የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ሚስዮናውያንን እያሠለጠነ ይልካል
የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት በተለያዩ ስፍራዎች ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል። ከ1943 እስከ 1960 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በደቡብ ላንሲንግ ኒው ዮርክ ዩ ኤስ ኤ በሚገኙ ሕንፃዎች ውስጥ ከ95 አገሮች ለመጡ ተማሪዎች ልዩ ሥልጠና እየሰጠ 35 ጊዜ አስመርቋል። ከዚያ በኋላ ትምህርት ቤቱ ለ28 ዓመታት ያህል ሲሠራ ወደ ቆየበት በኒው ዮርክ ውስጥ ወደሚገኘው ዓለም አቀፉ ዋና መሥሪያ ቤት ተዛወረ። ከ1988 እስከ 1995 መጀመሪያ ድረስ የጊልያድ ትምህርት ቤት በዎልኪል ኒው ዮርክ ውስጥ ትምህርት ሲሰጥ ነበር።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ትምህርት ቤቱ የእንቅስቃሴ አድማሱን አስፍቷል። በጊልያድ ትምህርት ቤት ሥር በሜክሲኮ ሦስት ጊዜ፣ በጀርመን አምስት ጊዜ እንዲሁም በሕንድ ሁለት ጊዜ የአሥር ሣምንታት ኮርሶች ተሰጥተዋል። ከ1987 ጀምሮ የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚታወቀው የጊልያድ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት በ34 አገሮች ውስጥ ብቃቱ ላላቸው ወንዶች የስምንት ሳምንታት ልዩ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። አዲስ በተሠራው በኒው ዮርክ በሚገኘው በፓተርሰን የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከል ለ99ኛው የጊልያድ ክፍል የተሰጠው ትምህርት ግን የ20 ሳምንታት ኮርስ ነበር። ይህ ኮርስ ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የተጠናበት፣ በዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክና ድርጅት ላይ ውይይት የተደረገበት እንዲሁም በውጭ አገር የሚያከናውኑትን የሚስዮናዊነት ሥራ አስመልክቶ ሰፋ ያለ ምክር የተሰጠበት ነበር።
99ኛው ክፍል የተመረቀው መስከረም 2 ነበር። ሦስት ሰዓት የፈጀው የምረቃ ፕሮግራም የተካሄደው በአዲሱ የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከል አዳራሽ ውስጥ ነበር። አዳራሹ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። ፓተርሰን፣ ዎልኪልና ብሩክሊን ውስጥ በሚገኙ የቤቴል ሕንፃዎች ውስጥ ያሉ ሌሎች አድማጮች ፕሮግራሙን ለመከታተል እንዲችሉ የኤሌክትሮኒክ ሲስተም ተዘርግቶ ነበር። ይህ ከዘመዶቻቸውና ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር ለመጡት ተመራቂዎች ብቻ ሳይሆን የዚህን ግሩም የሆነ አዲስ ትምህርት ቤት ሕንፃዎች በመሥራቱ ተግባር ለተሳተፉት በመቶ የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች አስደሳች ቀን ሆኖላቸው ነበር።
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ኬሪ ባርበር በመክፈቻ ንግግሩ ላይ እየተከናወነ ያለው ነገር መሠረታዊ ትርጉም እንዳለው አብራርቷል። “ይህ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ምድር ላይ ታይቶ ለማይታወቀው ታላቅ የመለኮታዊ ትምህርት እንቅስቃሴ ማዕከል ይሆናል” አለ። በሴቲቱ ዘርና በእባቡ ዘር መካከል የሚካሄደው ጦርነት ፍጻሜውን ወደሚያገኝበት ጊዜ እየተቃረብን መሆኑን ገለጸ። (ዘፍጥረት 3:15) በመጪው ታላቁ መከራ ወቅት ከሚመጣው አስፈሪ ጦርነት በሕይወት መትረፍ የሚችሉት የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት ያገኙና ለቃሉ የሚታዘዙት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ጠቆመ።
እንዲህ አለ፦ “በአሁኑ ጊዜ ያለን የትምህርት መርሐ ግብር የተዘጋጀው በሁሉም ቦታ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች በምሳሌ 1:1–4 ላይ ወደ ተገለጸው ዓይነት የጉልምስና ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ነው። ይህ ጉልምስና ጥበብና ተግሣጽ ምን እንደሆኑ መገንዘብን፣ እውቀት መቅሰምን እንዲሁም ጥልቅ ማስተዋልን፣ ጽድቅን፣ ፍርድን፣ ቅንነትንና የማመዛዘን ችሎታን የሚያስገኘውን ተግሣጽ መቀበልን ያካትታል።” እንደነዚህ ያሉትን መንፈሳዊ ሀብቶች ማግኘት እንዴት ያለ ጥበቃ ነው!
ለተመራቂዎቹ የተሰጣቸው ምክር
በመክፈቻው ንግግር ላይ ከቀረቡት ከእነዚህ ማብራሪያዎች ቀጥሎ አምስት እጥር ምጥን ያሉ ተከታታይ ንግግሮች ለተመራቂዎቹ ቀረቡላቸው። ቀደም ሲል የጊልያድ አስተማሪ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በብሩክሊን ውስጥ የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት አባል የሆነው ሃሮልድ ጃክሰን “አምላካዊ ደስታችሁን አጥብቃችሁ ያዙ” በማለት አሳሰባቸው። ለረጅም ጊዜያት በሚስዮናዊነት ያገለገለውና በአሁኑ ጊዜ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሎይድ ባሪ “ይሖዋን በትሕትና ማገልገል” በሚል ርዕስ ንግግር አደረገ። ይህ ጠባይ ተመራቂዎቹ ራሳቸውን ከሚያጋጥሟቸው አዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ለማለማመድ እንዲችሉም ሆነ ከሌሎች ሚስዮናውያን፣ ከሚያገለግሏቸው ጉባኤዎችና ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገለጸ።
በአሁኑ ጊዜ በጊልያድ ፋኩልቲ ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኘው ካርል አዳምስ ለተማሪዎቹ “እምነት ምን እንድታደርጉ ይገፋፋችኋል?” የሚል ጥያቄ በማንሣት በጉዳዩ ላይ በጥልቀት እንዲያስቡ አደረጋቸው። በምድረ በዳ ባጋጠሟቸው ሁኔታዎች ያጉረመረሙትንና ወደ ግብፅ ለመመለስ የተመኙትን እስራኤላውያን ሳይሆን ካጋጠሙት ችግሮች ለመላቀቅ ወደ ከለዳውያን ዑር ከመመለስ ይልቅ በአምላክ መንግሥት ላይ ትምክህቱን የጣለውን አብርሃምን እንዲመስሉ አበረታታቸው። (ዘጸአት 16:2, 3፤ ዕብራውያን 11:10, 15, 16) የትምህርት ቤቱ ሬጅስትራር የሆነው ዩሊሲዝ ግላስ በመዝሙር 73 ላይ የተመዘገበውን የአሳፍን ተሞክሮ በማንሣት “ያገኛችኋቸውን በረከቶች ወደ ኋላ ተመልሳችሁ አስቡ” በማለት ተመራቂዎቹን አሳሰባቸው። በተጨማሪም የአስተዳደር አካሉ የትምህርት ኮሚቴ አባል የሆነው አልበርት ሽሮደር “ይሖዋ ይሰጣል” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። ለእንዲህ ዓይነቱ ስጦታ እንደ ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ የጊልያድ ትምህርት ቤትንና ይህ ትምህርት ቤት በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ታላቅ ሥራ ምን ያህል ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ እንዳለ ጠቆመ።
ከዚህ ቀጥሎ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆነው ሚልተን ሄንሽል “የአንድ አካል ብልቶች” በሚል ርዕስ ንግግር ሲያደርግ በምረቃው ላይ የተገኙት ሁሉ በተመስጦ አዳመጡት። ከሮሜ ምዕራፍ 12 ብዙ ጥቅሶችን እያነበበ አብራራ። ከተናገራቸው ነገሮች መካከል የሚከተለው ሐሳብ ይገኝበታል፦ “በጉባኤው ውስጥ ካሉ አብረውን ከሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ጋር ስላለን የተቀራረበ ግንኙነት በቁም ነገር ማሰብ ይኖርብናል።” አክሎም እንዲህ አለ፦ “ምን ጊዜም ቢሆን አንዳችን ሌላውን የይሖዋ ንብረት እንደሆነ አድርገን ብንመለከት ጥሩ ነው፤ በተጨማሪም ነቃፊዎችና ስሕተት ፈላጊዎች ከመሆን ይልቅ ሁልጊዜ ሌሎች ሰዎችን እንርዳ። የክርስቲያን ጉባኤን መንፈሳዊ አንድነት ስንጠብቅ ራሳችንን እንጠቅማለን።” በሚስዮናውያን ቤቶች ውስጥ ምግብ በሚዘጋጅበት ወቅት ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ምግብ መብላት የማይችል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲህ ዓይነቱን ሌሎችን የመርዳት መንፈስ እንዴት ማሳየት እንደሚቻል ጠቆመ። በተጨማሪም አነስተኛ ገቢ ካላቸው ክርስቲያን የእምነት ጓደኞቻቸው ጋር አብረው በመስክ አገልግሎት ሲሰማሩ እነዚህን ወንድሞቻቸውን ከመንቀፍ ይልቅ እንዲረዷቸው አበረታታቸው። ወንድም ሄንሽል እርስ በርሳችን ከልባችን የምንረዳዳ፣ የምንተናነጽና የምንበረታታ ከሆነ “ይሖዋ ይህን በማድረጋችን ምክንያት ይወደናል” አለ። ይህ ወደፊት ቀደም ሲል ይኖሩባቸው ከነበሩት አገሮች በብዙ መንገዶች በሚለዩ አገሮች ውስጥ ተሠማርተው ለሚያገለግሉት ሚስዮናውያን እንዴት ያለ ግሩም ምክር ነበር!
ተማሪዎቹን በይበልጥ ማወቅ
አርባ ስምንቱ የ99ኛው ክፍል ተማሪዎች አማካይ ዕድሜያቸው 32 ዓመት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአማካይ ከ11 ዓመት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፈዋል።
የምረቃው ፕሮግራም ክፍል የሆኑት ቃለ ምልልሶች አድማጮች ከተመራቂዎች መካከል ጥቂቶቹን በይበልጥ እንዲያውቋቸው አጋጣሚ ከፍተውላቸዋል። የዩናይትድ ስቴትሷ ኒኪ ሊብልና ከእንግሊዝ የመጣው ሳይመን ቦልተን የሚያስፈልጋቸውን ሥጋዊ ነገሮች በማቅረብ ረገድ በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት የፈተኑ ገጠመኞቻቸውን ተናገሩ። ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠታቸው ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟልቶላቸዋል።
የትውልድ ቋንቋዋ ፈረንሳይኛ የሆነው ኢዛቤል ካዛን በትውልድ አገሯ ውስጥ ለሚገኙ አረብኛ ተናጋሪ ሰዎች ለመመሥከር ስትል አረብኛ ቋንቋ እንደ ተማረች ገልጻለች። በ1987 ይህን ቋንቋ መማር ስትጀምር በፓሪስ ውስጥ የነበረው አንድ አነስተኛ ቡድን እሷንና አንዲት ቋንቋውን በመማር ላይ የነበረች እህትን ጨምሮ አራት አረብኛ ተናጋሪ ወንድሞችን ብቻ ያቀፈ ነበር። (ይህ ቀላል አልነበረም። እነዚህ እህቶች ሐሳብ ለመስጠት እንዲችሉ መጠበቂያ ግንብን ለመዘጋጀት በየሳምንቱ ስምንት ሰዓት ያጠፉ ነበር።) ይህ ሁሉ ከንቱ ልፋት ነበርን? በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ ውስጥ አረብኛ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ብቻ ያቀፉ አምስት ወረዳዎች ይገኛሉ። ሚኮ ፑሮ የተባለ ሌላ ተማሪ በትምህርት ቤት ያጠናው የፈረንሳይኛ ቋንቋ የትውልድ አገሩ በሆነችው በፊንላንድ ውስጥ ለአፍሪካውያን ስደተኞች እንዴት ለመስበክ እንዳስቻለው ተናገረ። በተጨማሪም ይኸው ቋንቋ በቤኒን ውስጥ ለተሰጠው የሚስዮናዊነት አገልግሎት ይጠቅመዋል። ቦኒ ቦዝ ካናዳ በምትገኘው በኩቤክ ውስጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማገልገል እንድትችል የፈረንሳይኛ ቋንቋን አቀላጥፋ ለመናገር ያደረገችውን ትግል በዝርዝር ገለጸች። በተጨማሪም ከዴንማርክ የመጣው ባያርኪ ራስሙሰን እሱና ባለቤቱ ለበርካታ ዓመታት በፌሮ ደሴቶች ሲያገለግሉ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች ተናገረ። አዎን፣ እነዚህ አዲስ ሚስዮናውያን ተሞክሮ ያካበቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው።
ተመራቂዎቹ በአፍሪካ፣ በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በምሥራቅ አውሮፓና በሩቅ ምሥራቅ በሚገኙ 19 አገሮች ውስጥ ተመደቡ። ቀደም ሲል ከነበሩት ክፍሎች የተመረቁት ሚስዮናውያን ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ አገልግለዋል። ከእነዚህ ተመራቂዎች ውስጥ ብዙዎቹ አሁንም በምድብ ሥራቸው ላይ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ እነዚህ አዲስ ሚስዮናውያን የመንግሥቱን ምሥራች እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ በሰፊው በማሰራጨቱ ተግባር ለመሳተፍ ከእነሱ ጋር ሊቀላቀሉ ነው።—ሥራ 1:8
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ክፍሎች
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀው 99ኛ ክፍል
ቀጥሎ ከፊት ለፊት በቆሙት ተማሪዎች በመጀመር ከግራ ወደ ቀኝ ስማቸው እንደሚከተለው ተዘርዝሯል።
(1) ሄፊ ኤስ፣ ሪሌይ ኢ፣ ሞርተንሰን ዲ፣ ኦነብል ኤ፣ ቦልተን ጄ፣ ፑል ጄ፣ ሲመስ ጂ፣ ሶዛ ኤል። (2) ፓሽኒትስኪ ቢ፣ ሼፐርድ ዲ፣ ፓሽኒትስኪ ደብልዩ፣ ዮርቪነን ጄ፣ ፖልሰን ኬ፣ ራስሙሰን ኢ፣ ሽዌቬ ኬ፣ ኦልሰን ኤል። (3) ፖልሰን ኢ፣ ሳምሰል ቲ፣ ቦዝ ቢ፣ ሃሪስ ኢ፣ ካዛን አይ፣ ሊብል ኤን፣ ሶዛ ፒ፣ ፑሮ ጄ። (4) ላገር ኬ፣ ላገር ቪ፣ ጎልደን ኬ፣ ቦልተን ኤስ፣ ጆንሰን ኤም፣ ጆንሰን ኤስ፣ ሊብል ኤ፣ ራስሙሰን ቢ። (5) ሃሪስ ዲ፣ ሳምሰል ደብልዩ፣ ሽዌቬ ኦ፣ ካዛን ኤል፣ ሪሌይ ቲ፣ ዮርቪነን ኦ፣ ፑሮ ኤም። (6) ሞርተንሰን ዲ፣ ጎልደን አር፣ ኦነብል ኤል፣ ሼፐርድ ኤም፣ ቦዝ አር፣ ሲመስ ቲ፣ ፑል ኢ፣ ኦልሰን ጄ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በተመደቡበት ቦታ በማገልገል ላይ የሚገኙ ሚስዮናውያን፦ (በስተግራ) የጊልያድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያውና የስድስተኛው ክፍል ተመራቂ የሆኑት ቻርለስ ሌትኮና ባለቤቱ ፈርን በብራዚል ውስጥ፤ (ከታች) የጊልያድ ትምህርት ቤት የሰባተኛው ክፍል ተመራቂ የሆነችው ማርታ ሄስ በጃፓን ውስጥ