የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በሩስያ የሚገኙ ‘የተጠሙ’ ሰዎችን መርዳት
“ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፣ ይጠግባሉና” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:6) ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ታግዶ በነበረበት በሩስያ መንፈሳዊ ውኃ የተጠሙ ብዙ ሰዎችን ለማርካት የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት አድርገው እርዳታ እየሰጡ እንዳሉ የሚከተሉት ተሞክሮዎች ያሳያሉ።
▪ ቫሊንቲና የምትባል አንዲት ሴት ለብዙ ዓመታት መልስ ያላገኘችላቸው ጥልቅ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ነበሯት። ለምሳሌ ‘ኢየሱስ የጸለየው ወደ ማን ነበር?’ የሚለው ጥያቄ አእምሮዋን ይከነክናት ነበር። ኢየሱስ ከእርሱ ወደሚበልጠው አንድ አካል ጸልዮ መሆን አለበት ብላ አሰበች። እንዲሁም የዚህ አካል ስም ማን እንደሆነም ለማወቅ ጓጓች።
ወደ ሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሄደች። ይሁን እንጂ በዚህ ሃይማኖት ውስጥ ለጥያቄዎቿ መልስ አላገኘችም። ተስፋ ቆርጣ ወደ ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ሄደች። ይሁን እንጂ እዚያም ቢሆን ግልጽ የሆነ መልስ ማግኘት አልቻለችም። ከዚህ በኋላ የት መሄድ እንዳለባት ስላላወቀች ለጥያቄዎቿ መልስ ለማግኘት በግሏ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመረች። ይህም ምንም ውጤት አላስገኘላትም። እርዳታ ለማግኘት ጸለየች።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በሯን አንኳኩ። የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩአት። በመጨረሻም ኢየሱስ የጸለየው ወደ ማን እንደሆነ አወቀች! ከምሥክሮቹም ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራ ማጥናት ጀመረች። ብዙዉን ጊዜም በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተሙትን ጽሑፎች በማንበብና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በማመሳከር ሌሊቱን ሙሉ ታሳልፍ ነበር። ወዲያውም ቫሊንቲና እውነትን እንዳገኘች አረጋገጠች። በሦስት ወር ውስጥ በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመረች። ከዚያም ከሁለት ወር በኋላ ተጠመቀች። እውነትን ለማግኘት ያደረገችው ጸሎት የታከለበት ጥረት ጥሩ ዋጋ አስገኘላት።
▪ አንድ የይሖዋ ምሥክር ራቅ ወዳለ አካባቢ ሄዶ ለመስበክ በአውቶቡስ ይጓዝ ነበር። በጉዞ ላይ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸውን ተስፋዎች ለአንዲት ወጣት ሴት ነገራት፤ ወጣቷ ሴት ግን ፍላጎት አላሳየችም ነበር። ከሁለት ወር በኋላ እዚያው አካባቢ የሕዝብ ንግግር ለመስጠት የይሖዋ ምሥክሩ ለሁለተኛ ጊዜ ጉዞ አደረገ። ከንግግሩ በኋላ ወደ አንድ እንግዳ ቀረብ ብሎ “መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ምሥራች ከዚህ ቀደም የነገረህ ሰው አለ?” ብሎ ጠየቀው። ሰውየውም “አዎን፣ አንተ ነግረኸኛል” በማለት መለሰ። የይሖዋ ምሥክሩም ሰውየው እየቀለደ ያለ መሰለው። ከሁለት ወር በፊት በአውቶቡስ እየተጓዙ እያለ ምሥክሩ ከአንዲት ወጣት ሴት ጋር ያደርግ የነበረውን ውይይት አዳምጦ እንደነበር ወጣቱ ሰው ገለጸ። “ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ፈለግኩ። ይሁን እንጂ አንተ ከአውቶቡሱ ቀደም ብለህ ወረድክ። እኔም የይሖዋ ምሥክሮችን ዳግመኛ አላገኛቸውም ብዬ አስቤ ነበር። ከዚያም በምሠራበት ቦታ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠና አንድ ሰው አገኘሁ። በዚህም ምክንያት እዚህ ልመጣ ቻልኩ!”
ሰውየውና ባለቤቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሥራው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እንደማይጣጣም ለመገንዘብ ቻለ። በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና ለመያዝ ስለ ፈለገ የሥራውን ዓይነት ለወጠ። አሁን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ይናገራል። ባለቤቱም በምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እድገት እያደረገች ነው።
በጣም ሰፊ ክልል በሆነው ሩስያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅን ለሆኑ ሰዎች ሁሉ “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” ብሎ የመጋበዝ ድርሻ በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው።—ራእይ 22:17