ የሰይጣንን ስጦታ አልቀበልም ያለው ለዚህ ነበር።​—ማቴዎስ 4:1-10

እኛም የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጣቸው ነገሮች ከጌታችን ጋር አንድ ዓይነት መሆን አለባቸው። በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ጥሩ ጥቅም የሚያስገኙ የሚመስሉ ቢሆኑም እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሹ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ማኅበራዊ የዕድገት መሰላሎችን መውጣት፣ ደረጃን ለማሻሻል ተብሎ ከፍተኛ ትምህርትን መከታተል፣ የማያምኑ ሰዎችን ለጋብቻ አስቦ መቀራረብ፣ ወይም አጠያያቂ በሆኑ የንግድ ዕቅዶች መካፈል የመሳሰሉት ነገሮች በቀላሉ እምነትን ወደማጣትና የኋላ ኋላም ከይሖዋ ሞገስ ወደ መውጣት ሊያደርሱ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ ማባበያዎች ሲያጋጥሙን የምንከፍለውን ዋጋ በጥንቃቄ ማስላት አለብን።

እውነተኛ ጥበብ መከላከያ ነው

ከጥቂት ዓመታት በፊት በሩቅ ምሥራቅ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ ከተማ የሚኖር አንድ ወጣት ክርስቲያን ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ ባሕር ማዶ የመሄድ አጋጣሚ አገኘ። ምንም እንኳን ቀደም ሲልም ጥሩ ዓለማዊ ትምህርት የነበረው ቢሆንም ይህ በቂ እንዳይደለ ተሰማው። የኑሮ ደረጃውን ለማሻሻል ፈለገ። መሰል ክርስቲያኖች እስካሁን ከተመለከትናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ቁም ነገሮች ጋር የሚስማማ ምክንያት በማቅረብ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ጥረው ነበር፣ እርሱ ግን ፍንክች ሳላላለ በዕቅዱ ገፋበት። መጀመሪያ ላይ እምነቱን አጥብቆ ለመያዝ ቢጥርም ቀስ በቀስ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረውን አድናቆት አጣ። መጠራጠርም ጀመረ። በዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ብቻ እምነቱን ሙሉ በሙሉ አጣና ስለ አምላክ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ባይ ሆነ። እርግጥ ነው፣ ዓለማዊ ትምህርቱን በማሻሻል በኩል ከፍተኛ ዲግሪ ማግኘቱ መጠነኛ እርካታ አምጥቶለታል። ይሁን እንጂ ለጊዜያዊ ታላቅነት ብሎ ምንኛ ከባድ ዋጋ መክፈል አስፈለገው! ይህም ዋጋ እምነቱን ማጣትና የዘላለም ሕይወቱንም የማጣት አደጋ ነው።​—1 ጢሞቴዎስ 1:19

በሌላ በኩል ደግሞ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ምንም ነገር በአደጋ ላይ እንዲጥልባቸው የማይፈቅዱ ሰዎች ከይሖዋ ብዙ በረከቶችን አጭደዋል።

እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ከላይ በተጠቀሰው ከተማ የሚኖር የቤት ማስጌጥ ሥራ የነበረው አንድ ወጣት ሰው ነው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ የእደሳ ሥራ በ30,000 ዶላር እንዲሠራ የሚያጓጓ ሐሳብ ቀረበለት። ይሁን እንጂ እደሳው አንድ ሕገ ወጥ ቋሚ ለመትከል የሕንፃውን ልዩ ማስታወሻና ቁመናውን መቀያየር የሚጠይቅ ነበር። ክርስቲያኖች ሕግ አክባሪዎች መሆን እንዳለባቸው ስለተማረ ይህን ሥራ መቀበል ማለት የአምላክን ሞገስ ማጣት ማለት መሆኑን ተገነዘበ። (ሮሜ 13:1, 2) ጉዳዩን በጥንቃቄ ከመዘነው በኋላ ሥራውን አልቀበልም አለ። ውጤቱስ? ይህ የእምነት ተግባር ለሰውየው በመንፈሳዊ ዕድገቱ ትልቅ ለውጥ አመጣለት። በዚያው ዓመት ውስጥ ሕይወቱን ወደ መወሰንና ወደ መጠመቅ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ መሻሻል አደረገ። የሥራ ፈቃዱን ሸጠና መንፈሳዊ ነገሮችን ለመከታተል ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጠው ሌላ ሥራ አገኘ። አሁን ይሖዋን በደስታና በቅንዓት ያገለግላል።

ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ወጣት ሰዎች ኪሳራቸውን ቆጥረዋል። በምርጫቸው ላይ ልዩነት ያመጣው ምንድን ነው? አምላካዊ ጥበብ ነው! እንዴት? ጥበብ ማለት አብዛኛውን ጊዜ ዘላቂ ጥቅሞችን በሚያመጣ መንገድ እውቀትን በሥራ ላይ ማዋል ማለት ነው። አምላካዊ ጥበብ ደግሞ አምላክ ለእኛ ካለው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ዕውቀትን በሥራ ላይ ማዋል ማለት ነው። ሁለቱም ወጣት ሰዎች መጠነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የነበራቸው ሲሆን ዕውቀታቸውን በሥራ ላይ አዋዋላቸው የተለያዩ ውጤቶችን አምጥቷል። የምሳሌ መጽሐፍ “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ (አርቆ ማየት) ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን” ይላል።​—ምሳሌ 2:10-12

የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ማድረግ በሚኖርባችሁ በማንኛውም ጊዜ የምታማክሩት የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ ነው። በራሳችሁ አስተያየት ጠቢባን ከመሆን ይልቅ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን ምክር ተቀበሉ። (ምሳሌ 3:5, 6) በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በጣም የተስፋፋውን በራስ ፈቃድና ሐሳብ የመመራትን መንፈስ አስወግደን ለመማር እንድንችል ትሑቶችና ፈቃደኞች መሆን አለብን።

አዎን፣ የዘራነውን ከማጨድ ልናመልጥ አንችልም። የምናደርጋቸውን ውሳኔዎችና ምርጫዎች ውጤት መሸከም ያለብን መሆኑም አግባብ ያለውና ትክክለኛ ነገር ነው። (ገላትያ 6:7, 8) ስለዚህ ማንኛውንም ውጥን ከመጀመራችሁ በፊት የምትከፍሉትን ዋጋ አስሉ። ጠቃሚ የሚመስል ማንኛውም ነገር መንፈሳዊነታችሁን ወይም ከይሖዋ አምላክ ጋር ያላችሁን ዝምድና እንዲቀማችሁ አትፍቀዱ። አሁን የምታደርጉት ውሳኔ የዘላለማዊ ሕይወትና የዘላለማዊ ሞት ልዩነት የሚያመጣ ሊሆን ስለሚችል ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ ጥበብና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንድታገኙ ጸልዩ!​—ከዘዳግም 30:19, 20 ጋር አወዳድሩት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሕይወቱ ውስጥ ለመንፈሳዊ ሥራዎች ቅድሚያ ይሰጥ ይሆን ወይስ ዓለማዊ ሥራውን ያስቀድማል?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ