የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ኢየሱስ እንደ መሲሕና ንጉሥ በመሆን ጥሩ አቀባበል ተደረገለት!
ኒሳን 9, 33 እዘአ እየተንጫጫ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባው ሕዝብ ብዙ አይሁዳውያንን በጣም አስገርሟል። ከማለፍ በዓል በፊት ሰዎች ወደ ከተማይቱ ሲጎርፉ ማየት ያልተለመደ ነገር ባይሆንም የዚያን ዕለቱ ግን ለየት የሚያደርገው ነገር ነበር። ሰዎቹ ወደ ከተማይቱ የመጡት አንድ በአህያ ውርንጫ ላይ የተቀመጠ ሰው አጅበው ነው። ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ሰዎቹ ልብሳቸውንና የዘንባባ ዝንጣፊዎችን እፊቱ እያነጠፉ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ይጮኹ ነበር። ቀደም ብለው ኢየሩሳሌም ደርሰው የነበሩ በርካታ ሰዎች ሕዝቡን ሲመለከቱ እነሱም አብረው ለማጀብ ተገፋፉ።— ማቴዎስ 21:7-9፤ ዮሐንስ 12:12, 13
ኢየሱስ አሁን ጥሩ አቀባበል ቢደረግለትም ከፊቱ መከራ እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር። እንዲያውም ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚህችው ከተማ ውስጥ ይገደላል! ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ለእሱ በጣም አደገኛ ቦታ እንደሆነች እያወቀ በዚህ ከፍተኛ ትኩረት በሚስብ አኳኋን ወደ ከተማይቱ ለመግባት ዝግጅት አደረገ።
ጥንት የተነገረ አንድ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ
ኢየሱስ በከፍተኛ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚገባ ዘካርያስ በ518 ከዘአበ ተንብዮ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ እልል በዪ፤ እነሆ፣ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። . . . ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፣ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሆናል።”— ዘካርያስ 9:9, 10
ስለዚህ ኢየሱስ ኒሳን 9 ቀን ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል። ይህ እንዲያው በአጋጣሚ የሆነ ጉዳይ ሳይሆን በሚገባ ታስቦበት የተደረገ ነው። ቀደም ብሎ ማለትም ገና ከኢየሩሳሌም ውጭ ሳሉ ኢየሱስ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል አዘዛቸው:- “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፣ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች ቢላችሁ:- ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።” (ማቴዎስ 21:1-3) ነገር ግን ኢየሱስ በአህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባት የፈለገው ለምንድን ነው? ሕዝቡ ያደረገለት አቀባበልስ ምን ትርጉም ነበረው?
ንግሥናን የሚመለከት መልእክት
በቃል ከሚነገር ነገር ይልቅ የሚታይ ነገር ይበልጥ ኃይል አለው። ስለዚህ ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ነቢያቱ የሚናገሩትን መልእክት ኃይል ለማጠንከር ራሳቸው መልእክቱን በተግባር እንዲያሳዩ ያደርግ ነበር። (1 ነገሥት 11:29-32፤ ኤርምያስ 27:1-6፤ ሕዝቅኤል 4:1-17) በዚህ መንገድ በተግባር በማሳየት መልእክት ማስተላለፍ ደንዳና ልብ ባለው ሰው አእምሮ ውስጥ እንኳ በማይጠፋ ሁኔታ ይቀረጻል። ኢየሱስም በተመሳሳይ በአህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በመግባት ሊያስተላልፍ የፈለገውን አንድ ኃይለኛ መልእክት በተግባር አሳይቷል። እንዴት?
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አህዮች ለከፍተኛ የክብር መግለጫ ያገለግሉ ነበር። ለምሳሌ ሰሎሞን ንጉሥ ሆኖ ለመቀባት የሄደው በአባቱ ‘ሴት በቅሎ’ ተቀምጦ ነው፤ በቅሎ ደግሞ በማዳቀል የምትገኝ የወንድ አህያ ዝርያ ነች።a (1 ነገሥት 1:33-40) ስለዚህ ኢየሱስ በአህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣቱ ራሱን እንደ ንጉሥ አድርጎ ማቅረቡን የሚያመለክት ነበር። ሕዝቡ ያደረጉት ነገር ይህን መልእክት ይበልጥ አጠናክሮታል። ሕዝቡ በአብዛኛው የገሊላ ነዋሪዎች እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፤ በኢየሱስ ፊት ልብሳቸውን ማንጠፋቸው ኢዩ ንግሥናውን ለሕዝብ ባስተዋወቀበት ጊዜ የተደረገውን የሚያስታውስ ነበር። (2 ነገሥት 9:13) ሰዎቹ ኢየሱስን “የዳዊት ልጅ” ብለው መጥራታቸው ሕጋዊ የመግዛት መብት እንዳለው የሚያሳይ ነበር። (ሉቃስ 1:31-33) የዘንባባ ዝንጣፊዎችን መያዛቸው ደግሞ ለንጉሣዊ ሥልጣኑ ተገዢዎች መሆናቸውን የሚያመለክት ነበር።— ከራእይ 7:9, 10 ጋር አወዳድር።
ስለዚህ ኒሳን 9 በኢየሩሳሌም የተከናወነው ሁኔታ ኢየሱስ የተሾመ የአምላክ መሲሕ እና ንጉሥ መሆኑን በማያሻማ መንገድ አሳይቷል። እርግጥ ኢየሱስ ራሱን በዚህ መንገድ ማቅረቡ ያላስደሰታቸው ሰዎች ነበሩ። በተለይ ፈሪሳውያን ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ንጉሣዊ ክብር ማግኘቱ ፈጽሞ ተገቢ እንዳልሆነ ተሰምቷቸዋል። “መምህር ሆይ፣ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ሲሉ ጠየቁት፤ እንዲህ ብለው የጠየቁት በቁጣ ስሜት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ደግሞ “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ሲል መለሰላቸው። (ሉቃስ 19:39, 40) አዎን፣ የአምላክ መንግሥት የኢየሱስ ስብከት ጭብጥ ነበር። ሰዎች ይህን መልእክት ተቀበሉትም አልተቀበሉትም በድፍረት ከማወጅ ወደኋላ አላለም።
ከዚህ የምናገኘው ትምህርት
ነቢዩ ዘካርያስ በተነበየው መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም መግባት ለኢየሱስ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ነገር ነበር። እንዲህ ማድረጉ የጠላቶቹን ቁጣ እንደሚያስነሳበት ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ተከታዮቹ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩና ‘አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ አዝዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በተመሳሳይም ይህን ሥራ ማከናወን ድፍረትን የሚጠይቅ ነበር። ይህ መልእክት የሚያስቆጣቸው ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ለዚህ መልእክት ግዴለሾች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ይቃወሙታል። አንዳንድ መንግሥታት በስብከቱ ሥራ ላይ አንዳንድ ገደቦችን ጥለዋል ወይም እስከ ጭራሹ ሥራው እንዲታገድ አድርገዋል።
ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ሰዎች ለመስማት ቢፈልጉም ባይፈልጉም ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ምሥራች መሰበክ እንዳለበት ይገነዘባሉ። (ሕዝቅኤል 2:7) ይህን ሕይወት አድን ሥራ በሚያከናውኑበት ጊዜ ኢየሱስ “እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት የገባው ቃል ያጽናናቸዋል።— ማቴዎስ 28:20
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ውርንጫው “ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት” መሆኑን የማርቆስ ዘገባ ተጨማሪ መግለጫ ይሠጣል። (ማርቆስ 11:2) ከዚህ ቀደም ለምንም ግልጋሎት ያልዋለ እንሰሳ ለቅዱስ ዓላማ መጠቀም ተገቢ ነበር።— ከዘኁልቁ 19:2፤ ዘዳግም 21:3 እና ከ1 ሳሙኤል 6:7 ጋር አወዳድር።