የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ወደ ይሖዋ ቲኦክራሲያዊ ድርጅት መሸሽ
ከብዙ ዘመናት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ‘ይሖዋን በባሕር ደሴቶች አክብሩ’ ብሎ እንዲያውጅ ተገፋፍቶ ነበር። (ኢሳይያስ 24:15) ኢየሱስ “የመንግሥት ወንጌል . . . ይሰበካል” ብሎ በተናገረው ‘ዓለም’ ውስጥ የባሕር ደሴቶቸ እንደሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ይገነዘባሉ።— ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10
ከታሂቲ ሰሜናዊ ምሥራቅ 1,400 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው የማርኬሳስ ደሴቶች ይገኛሉ። እነዚህ ደሴቶች በደቡብ ፓስፊክ ፍሬንች ፖሊኔዥያ በመባል በሚጠሩት ራቅ ብለው ከሚገኙት የደሴት ስብስብ መካከል የሚገኙ ናቸው። ለም የሆነው የእሳተ ገሞራ አፈር እንዲሁም ሞቃታማና እርጥበት አዘል የሆነው አየር በእነዚህ ደሴቶች ልምላሜ እንዲኖር አስተዋፅዖ አድርገዋል። ይሁን እንጂ የማርኬሳስ ደሴቶች ሌላ ዓይነት ፍሬም እያፈሩ ናቸው። ሂቫ ኦ በተባለው ደሴት ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ የሰጡ የአንድ ቤተሰብ ሁኔታ ተመልከት።
ዣን እና ናዲን የተባለችው ባለቤቱ ይኖሩበት በነበረው ሠልጥኗል በሚባለው የምዕራብ አውሮፓ ኅብረተሰብ አልተደሰቱም። በዚህም የተነሳ ጥድፊያ የበዛበትን ያንን መኖሪያ ለቀው ለመሄድ ወሰኑና ልጃቸውን ይዘው ወደ ማርኬሳስ ደሴቶች ሄዱ። ከቀርከሃ የተሠራው አዲሱ ቤታቸው የሚገኘው ራቅ ብሎ በሚገኝ አንድ ሸለቆ ውስጥ ነበር። አቅራቢያቸው ወደሚገኙ አጎራባች መንደሮች ለመድረስ ወጣ ገባ በበዛበት ተራራማ መንገድ ላይ ለሁለት ሰዓታት መጓዝ ነበረባቸው። ሐኪም፣ ትምህርት ቤትና ገበያ ያለው በጣም ቅርብ የሚባለው መንደር በጂፕ መኪና ሦስት ሰዓት ይፈጅ ነበር።
ዣን እና ናዲን ለሃይማኖት ግዴለሾች ነበሩ። ሆኖም የሕይወት አመጣጥን አስመልክቶ በሚደረግ ውይይት ላይ ይካፈሉ ነበር። ብዙውን ጊዜም ውስብስብ የሆነውን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ ተንትነው ይናገሩ ነበር። ይሁን እንጂ የሚያምኑበት የትኛውም ጽንሰ ሐሳብ እርካታ አላመጣላቸውም።
ከሰው ተገልለው ለስድስት ዓመታት ብቻቸውን ከኖሩ በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ሄደው ሲጎበኟቸው ያልጠበቁት ነገር ሆነባቸው። ምሥክሮቹ ዣን እና ናዲን እዚህ አካባቢ እንደሚኖሩ አቅራቢያቸው ካሉት መንደሮች ተረድተው ነበር። እንደተለመደው ውይይታቸው ወደ ዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ አመራ። እንዲያውም ምሥክሮቹ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ለባልና ሚስቱ አሳዩአቸው። ዣን እና ናዲን ሕይወት እንዴት እንደተገኘ አጠቃላይ ማብራሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ በማግኘታቸው በጣም ተደሰቱ።
ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ሦስት ዓመት በሚያክል ጊዜ ውስጥ ዣን እና ናዲን የማያቋርጥ እድገት አደረጉ። መላዋ ምድር በቅርቡ ገነት እንደምትሆን አምነው ተቀበሉ። የቤተሰባቸው ቁጥር በሦስት ልጆች በመጨመሩ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አራት ሰዓት መጓዝ አስቸጋሪ ሆነባቸው። ሆኖም ይህ ሁኔታ ስብሰባ እንዳይሄዱ አላገዳቸውም። በመጨረሻም ዣን እና ናዲን ለይሖዋ ያደረጉትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት አሳዩ። ይህን ያደረጉት 38 ከፍተኛ ተሰብሳቢዎች በተገኙበት በዋናው መንደር በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ነበር!
ቤተሰቡ ትንሹን የመንግሥት አስፋፊዎች ቡድን ለመርዳት ሲል ይኖርበት የነበረውን ገለልተኛ መኖሪያ ለቆ ለመሄድ ወሰነ። አንድ ሺህ አካባቢ ነዋሪ ወዳለበት መንደር ሄዱ። በአሁኑ ጊዜ በዚህ መንደር ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ዣን የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ይሠራል። ከሥልጣኔ ለመራቅ ብሎ ወደ ደሴቶች ሸሽቶ የሄደው ይህ ቤተሰብ ብቸኛ እውነተኛ መቅደስ የሆነውን የይሖዋን ቲኦክራሲያዊ ድርጅት በማግኘቱ እንደ መብት አድርጎ ይቆጥረዋል።