የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 1/15 ገጽ 8-13
  • ‘በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኖኅ ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት ይዞ ተመላልሷል
  • የአብርሃም እምነት
  • ሙሴን ለሥራ ያንቀሳቀሰው እምነት
  • “ልባችሁን አጽኑ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • አብርሃም ማን ነበር?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ይሖዋ “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • አምላክ የአብርሃምን እምነት ፈተነው
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 1/15 ገጽ 8-13

‘በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ’

“በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 5:​7

1. ‘በእምነት መመላለስ’ ማለት ምን ማለት ነው?

በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን መመሪያ ተከትለን ወደ አምላክ ስንጸልይ ቢያንስ ጥቂት እምነት እንዳለን ማሳየታችን ነው። ለሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት መመሥከር መጀመራችንም እምነታችንን የሚያሳይ ነው። ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን ‘በእምነት ለመመላለስ፣’ ማለትም በእምነት የሚመራ ኑሮ ለመኖር ፍላጎት ያለን መሆኑን ማሳየታችን ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 5:​7፤ ቆላስይስ 1:​9, 10

2. አንድ ሰው በጉባኤ እንቅስቃሴዎች መሳተፉ ብቻ እምነት እንዳለው የሚያሳይ ማረጋገጫ ሆኖ ሊቀርብ የማይችለው ለምንድን ነው?

2 በእርግጥ በዚህ መንገድ ለመመላለስ የምንፈልግ ከሆነ ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል። (ዕብራውያን 11:​1, 6) ብዙ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚታየውን ፍቅርና ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ደረጃ ይመለከቱና ከእነርሱ መካከል ለመሆን ይፈልጋሉ። በጣም ጥሩ ጅምር ቢሆንም ይህ ብቻውን ግን እምነት እንዳላቸው አያመለክትም። ሌሎች ደግሞ ጠንካራ እምነት ያለው የትዳር ጓደኛ ወይም ወላጅ ይኖራቸውና ይህ የሚወዱት ሰው በሚያደርጋቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ይካፈሉ ይሆናል። እንዲህ ያለ በጎ ተጽእኖ የሚያሳድር የቤተሰብ አባል ማግኘት ትልቅ በረከት ቢሆንም ይህ እያንዳንዱ ሰው በግሉ ለአምላክ ሊኖረው የሚገባውን ፍቅርና የግል እምነት የሚተካ አይሆንም።​—⁠ሉቃስ 10:​27, 28

3. (ሀ) በጠንካራ መሠረት ላይ የተጣለ እምነት እንዲኖረን ከፈለግን መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት በግላችን ምን ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል? (ለ) አንዳንድ ሰዎች ከሌሎቹ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን በቀላሉ አምነው የሚቀበሉት ለምንድን ነው?

3 በፍጹም ልባቸው በእምነት የሚመላለሱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምነው የተቀበሉ ናቸው። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘በአምላክ መንፈስ የተጻፉ መሆናቸውን’ የሚያረጋግጡ እጅግ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።a (2 ጢሞቴዎስ 3:​16 የ1980 ትርጉም) አንድ ሰው ይህን ነገር አምኖ ለመቀበል ከእነዚህ ማስረጃዎች መካከል ምን ያህሎቹን ማየት ያስፈልገዋል? ይህ ሁኔታ ግለሰቡ ባለው ተሞክሮና እውቀት ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል። አንዱን ሰው ሙሉ በሙሉ የሚያሳምነው ማስረጃ ሌላውን ሰው ላያሳምነው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ሊታበል የማይቻል በርካታ ማስረጃ ቢቀርብለትም ማስረጃው የሚጠቁመውን ነገር ለመቀበል ፈቃደኛ የማይሆን ሰው ይኖራል። ለምን? በልቡ ውስጥ በተቀበረው ስውር ምኞት የተነሣ ነው። (ኤርምያስ 17:​9) በመሆኑም አንድ ሰው ስለ አምላክ ዓላማ ለማወቅ እፈልጋለሁ ቢልም ልቡ በዓለም ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ይጓጓ ይሆናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ደንቦች ጋር የሚጻረረውን አኗኗሩን መተው አይፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለእውነት ልባዊ ጥማት ካለው፣ ለራሱ ሐቀኛ ከሆነና ትህትና ካለው ይዋል ይደር እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ማመኑ አይቀርም።

4. አንድ ሰው እምነት እንዲኖረው ከፈለገ ምን ማድረግ ያስፈልገዋል?

4 ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የሚያስችል እርዳታ ያገኙ ሰዎች በጥቂት ወራት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ለማመን የሚያስችል በቂ ማስረጃ እንዳለ ይገነዘባሉ። ይህ ነገር ከይሖዋ ለመማር ልባቸውን እንዲከፍቱ የሚያነሳሳቸው ከሆነ ውስጣዊ አስተሳሰባቸው፣ ፍላጎታቸውና የልባቸው ዝንባሌ በሚማሩት ነገር ቀስ በቀስ ይቀረጻል። (መዝሙር 143:​10) ሮሜ 10:​10 ሰው የሚያምነው “በልቡ” እንደሆነ ይናገራል። እንዲህ ያለው እምነት የግለሰቡን ውስጣዊ ስሜት የሚያንጸባርቅ ከመሆኑም ሌላ በአኗኗሩ ገሐድ ሆኖ ይታያል።

ኖኅ ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት ይዞ ተመላልሷል

5, 6. የኖኅ እምነት በምን ላይ የተመሠረተ ነበር?

5 ኖኅ በጠንካራ መሠረት ላይ የተጣለ እምነት የነበረው ሰው ነው። (ዕብራውያን 11:​7) ኖኅ እንዲህ ዓይነት እምነት እንዲኖረው ያስቻለው ምን ነበር? ኖኅ የተቀበለው የአምላክ ቃል በጽሑፍ የሠፈረ ሳይሆን በቃል የተነገረ ነበር። ዘፍጥረት 6:​13 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ኖኅን አለው:- የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ይሖዋ መርከብ እንዲሠራ ካዘዘው በኋላ ስለ አሠራሩ ዝርዝር መመሪያ ሰጠው። ከዚያም አምላክ እንዲህ ሲል አክሎ ተናገረ:- “እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፣ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል።”​—⁠ዘፍጥረት 6:​14-17

6 ከዚያ በፊት ዝናብ ዘንቦ ያውቅ ነበርን? መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ዘፍጥረት 2:​5 “እግዚአብሔር አምላክ በምድር ላይ አላዘነበም ነበር” ይላል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የሰፈረው ሐሳብ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ የኖረው ሙሴ ስለ ኖኅ ዘመን ሳይሆን ከዚያ በፊት ስለነበረ ጊዜ ሲናገር የሰጠው መግለጫ ነው። ዘፍጥረት 7:​4 እንደሚያመለክተው ይሖዋ ለኖኅ በተናገረበት ጊዜ ዝናብ እንደሚመጣ ጠቅሷል። ኖኅም ይሖዋ ይህን ሲናገር ምን ማለቱ እንደነበረ እንደገባው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ቢሆንም የኖኅ እምነት የተመሠረተው ሊያያቸው በሚችላቸው ነገሮች ላይ አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ኖኅ “ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ” ነበር። አምላክ በምድር ላይ “የጥፋት ውኃ” ወይም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ በዘፍጥረት 6:​17 ላይ እንደሚለው “የሰማይን ውቅያኖስ” እንደሚያወርድ ለኖኅ ነግሮት ነበር። እስከዚያ ዘመን ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ሆኖ አያውቅም ነበር። ቢሆንም ኖኅ፣ የሚመለከታቸው የፍጥረት ሥራዎች በሙሉ አምላክ በእርግጥ እንዲህ ያለ አጥፊ ጎርፍ ሊያመጣ እንደሚችል የሚያስረዱ ግልጽ ምሥክሮች ነበሩ። ኖኅ በእምነት ተገፋፍቶ መርከብ ሠራ።

7. (ሀ) ኖኅ አምላክ ያዘዘውን ነገር ለመፈጸም ምን ማድረግ አላስፈለገውም? (ለ) የኖኅን እምነት በመመርመራችን የተጠቀምነው እንዴት ነው? የእኛስ እምነት ለሌሎች በረከት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

7 አምላክ የጥፋቱ ውኃ የሚጀምርበትን ጊዜ ለኖኅ አልነገረውም ነበር። ቢሆንም ኖኅ በዚህ አመካኝቶ ለስብከቱና ለመርከቡ ሥራ ሁለተኛ ቦታ በመስጠት ቸልተኛ አልሆነም። አምላክም ኖኅ ወደ መርከብ መቼ መግባት እንደሚኖርበት ከነገረው በኋላ በቂ ጊዜ ሰጥቶታል። እስከዚያ ጊዜ ግን ኖኅ “እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ” ማድረጉን ቀጥሎ ነበር። (ዘፍጥረት 6:​22) ኖኅ በማየት ሳይሆን በእምነት ተመላልሷል። ይህን በማድረጉ ከፍተኛ ውለታ ውሎልናል! ዛሬ በሕይወት ልንኖር የቻልነው እርሱ ባሳየው እምነት ምክንያት ነው። በእኛም ሁኔታ ቢሆን የምናሳየው እምነት በራሳችን የወደፊት ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በልጆቻችንና በአካባቢያችን በሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ላይ ጭምር ወሳኝ ውጤት ሊኖረው ይችላል።

የአብርሃም እምነት

8, 9. (ሀ) አብርሃም እምነቱን በምን መሠረት ላይ ጥሎ ነበር? (ለ) ይሖዋ ለአብርሃም ‘የተገለጠለት’ በምን መንገድ ነው?

8 የአብርሃምን ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። (ዕብራውያን 11:​8-10) የአብርሃም እምነት የተመሠረተው በምን ላይ ነበር? አብርሃም ባደገበት በከለዳውያን ኡር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ጣዖት አምላኪዎችና ፍቅረ ነዋይ የተጠናወታቸው ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ አብርሃም የተስተካከለ አመለካከት እንዲኖረው የረዱት ሌሎች ነገሮች ነበሩ። አብርሃም ከእርሱ መወለድም በኋላ 150 ለሚያክሉ ዓመታት በሕይወት ከቆየው ከኖኅ ልጅ ከሴም ጋር ሊገናኝ ይችል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። አብርሃም፣ ይሖዋ ‘ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል አምላክ’ እንደሆነ ሙሉ እምነት አድሮበት ነበር።​— ዘፍጥረት 14:​22 የ1980 ትርጉም

9 በአብርሃም አመለካከት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለ ሌላም ምክንያት ነበር። ይሖዋ ‘ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታይቶ ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና’ ብሎት ነበር። (ሥራ 7:​2, 3) ይሖዋ ለአብርሃም ‘የታየው’ በምን መንገድ ነበር? አብርሃም አምላክን በገሐድ አላየውም። (ዘጸአት 33:​20) ይሁን እንጂ ይሖዋ ለአብርሃም በሕልም፣ ክብሩን በሚያሳይ አንድ ዓይነት ታላቅ ክስተት ወይም ደግሞ በመላእክት አማካኝነት ተገልጦለት ሊሆን ይችላል። (ከዘፍጥረት 18:​1-3፤ 28:​10-15፤ ዘሌዋውያን 9:​4, 6, 23, 24 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ለአብርሃም የተገለጠለት በምንም መንገድ ይሁን በምን ይህ የታመነ ሰው አምላክ ውድ የሆነ መብት ከፊቱ ዘርግቶለት እንደነበረ አውቋል። አብርሃምም በእምነት ምላሽ ሰጥቷል።

10. ይሖዋ የአብርሃምን እምነት ያጸናለት እንዴት ነው?

10 የአብርሃም እምነት አምላክ ስለሚሰጠው ምድር ዝርዝር ማብራሪያ በማግኘት ላይ የተመካ አልነበረም። ይህ ምድር መቼ እንደሚሰጠው በማወቁም ላይ የተመካ አልነበረም። እምነት ያሳየው ይሖዋ ሁሉን የሚችል አምላክ መሆኑን ስላወቀ ነው። (ዘጸአት 6:​3) አብርሃም ልጆች እንደሚኖሩት ይሖዋ ነግሮት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ እንዴት እንደሚፈጸም ግራ የተጋባባቸው ጊዜያት ነበሩ። ዕድሜው እየገፋ ሄዶ ነበር። (ዘፍጥረት 15:​3, 4) አብርሃም የሰማይን ከዋክብት እንዲመለከትና መቁጠር ይችል እንደሆነ እንዲቆጥራቸው በመጠየቅ ይሖዋ እምነቱን አጠንክሮለታል። ከዚያም አምላክ “ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” አለው። አብርሃም በእጅጉ ተነካ። የእነዚህ አስደናቂ የሆኑ የጠፈር አካላት ፈጣሪ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ግልጽ ነበር። አብርሃም ‘በይሖዋ አመነ።’ (ዘፍጥረት 15:​5, 6) አብርሃም ያመነው እንዲሁ የሰማው ነገር ስላስደሰተው አልነበረም። ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት ነበረው።

11. (ሀ) አብርሃም ዕድሜው ወደ 100 ዓመት እየተጠጋ ሲመጣ ባልቴቷ ሣራ ልጅ ትወልድልሃለች ሲል አምላክ ለገባለት ቃል ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) አብርሃም ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሞሪያ ተራራ የመውሰዱን ፈተና የተወጣው በምን ዓይነት እምነት ነበር?

11 አብርሃም ወደ 100 ዓመት ሚስቱ ሣራ ደግሞ ወደ 90 ዓመት ዕድሜ በተጠጉ ጊዜ ይሖዋ የገባውን ቃል በመድገም ከሣራ ወንድ ልጅ እንደሚወልድ ነገረው። አብርሃም ሁለቱም የነበሩበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነበር። “ለእግዚአብሔር ክብር እየሰጠ፣ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፣ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።” (ሮሜ 4:​19-21) አብርሃም አምላክ ‘የሰጠው ተስፋ’ ሳይፈጸም እንደማይቀር ያውቅ ነበር። አብርሃም እምነት ስለነበረው ከጊዜ በኋላ አምላክ ልጁን ይስሐቅን ወደ ሞሪያ ተራራ ወስዶ እንዲሠዋለት ሲጠይቀው ታዛዥ ሆኖ ተገኝቷል። (ዘፍጥረት 22:​1-12) ይህ ልጅ በተአምር እንዲወለድ ያደረገው አምላክ ከዚሁ ልጅ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የተናገረውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ሲል ወደ ሕይወት ሊመልሰው እንደሚችል ሙሉ ትምክህት ነበረው።​— ዕብራውያን 11:​17-19

12. አብርሃም በእምነት መመላለሱን የቀጠለው ለምን ያህል ጊዜ ነበር? እርሱንም ሆነ ጠንካራ እምነት ያሳዩትን የቤተሰቡን አባላት ምን ሽልማት ይጠብቃቸዋል?

12 አብርሃም በእምነት የተገራ ሰው መሆኑን ያሳየው በአንዳንድ የተለዩ ወቅቶች ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ነው። በሕይወት ዘመኑ ከተስፋይቱ ምድር ቅንጣት መሬት እንኳን አልወረሰም። (ሥራ 7:​5) ቢሆንም አብርሃም ተሰላችቶ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ኡር አልተመለሰም። እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ 100 ዓመት ለሚያክል ጊዜ አምላክ በመራው ምድር በድንኳን ውስጥ ኖሯል። (ዘፍጥረት 25:​7) ዕብራውያን 11:​16 ስለ አብርሃምና ስለ ሚስቱ ስለ ሣራ፣ ስለ ልጃቸው ስለ ይስሐቅና ስለ ልጅ ልጃቸው ስለ ያዕቆብ ሲናገር “ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፣ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና” ይላል። አዎን፣ በመሲሐዊው መንግሥቱ ምድራዊ ግዛት ቦታ አዘጋጅቶላቸዋል።

13. ዛሬ ከይሖዋ አገልጋዮች መካከል እንደ አብርሃም ያለ እምነት የሚያሳዩት እነማን ናቸው?

13 ዛሬም በይሖዋ አገልጋዮች መካከል እንደ አብርሃም ያሉ ሰዎች ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ለበርካታ ዓመታት በእምነት ተመላልሰዋል። አምላክ በሚሰጠው ኃይልና ብርታት እንደ ተራራ ያሉ እንቅፋቶችን ተወጥተዋል። (ማቴዎስ 17:​20) አምላክ ቃል የገባላቸውን ውርሻ የሚሰጣቸው መቼ እንደሆነ ስለማያውቁ ብቻ በእምነታቸው አይወላውሉም። የይሖዋ ቃል ሳይፈጸም እንደማይቀር ያውቃሉ። ከእርሱ ምሥክሮች መካከል መቆጠራቸውን በዋጋ ሊተመን እንደማይችል ታላቅ መብት ይቆጥራሉ። እናንተስ እንደዚህ ይሰማችኋልን?

ሙሴን ለሥራ ያንቀሳቀሰው እምነት

14. ለሙሴ እምነት መሠረት የሆነው ነገር የተጣለው እንዴት ነበር?

14 ሌላው የእምነት ምሳሌ ደግሞ ሙሴ ነው። ሙሴ እምነት ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? የእምነቱ መሠረት የተጣለው ገና በሕፃንነቱ ነበር። የፈርዖን ሴት ልጅ ሙሴን በናይል ወንዝ ከደንገል በተሠራ ቅርጫት ውስጥ አግኝታ ብትወስደውና ልጅዋ ብታደርገውም እያጠባች ያሳደገችውና በጨቅላ ዕድሜው የተንከባከበችው ዮካቤድ የተባለችው ዕብራዊት እናቱ ነበረች። ዮካቤድ በደንብ እንዳስተማረችውና ለይሖዋ ፍቅር ኮትኩቶና ለአብርሃም በሰጠው ተስፋ ላይም አድናቆት ኖሮት እንዲያድግ እንዳደረገች ግልጽ ነው። ባደገ ጊዜም በፈርዖን ቤት ‘ሆኖ የግብጻውያንን ጥበብ በሙሉ’ ተምሯል። (ሥራ 7:​20-22፤ ዘጸአት 2:⁠1-10፤ 6:​20፤ ዕብራውያን 11:​23) ሙሴ በጣም በተመቻቸ ኑሮ ይኖር የነበረ ቢሆንም ልቡ በባርነት ሥር ከነበሩት የአምላክ ሕዝቦች አልራቀም።

15. ሙሴ ራሱን ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ማስመደቡ ምን ይጠይቅበት ነበር?

15 አርባ ዓመት በሞላው ጊዜ ግፍ የሚፈጸምበትን አንድ እስራኤላዊ ለማዳን ሲል አንድን ግብጻዊ መትቶ ገደለ። ይህ ድርጊት ሙሴ ለአምላክ ሕዝቦች ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ያሳየ አጋጣሚ ነበር። በእርግጥም “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ” ብሏል። የግብጽ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ሆኖ ‘ለጊዜው በኃጢአት ከሚያገኘው ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ’ መከራ ይቀበሉ ከነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ጋር ለመቆጠር በእምነት ተገፋፋ።​— ዕብራውያን 11:​24, 25፤ ሥራ 7:​23-25

16. (ሀ) ይሖዋ ለሙሴ ምን ተልእኮ ሰጠው? አምላክስ የረዳው እንዴት ነው? (ለ) ሙሴ የተሰጠውን ተልእኮ ሲፈጽም እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

16 ሙሴ ለሕዝቦቹ እፎይታ ለማምጣት በጣም ጓጉቶ ነበር። አምላክ የቀጠረው ነጻ የሚወጡበት ጊዜ ግን ገና አልደረሰም። በመሆኑም ከግብጽ ለመሸሽ ተገደደ። ሙሴ ወደ ግብጽ ተመልሶ እስራኤላውያንን እየመራ ከዚያች ምድር ነጻ እንዲያወጣ አምላክ በአንድ መልአክ አማካኝነት የሾመው ከ40 ዓመታት በኋላ ነበር። (ዘጸአት 3:​2-10) በዚህ ጊዜ ሙሴ እንዴት ተሰማው? ይሖዋ እስራኤላውያንን ነጻ ለማውጣት እንደሚችል ባይጠራጠርም አምላክ በፊቱ ላዘጋጀለት ሥራ ብቁ እንዳልሆነ ተሰማው። ይሖዋም በፍቅር ሙሴ ያስፈልገው የነበረውን ማበረታቻ ሰጠው። (ዘጸአት 3:​11–4:​17) የሙሴ እምነት ጠነከረ። ወደ ግብጽም ተመልሶ ይሖዋን ያመልኩ ዘንድ እስራኤላውያንን ባይለቅ በምድሪቱ ላይ መቅሰፍት እንደሚወርድ ፈርዖንን በተደጋጋሚ ጊዜያት ፊት ለፊት አስጠነቀቀው። ሙሴ እነዚህን መቅሰፍቶች ለማምጣት የሚያስችል አንዳች ኃይል አልነበረውም። በማየት ሳይሆን በእምነት ተመላልሷል። በይሖዋና በቃሉ ሙሉ እምነት ነበረው። ፈርዖን በሙሴ ላይ ዛተ። ሙሴ ግን ይህን ሁሉ ተቋቁሟል። “የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።” (ዕብራውያን 11:​27) ሙሴ ፍጹም ሰው አልነበረም። ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዘኁልቁ 20:​7-12) ይሁን እንጂ በአምላክ ከተሾመ በኋላ መላ ሕይወቱ ይመራ የነበረው በእምነት ነበር።

17. ኖኅ፣ አብርሃምና ሙሴ የአምላክን አዲስ ዓለም በዓይናቸው ለማየት ባይበቁም በእምነት መመላለሳቸው ምን አስገኝቶላቸዋል?

17 የእናንተም እምነት እንደ ኖኅ፣ እንደ አብርሃምና እንደ ሙሴ ያለ ይሁን። እነርሱ በዘመናቸው የአምላክን አዲስ ዓለም እንዳላዩ አይካድም። (ዕብራውያን 11:​39) አምላክ የቀጠረው ጊዜ አልደረሰም ነበር። ገና መፈጸም የነበረባቸው ከአምላክ ዓላማ ጋር የተያያዙ ሌሎች ነገሮች ነበሩ። ይሁን እንጂ በአምላክ ቃል ላይ የነበራቸው እምነት አልተናወጠም። በዚህ ምክንያት ስማቸው በአምላክ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቧል።

18. ለሰማያዊ ሕይወት የተጠሩት ሰዎች በእምነት መመላለሳቸው አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

18 ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ “ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና” ብሏል። አምላክ፣ እንደ ጳውሎስ ላሉት ከክርስቶስ ጋር ሰማያዊ ሕይወት ለማግኘት ለተጠሩ ሰዎች የሚበልጥን ነገር ተመልክቶ ነበር ማለት ነው። (ዕብራውያን 11:​40) ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 5:​7 ላይ “በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም” ሲል የጻፈው በተለይ እንዲህ ያሉትን ሰዎች በአእምሮው በመያዝ ነበር። ይህ ቃል በተጻፈበት ጊዜ አንዳቸውም ቢሆኑ ሰማያዊ ሽልማታቸውን አላገኙም። በሰብዓዊ ዓይናቸው ሊያዩት ባይችሉም ሽልማታቸውን በተመለከተ የነበራቸው እምነት ግን በጠንካራ መሠረት ላይ የተጣለ ነበር። የሰማያዊ ሕይወት ሽልማት የሚያገኙት ሁሉ በኩራት የሆነው ክርስቶስ ከሙታን ተነስቷል። ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊትም ከ500 የሚበልጡ ምሥክሮች ተመልክተውታል። (1 ቆሮንቶስ 15:​3-8) መላ ሕይወታቸው በዚህ እምነት እንዲመራ የሚያደርጉበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። እኛም ብንሆን በእምነት እንድንመላለስ የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለን።

19. በዕብራውያን 1:​1, 2 ላይ እንደተገለጸው አምላክ ለእኛ የተናገረን በማን በኩል ነው?

19 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሚናገረው ሙሴን በሚነድድ ቁጥቋጦ ውስጥ እንዳነጋገረው በመልአክ አማካኝነት አይደለም። አምላክ በገዛ ልጁ በኩል ተናግሮናል። (ዕብራውያን 1:​1, 2) አምላክ በኢየሱስ በኩል የተናገረው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገብ ከማድረጉም በላይ በምድር ዙሪያ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች እንዲተረጎም አድርጓል።

20. የእኛ ሁኔታ ከኖኅ፣ ከአብርሃምና ከሙሴ እጅግ የላቀ የሆነው እንዴት ነው?

20 ከኖኅ፣ ከአብርሃምና ከሙሴ እጅግ የሚበልጥ ነገር አግኝተናል። የተሟላው የአምላክ ቃል አለን። ከዚህም ውስጥ አብዛኛው ፍጻሜውን አግኝቷል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የደረሰባቸውን ማንኛውም ዓይነት ፈተና ተቋቁመው ለይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች ስለሆኑ ወንዶችና ሴቶች ከሚናገረው ነገር አንፃር ዕብራውያን 12:​1 እንዲህ በማለት ይመክራል:- “እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።” እምነት በግድየለሽነት ሊታይ የሚገባው ነገር አይደለም። “ቶሎም የሚከበን ኃጢአት” የተባለው የእምነት ማጣት ነው። በእምነት መመላለሳችንን ለመቀጠል ከፈለግን ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ያስፈልገናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ​—⁠የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ‘በእምነት መመላለስ’ ምን ይጠይቃል?

◻ ኖኅ እምነት ካሳየበት ሁኔታ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

◻ አብርሃም እምነት ያሳየበት መንገድ እኛን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴን የእምነት ምሳሌ አድርጎ የሚጠቅሰው ለምንድን ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም በእምነት ተመላልሷል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙሴና አሮን ፈርዖን ፊት በቀረቡ ጊዜ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ