ፓፒያስ ጌታ ለተናገራቸው ነገሮች ትልቅ ግምት ሰጥቷል
“እውነት የሆነውን ነገር ከሚያስተምሩ እንጂ ብዙ ከሚያወሩ ጋር መሆን አያስደስተኝም።” ይህንን የጻፈው በ2ኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የኖረው ፓፒያስ የተባለ ክርስቲያን ነኝ ይል የነበረ ሰው ነው።
ፓፒያስ የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ከሞቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በነበሩት ዓመታት ነው። እንዲያውም ከሐዋርያው ዮሐንስ እንደተማረ ከሚነገርለት ከፓሊካርፕ ጋር ግንኙነት ነበረው። እነዚህ መረጃዎች ከፓፒያስ የእውቀት ማሰባሰቢያ ዘዴ ጋር ተጣምረው ጥሩ እውቀት የነበረው ሰው መሆኑን ያሳያሉ።
ጥንቃቄ የተሞላበት ዘዴ
ፓፒያስ ስለ ጌታ ንግግሮች በጻፋቸው አምስት መጻሕፍት ላይ ለእውነት ያለው ጥማት በግልጽ ታይቷል። ፓፒያስ ቀደም ባሉት የሕይወቱ ዘመናት የሰማቸውን ብዙ የእውነት ንግግሮች እንደሰበሰበ አያጠራጥርም። በኋላም ፓፒያስ በሚኖርበት በትንሿ እስያ በምትገኘው በሄሮፖሊስ ከተማ በፍርግያ የሚገኙትን አረጋውያን ከኢየሱስ ሐዋርያት መካከል አንዱን አይተው ወይም ሲናገር አዳምጠው እንደሆነ ለማረጋገጥ እየዞረ ጠይቋል። በጉጉት ይጠይቃቸውና የሚናገሩትንም ይመዘግብ ነበር።
ፓፒያስ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “የእነርሱን እውነተኝነት የሚያረጋግጥላችሁን በማንኛውም ጊዜ ከሽማግሌዎቹ በጥንቃቄ የተማርኩትንና በደንብ የማስታውሰውን ከማስፈር ወደኋላ አልልም። እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ሁሉ እኔም ብዙ ከሚያውሩ ጋር ሳይሆን እውነት የሆነውን ከሚያስተምሩ እንዲሁም የሌሎችን ትዕዛዝ ከሚጠቅሱ ጋር ሳይሆን ከጌታ ለሃይማኖታችን የተሰጡትንና ከእውነት የመነጩትን ትዕዛዛት ከሚዘግቡት ጋር መሆኑ ያስደስተኛል። የሽማግሌዎች ተከታይ የነበረ ሰው ካጋጠመኝ በሽማግሌዎቹ የተሰጠውን ትረካ እጠይቀዋለሁ፤ እንድርያስ ወይም ጴጥሮስ ምን እንዳለ፤ ወይም ፊሊጶስ ወይም ቶማስ ወይም ያዕቆብ ወይም ዮሐንስ ወይም ማቴዎስ ወይም ከጌታ ደቀ መዛሙርት አንዱ ምን እንዳለ እጠይቀዋለሁ።”
የጽሑፍ ሥራው
ፓፒያስ የመንፈሳዊ ዕውቀት ሀብት እንደቀረበለት አያጠራጥርም። የሐዋርያትን የግል ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹትን ዝርዝር ሁኔታዎች ለማወቅ እንዴት በተመስጦ ያዳምጥ እንደነበር ከመገመት በቀር ሌላ ምንም ማድረግ አንችልም። ፓፒያስ ሊያስተላልፈው የፈለገውን ነገር በ135 እዘአ አካባቢ የራሱን መጽሐፍ በመጻፍ አስፍሮታል። የሚጸጽተው ግን ይህ መጽሐፍ ጠፍቷል። በ2ኛው መቶ ዘመን የኖረውና ራሱን ክርስቲያን አድርጎ ይቆጥር የነበረው ኢራኒየስ፣ እንዲሁም የአራተኛው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ ዮሴቢዬስ ከዚህ መጽሐፍ በመጥቀስ ጽፈዋል። እንዲያውም እስከ 9ኛው መቶ ዘመን ድረስ ይነበብ ነበር። ምናልባትም እስከ 14ኛው መቶ ዘመን ድረስም ሳይቆይ አልቀረም።
ፓፒያስ በመጪው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ያምን ነበር። (ራእይ 20:2–7) እንደ ኢራኒየስ አባባል ፓፒያስ እንደሚከተለው በማለት ስለ እነዚያ ጊዜያት ጠቅሷል:- “ጌታ ስለ እነዚያ ጊዜያት እንዴት ያስተምር እንደነበር የጌታ ደቀ መዝሙር የሆነውን ዮሐንስን ያዩት ሽማግሌዎች ሰምተዋል። የሰሙትንም እንደተናገሩት ፍጥረት ሲታደስና ነፃ ሲወጣ ሁሉንም ዓይነት ምግብ ከሰማይ ጠልና ከምድር ልምላሜ በብዛት ያመርታሉ።” ከዚህም በተጨማሪ ፓፒያስ “እነዚህ ነገሮች እምነት በነበራቸው ዘንድ ሊታመኑ የሚችሉ ነበሩ። ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ በዚህ ለማመን እምቢ ብሎ ‘እንዲህ ያለው ነገር በጌታ ሊከናወን ይችላልን?’ ብሎ በጠየቀ ጊዜ ጌታ ‘በዚያን ጊዜ የሚኖሩ ያዩታል’ ሲል መለሰለት”።
ፓፒያስ ጽሑፉን የጻፈው ግኖስቲሲዝም [ነገር ሁሉ ክፉ ነው፤ ከዚህ መላቀቅ የሚቻለው በንቃተ ህሊና ነው] የሚል እምነት በተስፋፋበት ዘመን ነበር። የግኖስቲሲዝም አማኞች ፍልስፍናን፣ ግምታዊ አስተሳሰብንና ሊታመን የሚችል መሠረት የሌላቸውን አረመኔያዊ እምነቶችን ከክህደት ክርስትና ጋር አቀላቅለው ይይዙ ነበር። እንዲያውም ፓፒየስ የጌታን ንግግሮች ማጠናቀሩ የግኖስቲሲዝምን መስፋፋት ለመግታት የተደረገ ሙከራ ነበር። ከእርሱ በኋላም ኢራኒየስ የግኖስቲሲዝም ተከታዮችን የተጋነነ የሐሰት መንፈሳዊነት መቃወሙን ቀጥሎ ነበር። ፓፒያስ “ብዙ የሚያወሩ” ብሎ በምጸት እንዲናገር ያደረገው የግኖስቲሲዝም ጽሑፎች ብዙ የሚያወሩ ስለነበሩ መሆን አለበት። የእርሱ ዓላማ ግልጽ ነበር፤ ይኸውም ውሸትን በእውነት መዋጋት ነበር። — 1 ጢሞቴዎስ 6:4፤ ፊልጵስዩስ 4:5
ስለ ወንጌሎች የሰጣቸው አስተያየቶች
አሁንም በሚገኙት የፓፒያስ ጽሑፎች ቁርጥራጮች ላይ በማቴዎስና በማርቆስ ስለተጻፉት ትረካዎች ተጠቅሶ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል ፓፒያስ ስለ ማርቆስ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል:- “ማርቆስ የጴጥሮስ ተርጓሚ በመሆኑ ያስታወሰውን ነገር ሁሉ በትክክል አስፍሯል።” ከዚህም በተጨማሪ ስለዚህ ወንጌል ትክክለኛነት ሲያረጋግጥ ፓፒያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እንግዲያው ማርቆስ አንዳንድ ነገሮችን እንዳስታወሰ ቢጽፍም ምንም ስህተት አልሠራም፤ ምክንያቱም ከሰማው ነገር ምንም እንዳይቀንስ ወይም በመካከሉ የውሸት ቃል እንዳይጨምር በደንብ ይጠነቀቅ ነበር።”
ማቴዎስ በመጀመሪያ ወንጌሉን የጻፈው በዕብራይስጥ ቋንቋ ለመሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ፓፒያስ አንዱ ማስረጃ ይሆነናል። ፓፒያስ እንዲህ ይላል:- “ንግግሮቹን የጻፋቸው በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው፤ ከዚያም እያንዳንዱንም በተቻለው መጠን በጥራት ተርጉሞታል።” ፓፒያስ የሉቃስንና የዮሐንስን ወንጌል ዘገባዎች እንዲሁም ሌሎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ሳይጠቅስ የቀረ አይመስልም። እንደዚያ ከሆነ የወንጌሎቹን እውነተኛነትና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ለመሆናቸው ከቀደምት ምስክሮች መካከል አንዱ ይሆናል ማለት ነው። የሚያሳዝነው አሁን የሚገኙት የፓፒያስ ጽሑፎች ትንሽ ቁርጥራጮች ብቻ መሆናቸው ነው።
ለሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ ነበር
ፓፒያስ በሄራፖሊስ በሚገኘው ጉባኤ የበላይ ተመልካች እንደመሆኑ መጠን የማይታክት ተመራማሪ ነበር። ታታሪ ተመራማሪ ከመሆኑም በላይ ለቅዱሳን ጽሑፎች ቅንነት የተሞላበት አንድናቆት ያሳይ ነበር። በዘመኑ ከነበሩት የተምታቱ ጽሑፎች ይልቅ ኢየሱስ ወይም የእርሱ ሐዋርያት የተናገሯቸው የመሠረተ ትምህርት ቃላት ዋጋቸው የላቀ መሆናቸውን ፓፒያስ በትክክል ተናግሯል። — ይሁዳ 17
ፓፒያስ በጴርጋሞን በ161 ወይም 165 እዘአ ሰማዓት ሆኖ እንደሞተ ይነገራል። የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች የፓፒያስን ሕይወትና ጠባይ የቱን ያህል በጥልቅ እንደነካው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመማርና ስለ እነርሱ ለመወያየት ቅን ፍላጎት ነበረው። ዛሬም ክርስቲያኖች ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ ስለሆኑ እንዲሁ ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) እንደ ፓፒያስ ሁሉ እነርሱም ጌታ ለተናገራቸው ነገሮች ትልቅ ግምት ይሰጣሉ።