የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ከአጋንንት ተጽዕኖ መላቀቅ
መናፍስታዊ ድርጊት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መቆጣጠር ከጀመረ ረዥም ዘመን አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ ከዚህ ዓይነቱ ተጽእኖ መላቀቅ ይቻላል! በጥንቷ የኤፌሶን ከተማ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከመናፍስታዊ ድርጊት መላቀቅ ችለዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ዘገባ “ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው . . . አቃጠሉት፤ . . . እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር” በማለት ይገልጻል።— ሥራ 19:19, 20
በዛሬው ጊዜም ያለው የክርስቲያን ጉባኤ በተመሳሳይ መንገድ እያደገ ነው። በኤፌሶን እንደነበሩት ሰዎች ሁሉ አማኝ ከሆኑት ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት በአጋንንታዊ ድርጊት ይካፈሉ የነበሩ ናቸው። ከዚምባቡዌ የተገኘው የሚከተለው ተሞክሮ ይህንን ሁኔታ ያሳያል።
ጎጎ (የሴት አያት) ምቱፓ በነበራት የመናፍስት ኃይል በሰፊው የታወቀች ነበረች። ከዛምቢያ፣ ከቦትስዋናና ከደቡብ አፍሪካ ድረስ ሳይቀር በባሕላዊ ሕክምና ፈውስ ለማግኘት ብዙ ሰዎች ወደ እርሷ ይመጡ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ጎጎ ምቱፓ ናንጋ ወይም ጠንቋይ እንዴት መሆን እንደሚቻል ሌሎች ሰዎችን ታስተምር ነበር። አንዳንድ ጊዜ አስማት ትሠራ ነበር!
አንድ እሑድ ጠዋት ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ያገለግሉ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች እቤቷ ይመጣሉ። ምንም ዓይነት ክፉ ተጽእኖ የሌለበት ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በተመለከተ ከእነርሱ ጋር ባደረገችው ውይይት ሙሉ በሙሉ ተደሰተች። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህa የተባለውን መጽሐፍ ተቀበለችና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማች። ገና ሦስት ጊዜ ከማጥናቷ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች።
ጎጎ ምቱፓ ልዩ ኃይል ያገኘችው የይሖዋን ሉዓላዊነት በመቃወም ካመፁት ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ ተገነዘበች። (2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6) በተጨማሪም እነዚህ አጋንንት እያንዳንዱን ሰው ከይሖዋና ከንጹሕ አምልኮ ለማፈናቀል ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን ተረዳች። የምትተዳደረው እነዚህን ክፉ መናፍስታዊ ፍጥረታት በመለማመን ስለነበረ ከዚያ በኋላ ምን ታደርግ ይሆን?
ጎጎ ምቱፓ የጥንቆላ ክታቦቿንና በውርስ ያገኘቻቸውን ቁሳቁሶቿን በጠቅላላ ለማስወገድ እንደምትፈልግ ገለጸች። ይህም ለየት አድርጎ የሚያሳውቃትን ሻሽና “የሚያነጋግራትን የበሬ ቀንድ” የሚጨምር ነበር። ጎጎ ምቱፓ ብቻውን እውነተኛና ሕያው አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማገልገል እንድትችል እንደነዚህ ያሉትን ቁሳቁሶቿን ሁሉ ለማስወገድ ፈለገች።
ሆኖም በገንዘብ ትረዳቸው የነበሩት አንዳንድ የቅርብ ዘመዶቿ ተቃወሟት። እነርሱም ጥቅም ማግኘታቸውን እንዲቀጥሉ ምሥጢራዊ ኃይሏን ጨምሮ የመናፍስት ዕቃዎቿን እንድትሰጣቸው ለመኗት። ጎጎ ምቱፓ ግን ፈጽሞ እምቢ አለች።
አቅራቢያዋ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ባደረገላት እርዳታ በመታገዝ መናፍስታዊ መሣሪያዎቿን በጠቅላላ በሦስት ትልልቅ ሻንጣዎች ውስጥ አጨቀችና አቃጠለቻቸው። ለአጋንንት አምልኮ ትጠቀምባቸው የነበሩት መሣሪያዎቿ በእሳት ሲጋዩ “ተመልከቱ! ቀንዱ ራሱን ማዳን አልቻለም” በማለት ጎጎ ምቱፓ ከፍ ባለ ድምፅ ተናገረች።
በአሁኑ ጊዜ ጎጎ ምቱፓ በደስታ ለይሖዋ ያደረገችውን ውሳኔ በጥምቀት አሳይታለች። ታዲያ አሁን በምን ትተዳደራለች? የጓሮ አትክልቶችን በመሸጥ ነው። አዎን፣ አንድ ሰው የአምላክ ቃል በሚሰጠው ኃይል አማካኝነት ከአጋንንት አምልኮ ሊላቀቅ ይችላል። ጎጎ ምቱፓ “እንደዚህ የመሰለ ነፃነት አግኝቼ አላውቅም” በማለት ትናገራለች።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።