101ኛው የጊልያድ ክፍል ተመራቂዎች ለመልካም ሥራ የሚቀኑ ሚስዮናውያን
ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክም ሆነ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ሥራን ለመሥራት ቀናተኛ ናቸው። ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ሥራ በመፈጸም ማለትም ‘መልካም ሥራ ለመሥራት ቅንዓት ያለውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ ለማንጻት ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ በመስጠት’ ቅንዓት እንዳለው አሳይቷል። (ቲቶ 2:14) የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጊልያድ ትምህርት ቤት የ101ኛው ክፍል 48 አባላት ለመልካም ሥራ ቅንዓት እንዳላቸው አሳይተዋል። የእነዚህ ሚስዮናውያን የምረቃ ፕሮግራም የተካሄደው መስከረም 7, 1996 ፓተርሰን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ነው።
ቀናተኛ ሆኖ ለመቀጠል የሚረዱ ተግባራዊ ምክሮች
የምረቃው ፕሮግራም ሊቀ መንበር የነበረው ለ70 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈውና የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ኬሪ ባርበር ነበር። ወንድም ባርበር በመክፈቻ ንግግሩ ላይ “የዓለም ብርሃን” የነበረው ኢየሱስ ስላከናወነው የስብከትና የማስተማር ሥራ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 8:12) ኢየሱስ ይህን ክቡር ሥራ ለራሱ ብቻ ከመያዝ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱም ብርሃናቸውን እንዲያበሩ አጥብቆ እንዳሳሰባቸው ወንድም ባርበር ጠቀሰ። (ማቴዎስ 5:14-16) ይህ የአገልግሎት መብት የአንድ ክርስቲያን ሕይወት ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ከመርዳቱም ሌላ ‘የብርሃን ልጆች ሆነው በሚመላለሱት’ ሁሉ ላይ ከባድ ኃላፊነት ያስከትላል።—ኤፌሶን 5:8
ከዚህ የመክፈቻ ንግግር በኋላ ብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የአስተዳደር ቢሮ ውስጥ የሚያገለግለው ዶን አዳምስ ንግግር እንዲያደርግ ተጋበዘ። የንግግሩ ርዕስ “ወደኋላ ማፈግፈግ ሳይሆን ወደፊት መግፋት” የሚል ነበር። ወንድም አዳምስ ያተኮረው በራሱ በጊልያድ ትምህርት ቤትና ትምህርት ቤቱ በተቋቋመበት ዓላማ ላይ ማለትም የምሥራቹን ስብከት ወደ ሌሎች አገሮች በማዳረሱ ሥራ ላይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች እያዘጋጀ በዓለም ዙሪያ የሚያሰራጨው የአምላክ ድርጅት ስላደረገው መስፋፋት አብራርቷል። በ1995 የወጣው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ እስካሁን ድረስ በ111 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን በተጨማሪ ቋንቋዎችም እንዲዘጋጅ ፕሮግራም ተይዞለታል። አዳዲስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በጥቂት ወራት ውስጥ ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ወደ መጠመቅ እንዲደርሱ በመርዳት በኩል ትልቅ ድርሻ አበርክቷል። በመሆኑም አዲሶቹ ሚስዮናውያን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የሚያግዝ አዲስ መጽሐፍ አላቸው ማለት ነው።
ቀጥሎ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሊማን ስዊንግል “ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችሁን ቀጥሉ” በሚል ርዕስ በራእይ 7:15 ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ። ይሖዋ ራሱ ደስተኛ አምላክ በመሆኑ አንድን ሰው ደስተኛ የሚያደርገው ነገር እርሱን ሳያቋርጥ ማገልገሉ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) በዚህ አስደሳች የሆነ አገልግሎት አማካኝነት ከምድር ዙሪያ እጅግ ብዙ ሰዎች እርሱን ለማምለክ ተሰባስበዋል። ባለፉት በርካታ ዓመታት የጊልያድ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸው ሚስዮናውያን ከእነዚህ ብዙዎቹ ትክክለኛውን የእውነት እውቀት እንዲያገኙ በመርዳቱ ሥራ ተካፍለዋል። እንግዲያውስ ዛሬም ቢሆን ቁጥራቸው እያደገ የመጣውን የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ለመሰብሰብ የሚላኩትን ሚስዮናውያን የይሖዋ በረከት እንደማይለያቸው እርግጠኛ መሆን የምንችልበት በቂ ምክንያት አለን።
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ዳንኤል ሲድሊክ ያተኮረበት ጭብጥ ደግሞ “የይሖዋን ደስታ ማንጸባረቅ” የሚል ነበር። አዲሶቹን ሚስዮናውያን ጨምሮ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን ጎዳና እንዲሁም ዛሬ ሕይወትን በተሻለ ሁኔታ መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ ለሌሎች ሰዎች የማስተማር መብት እንዳገኙ ገልጿል። ወንድም ሲድሊክ “ማስተማር መልሶ የሚክስ ሙያ ነው። ይህ በሚያስተምሩትም ሆነ በሚማሩት ሰዎች ፊት ላይ ይንጸባረቃል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 16:8-11) በኢስቶኒያ የሚገኝ አንድ ሚስዮናዊ “በምድር ላይ ከሁሉም የላቀ መልእክት ይዘናል፤ ይህም በፊታችን ላይ ይንጸባረቃል” ሲል የተናገረውን ጠቅሷል። ፊታችን ላይ የሚነበበው ነገር ለብዙዎች በር የሚከፍትና ፍላጎታቸውን የሚያነሣሣ ሊሆን ይችላል። ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች ደስተኛ የሆኑበትን ምክንያት ለማወቅ ይፈልጋሉ። ወንድም ሲድሊክ “እንግዲያውስ በፊታችሁ ላይ ስለሚነበበው ስሜት በጥሞና አስቡ” በማለት ምክር ሰጥቷል። “ሰዎች ደስተኛ ፊት ሲያዩ ደስ ይላቸዋል።”
በ1949 ከተካሄደው ከአሥራ ሁለተኛው ክፍል አንስቶ ለጊልያድ ተማሪዎች ትምህርት በመስጠቱ ሥራ ሲካፈል የቆየው ወንድም ዩሊሰስ ግላስ “በትዕግሥት ነፍሳችሁን ጠብቁ” በሚል ርዕስ ንግግር አቅርቧል። ትዕግሥት ምንድን ነው? አንድን ነገር ተረጋግቶ መጠበቅ፣ ሰላም የሚነሳ ወይም የሚያስጨንቅ ነገር እያለ መቻል የሚል ትርጉም አለው። ትዕግሥተኛ ሰው ተረጋግቶ ይጠብቃል፤ ትዕግሥት የለሽ ሰው ግን ችኩልና ግልፍተኛ ነው። ወንድም ግላስ “ብዙ ሰዎች ትዕግሥት የድክመት ወይም ቆራጥ ያለመሆን ምልክት” እንደሆነ አድርገው እንደሚያስቡ ከጠቀሰ በኋላ “በይሖዋ ዘንድ ግን ጥንካሬና ዓላማ ያለን ሰዎች መሆናችንን የሚያሳይ” ነው በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 16:32) ትዕግሥት የሚያስገኘው ወሮታ ምንድን ነው? አንድ የቻይናውያን ብሂል “ጊዜያዊ ቁጣን በትዕግሥት ማሳለፍ ከመቶ ቀናት ሥቃይ ያድንሃል” ይላል። ወንድም ግላስ “ትዕግሥት የአንድን ሰው ሁለንተናዊ ባሕርይ ያሻሽላል። ሌሎች መልካም ባሕርይዎቹ ለዘለቄታው እንዲጠበቁ ያደርጋል። እምነቱን ውበት ያላብስለታል፣ ሰላሙ ዘላቂ ይሆናል ፍቅሩም አይናወጥም” ሲል ተናግሯል።
ለ11 ዓመታት ኬንያ ውስጥ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለውና በአሁኑ ጊዜ የጊልያድ አስተማሪ ሆኖ የሚያገለግለው ማርክ ኑሜር “ከይሖዋ አምላክ በድርጅቱ በኩል የአገልግሎት ምድብ መቀበል ትልቅ መብት ነው” ብሏል። “ያለ እምነት ብዙ አትገፉም” በሚል ጭብጥ የይሁዳ ንጉሥ ስለነበረው ስለ አካዝ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ንጉሡ የተሰጠውን ሥራ ሲያከናውን የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለየው ኢሳይያስ ቢያረጋግጥለትም አካዝ በይሖዋ ላይ እምነት ሳይጥል ቀርቷል። (ኢሳይያስ 7:2-9) ወንድም ኑሜር በመቀጠል ሚስዮናውያን እንዲሁም ሁላችንም በተሰጠን ቲኦክራሲያዊ ሥራ ወደፊት ለመግፋት በይሖዋ ላይ እምነት ሊኖረን እንደሚያስፈልግ ገልጿል። በሚስዮናዊነት የአገልግሎት መስክ የሚያጋጥሙት ፈታኝ ሁኔታዎች ጠንካራ እምነት የሚጠይቁ ናቸው። “በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ፍጹም የሆነ ምንም ነገር እንደሌለ አትዘንጉ” ሲል ወንድም ኑሜር ተናግሯል።
በቅንዓት መሥራትን የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች
ተማሪዎቹ በጊልያድ ሥልጠናቸው ወቅት በእያንዳንዱ ሳምንት መጨረሻ ላይ ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት ተካፍለዋል፤ በሚስዮናዊነት ተመድበው በሚሄዱበትም ቦታ ዋነኛ ትኩረታቸው የሚሆነው ይኸው ነው። የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተዳደር አባል የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ ለ15 ተማሪዎች ቃለ ምልልስ አድርጎላቸው ተሞክሯቸውን ተናግረዋል። ከዚያም በአገልግሎት ዘርፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው ሊየን ዊቨር እና የቤቴል ሥራዎች አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆነው ሎን ሺሊ ከአፍሪካና ከላቲን አሜሪካ ከመጡ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፤ እነዚህ ወንድሞች ከሚስዮናውያኑ መስክ የተገኙ ተሞክሮዎችን ከመናገራቸውም ሌላ ለተመራቂዎቹ ሚስዮናውያን ግሩም ምክሮችን አስተላልፈዋል። ሴራልዮን ውስጥ በ1995 የአገልግሎት ዓመት ከተጠመቁት መካከል 90 በመቶ የሚያክሉትን የረዷቸው ሚስዮናውያን መሆናቸው ተገልጿል። ይህ ቅንዓት የተሞላበት ሥራ ያስገኘው እንዴት ያለ ግሩም ውጤት ነው!
በመጨረሻም የማኅበሩ ፕሬዘዳንት ሚልተን ሄንሸል 2,734 ለሚያክሉት ተሰብሳቢዎች “የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ተወዳዳሪ የለውም” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። የአምላክ ድርጅት አቻ የሌለው በምን መንገድ ነው? በግዝፈቱ ወይም በብርታቱ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ የጽድቅ ሕግጋትና ፍርድ ስለሚመራ ነው። ጥንት ከሌሎቹ ልዩ የሚያደርጉ መመሪያዎች የተሰጡት የይሖዋ ሕዝብ ለነበረው ለእስራኤል ብሔር ነበር። (ሮሜ 3:1, 2) ዛሬ የይሖዋ ድርጅት በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት እንደ አንድ አካል ሆኖ ይንቀሳቀሳል። (ማቴዎስ 28:19, 20) እየጎለበተና እያደገ ነው። ከፍተኛ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ መመሪያ የሚፈልግ የአስተዳደር አካል ያለው ሌላ ድርጅት በዚህች ምድር ላይ ይገኛልን? በዚህና በሌሎችም መንገዶች የይሖዋ ድርጅት በእውነትም ተወዳዳሪ የለውም።
ለተማሪዎቹ ዲፕሎማ ከተሰጠና ስላገኙት ልዩ ሥልጠና ምሥጋናቸውን የገለጹበት ደብዳቤ ከተነበበ በኋላ ይህ አስደሳች ፕሮግራም ተጠናቀቀ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች፦ 9
የተመደቡባቸው አገሮች፦ 12
የተማሪዎቹ ብዛት፦ 48
አማካይ ዕድሜ፦ 31.7
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 13.8
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 9.8
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጊልያድ ትምህርት ቤት የ101ኛው ክፍል ተመራቂዎች
ቀጥሎ ከፊት ለፊት ተማሪዎች በመጀመር ከግራ ወደ ቀኝ ስማቸው ተዘርዝሯል።
(1) ስዊንት ኤች፣ ዜዘንስኪ ኤ፣ ሃይፊልድ ኤል፣ ማርኬዶ ኤስ፣ ዲል ኤ፣ ቻቬዝ ቪ፣ ስሚዝ ጄ፣ ሴሌኒየስ ኤስ (2)ኩርዝ ዲ፣ ክላርክ ሲ፣ ሊዝበርን ጄ፣ ሞርተንሰን ደብልዩ፣ ብሩምሊ ኤ፣ ቶኢካ ኤል፣ ማርተን ኤ፣ ስሚዝ ዲ (3)ዜዘንስኪ ዲ፣ ባርገር ኤል፣ ጋራፍሎ ቢ፣ ካልዳል ኤል፣ ቻቬዝ ኢ፣ ፍሮዲንግ ኤስ፣ ካን አር፣ ሴሌኒየስ አር (4)ስዊንት ቢ፣ ባርጋር ኤም፣ ጋራፍሎ ፒ፣ ሆልምብላድ ኤል፣ ኪዘር ኤም፣ ፍሮዲንግ ቲ፣ ፖልፍሬማን ጄ፣ ፖልፍሬማን ዲ (5)ሚንግዌስ ኤል፣ ሊዝበርን ኤም፣ ሜርካዶ ኤም፣ ኩርዝ ኤም፣ ዲል ኤች፣ ቶኢካ ጄ፣ ክላርክ ኤስ፣ ካን ኤ (6)ሚንግዌስ ኤፍ፣ ማርተን ቢ፣ ሃይፊልድ ኤል፣ ሆልምብላድ ቢ፣ ብሩምሊ ኬ፣ ካልዳል ኤች፣ ሞርተንሰን ፒ፣ ኪዘር አር