መላእክት ከእኛ ጋር አሉን?
ጉዳዩ የተፈጸመው ከመቅጽበት ነበር። ሜሪሊን በሐሳብ ተውጣ ያለችበትን ቦታ ሳታስተውል ዘና ብላ በባቡር ሐዲድ ላይ ትራመድ ነበር። ከየት መጣ ሳትል አንድ የሚያስገመግም ኃይለኛ ድምፅ ሰማች። ቀና ብላ ስትመለከት ወደ እርሷ እየመጣ ካለው ባቡር ብዙም ሳትርቅ ሐዲዱ ላይ መቆሟን ተገነዘበች! ሜሪሊን በድንጋጤ በድን ሆና ቀረች። ባቡሩ በጣም ከመቅረቡ የተነሣ የባቡሩን ሾፌር ሰማያዊ ዓይንና በፍርሃት የተሸበረ ፊቱን ለማየት ችላ ነበር። ቀጥሎ የሆነውን ነገር ሜሪሊን ፈጽሞ አትረሳውም። እንዲህ አለች፦ “ከበስተጀርባዬ አንድ ግዙፍ ነገር የገፈተረኝ ይመስልኛል። ከሐዲዱ ተወርውሬ ብዙም ሳልርቅ አመድ ላይ ወደቅሁ።” የደረሰባት ቢኖር ቀላል ጉዳት ነበር። ሜሪሊን ከሞት ያተረፋትን ሰው ለማመስገን ከወደቀችበት ተነሣች፤ ቢሆንም አንድም ሰው አልነበረም! ሜሪሊን ምን ብላ ደመደመች ? “ሕይወቴን ያተረፈው ጠባቂዬ የሆነው መልአክ ነው። አለበለዚያ ማን ሊሆን ይችላል?” አለች።
ይህ በጥርጣሬ የተሞላ ዓለም በድንገት ትኩረቱን ወደ መላእክት ያዞረ ይመስላል። በቅርብ ዓመታት ሰማያዊ ፍጡራን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የፊልሞችና ሌላው ቀርቶ የኒው ዮርክ ቲያትር ቤቶች ዋና ርዕስ ሆነዋል። ስለ መላእክት የሚያወሩ መጽሐፎች ጥሩ ገበያ ካላቸው ሃይማኖታዊ መጽሐፎች መካከል ከፍተኛውን ቦታ ይዘዋል። ከመላእክት ጋር የተያያዙ ክበቦች፣ ትምህርታዊ ጉባኤዎችና ጽሑፎች አሉ። አንድ ጽሑፍ እንዳሰፈረው “መላእክታዊ እርዳታ” ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያጠኑ ቡድኖች ተቋቁመዋል።
በመላእክቱ እንቅስቃሴ እየተጠቀሙ ያሉት ማለቂያ የሌለው የፍጆታ ዕቃዎችን የሚያቀርቡ ስግብግብ ነጋዴዎች ናቸው። ከሌላ ሰው ጋር በጋራ ሱቅ የከፈተች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የምትኖር አንዲት ሴት “መላእክት ያሉበት ማንኛውም ነገር ወፍራም ትርፍ ያስገኛል” ብላለች። በብዛት ከሚቸበቸቡት ስለ መላእክት ከሚናገሩት መጽሐፎች በተጨማሪ ይህች ሴት “በመላእክት ቅርጽ የተሠሩ ቅርጻ ቅርጾችን፣ ልብስ ላይ የሚለጠፉ ምስሎችን፣ አሻንጉሊቶችን፣ ቲ ሸርቶችን፣ ፖስተሮችንና የመልካም ምኞት መግለጫ ካርዶችን” የዘረዘረች ሲሆን እነዚህ በአጠቃላይ አንድ ጋዜጠኛ “ሰማያዊ ትርፍ” በማለት የጠራውን ትርፍ ማጋበሺያ ናቸው።
ነገር ግን መላእክትን አጥብቀው የሚደግፉ ሰዎች ይህ ፈጽሞ ጊዜ የሚያልፍበት ነገር አይደለም ብለው ይከራከራሉ። ለዚህ አባባላቸው “እውነተኛ” የመላእክት ገጠመኞችን በማስረጃነት ይደረድራሉ። አንዳንዶች ሰው የሚመስል መልአክ እንዳዩ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ የመላእክት እጅ እንዳለበት የሚያምኑበት ብርሃን አይተዋል፣ ድምፅ ሰምተዋል፣ በመንፈስ አብሯቸው ያለ መስሏቸዋል ወይም ከውስጣቸው ኃይለኛ ግፊት ተሰምቷቸዋል። እንደ ሜሪሊን ያሉ ብዙ ሰዎች መልአክ ከሞት እንዳተረፋቸው ይናገራሉ።
የተፈጠረው ነገር ምንድን ነው? “ከሰብዓዊ ፍጥረት ውጪ የሆነ ነገር” ስላጋጠማቸው ሰዎች የሚናገሩ ሁለት መጽሐፎችን የጻፈችው ጆን ዌስተር አንደርሰን “መንፈሳዊነት እንደገና በማንሰራራት ላይ ያለ ይመስለኛል” በማለት ተናግራለች። አንድ ሌላ መጽሐፍ ለማዘጋጀት እገዛ ያደረገች አልማ ዳንኤል የተባለች ሴት ከዚህ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥታለች። “ብዙ ሰዎች ልባቸው እንዲነካ ለማድረግ መላእክት ራሳቸውን እንዲያሳውቁ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። በተደጋጋሚ የሚታዩት ሆን ብለው ነው። ይህንን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።”
በእርግጥ ይህ ትክክል ነውን? ወይስ ስለ መላእክት ከተስፋፋው ትኩረት የሚስብ ነገር በስተጀርባ ሌላ ነገር ይኖር ይሆን? የዚህን መልስ ለማግኘት የአምላክን ቃል መመርመር አለብን። ቀጥለን እንደምንመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት እውነቱን ይናገራል።
[ምንጭ]
Pages 3 and 4: The New Testament: A Pictorial Archive from Nineteenth-Century Sources, by Don Rice/Dover Publications, Inc.