የአንባብያን ጥያቄዎች
በ1 ቆሮንቶስ 14:37 ላይ የተጠቀሰው “መንፈሳዊ ስጦታ” የሚለው አነጋገር የሚያሳየው አንድ ሰው ቅቡዕ በመሆን መንፈስ ቅዱስ መቀበሉን ነው? ወይስ ተአምራዊ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንዳለው?
በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ላይ ይህ ጥቅስ እንዲህ ይነበባል:- “ማንም ሰው ነቢይ እንደሆነ ወይም መንፈሳዊ ስጦታ እንዳለው የሚያስብ ከሆነ ይህ የምጽፍላችሁ ነገር የጌታ ትዕዛዝ እንደሆነ አውቆ ይቀበል።” — 1 ቆሮንቶስ 14:37
አንድ አንባቢ “መንፈሳዊ ስጦታ” የሚለውን ሐረግ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በመንፈስ ተመርጠው የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ስለመሆናቸው እንደሚጠቅስ አድርጎ ሊወስደው ይችላል። ወይም ደግሞ ይህንኑ ሐረግ የመንፈስ ቅዱስን ልዩ ስጦታ ለተቀበለ ሰው እንደሚሠራ አድርጎ መረዳት ይቻላል። ከጥቅሱ በፊት ያለውን ሐሳብ መሠረት በማድረግ መረዳት እንደምንችለው ሁለተኛው ትርጉም ትክክል ነው ወደማለት እናዘነብላለን።
እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ኒውማቲኮስ የሚለውን “ከመንፈስ ጋር የተያያዘ፣ ወይም መንፈሳዊ” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ያለውን ግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። የቃሉ የተለያዩ አገባቦች “መንፈሳዊ አካል”፣ “መንፈሳዊ በረከት”፣ “መንፈሳዊ ጥበብ” እና “መንፈሳዊ ቤት” የሚሉት ይገኙባቸዋል። — 1 ቆሮንቶስ 15:44፤ ኤፌሶን 1:3፤ ቆላስይስ 1:9፤ 1 ጴጥሮስ 2:5
በዚያ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈሳዊ” የሚለው ቃል የሚገልጻቸውን ስሞች (አካል፣ በረከት፣ ጥበብ፣ ቤት) ይዘረዝራል። በሌሎች ጊዜያት ግን “መንፈሳዊ” የሚለው ቃል ስሜቱና ተገቢው አተረጓጎሙ ከአገባቡ ተለይቶ ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል በ1 ቆሮንቶስ 2:14, 15 ላይ የፍጥረታዊ ሰውን አስተሳሰብ ከ‘ሆኒውማቲከስ’ ይህም ማለት ከ“መንፈሳዊ ሰው” ጋር ያነጻጽራል።
1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 እስከ 14 የሚያተኩረው በተአምራዊ የመንፈስ ስጦታዎች ላይ ነው። አምላክ በሥጋዊ እስራኤላውያን መጠቀሙን ፈጽሞ ያቆመ መሆኑንና ከዚያ ይልቅ ‘የአምላክ እስራኤል’ የሆኑትን ክርስቲያኖች እየባረከ እንዳለ ለማሳየት ይህንን ስጦታ ለአንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ሰጣቸው። (ገላትያ 6:16) ስለ እነዚህ ስጦታዎች ጳውሎስ “የፀጋውም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 12:4) ትንቢት መናገርና ልሳንን መተርጎም የመንፈስ ስጦታዎች እንደነበሩ ሁሉ ልዩ ጥበብ፣ እውቀትና እምነት ከመንፈስ ስጦታዎች መካከል ነበሩ። — 1 ቆሮንቶስ 12:8–11
ጳውሎስ የጻፈላቸው በቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች በአምላክ መንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ነበሩ። ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 6:11፤ 12:13) አዎን፣ ሁሉም “የመንፈሱን መያዣ” ተቀብለው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 5:5) ይሁን እንጂ የመንፈስ ቅዱስን ልዩ ስጦታ የተቀበሉት ሁሉም አልነበሩም። እንዲያውም ብዙዎቹ በልሳን የመናገር ስጦታ ይበልጥ የሳባቸው ይመስሉ ነበር፤ ለዚህ ስጦታ ከልክ ያለፈ ትኩረት ሰጥተዋል። ጳውሎስ ይህን አስተሳሰባቸውን ለማስተካከል ሲጽፍላቸው ትንቢት የመናገር ስጦታ ሊጠቅማቸው የሚችላቸውን ያህል በልሳናት መናገር እንደማይጠቅም ጠቁሞላቸዋል። በምዕራፍ 12 መደምደሚያ ላይ ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበሩትን ክርስቲያኖች:- “የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ” ሲል መከራቸው። — 1 ቆሮንቶስ 12:28–31
ከዚያም በምዕራፍ 14 መጀመሪያ ላይ እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳሰባቸው:- “ፍቅርን ተከታተሉ፣ [ታ ኒውማቲካን ] ይልቁንም ትንቢት መናገርንም በብርቱ ፈልጉ።” የሚፈልጉት ምንን ነበር? እነዚያ ክርስቲያኖች በመንፈስ መቀባትን መፈለግ አያስፈልጋቸውም፤ ምክንያቱም ቀደም ብለው አግኝተውታል። ጳውሎስ በምዕራፍ 12 ላይ እንዲፈልጉ አጥብቆ ያሳሰባቸው የመንፈስን “ስጦታዎች” እንደነበረ የታወቀ ነው። እንግዲያው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም 1 ቆሮንቶስ 14:1ን “መንፈሳዊ ስጦታንም . . . በብርቱ መፈለጋችሁን ቀጥሉ” በማለት ያስቀምጠዋል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም እዚህ ላይ ያለውን ታ ኒውማቲካ የሚለውን ቃል “መንፈሳዊ ስጦታዎች” ወይም “የመንፈስ ስጦታዎች” ብለው ይተረጉሙታል።
ይህንን መሠረት በማድረግ በምዕራፍ 14 መደምደሚያ አካባቢ ጳውሎስ ትንቢት መናገርን ከኒውማቲኮስ ጋር እንዳያያዘው እንመለከታለን። እዚህ ላይ ልክ በቁጥር 1 ላይ እንዳለው የመንፈስ ስጦታን መቀበል ማለቱ እንደሆነ በዙሪያው ካሉት ሐሳቦች መረዳት ይችላል። በአር ኤፍ ዊመዝ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ስፒች (አዲስ ኪዳን በዘመናዊ አነጋገር) የዚህን ትርጉም ሲያስቀምጥ እንዲህ ብሏል:- “ራሱን ነቢይ እንደሆነ ወይም መንፈሳዊ ስጦታ እንዳለው አድርጎ የሚቆጥር ማንኛውም ሰው አሁን የምጽፈውን እንደ ጌታ ትዕዛዝ አድርጎ ይቀበል።”
አዎን፣ ሁሉም ክርስቲያኖች የትንቢት ስጦታም ይሁን ሌላ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ቢኖራቸው፣ ነገሮች በጉባኤ ውስጥ እንዴት ሊከናወኑ እንደሚገባቸው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር መቀበልና መከተል ያስፈልጋቸው ነበር።