የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 1/1 ገጽ 11-20
  • “ልባችሁን አጽኑ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ልባችሁን አጽኑ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአብርሃም የእምነት ምሳሌ
  • አምላክን መስማት
  • ከአምላክ ጋር መነጋገር
  • በዛሬው ጊዜ የታየ እምነት
  • በዛሬው ጊዜ እምነት አዳብሩ
  • በቅርቡ ፍጻሜውን የሚያገኝ ተስፋ
  • ይሖዋ “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • የአብርሃም ዓይነት እምነት አላችሁን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • አብርሃም ማን ነበር?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ‘በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 1/1 ገጽ 11-20

“ልባችሁን አጽኑ”

“የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል።”​—⁠ዕብራውያን 10:​36

1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርከት ያሉ ክርስቲያኖች ምን ሁኔታ ገጥሟቸዋል? (ለ) እምነት በቀላሉ ሊደክም የሚችለው ለምንድን ነው?

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል የሐዋርያው ጳውሎስን ያህል እምነትን ደጋግሞ የጠቀሰ የለም። በተጨማሪም እምነታቸው ስለተዳከመባቸው ወይም ስለሞተባቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ “መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ፣ በእምነት ነገር ጠፍተዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 1:​19, 20) ዴማስ “የአሁኑን ዓለም ወዶ” ጳውሎስን ትቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​10) አንዳንዶች ኃላፊነት በጎደለው ክርስቲያናዊ ያልሆነ ተግባራቸው ‘እምነትን ክደዋል።’ ሌሎች ደግሞ በውሸት ጥበብ ተታልለው ‘ከእምነት ስተው ወጥተዋል።’​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​8፤ 6:​20, 21

2 እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በእነዚህ መንገዶች የወደቁት ለምንድን ነው? “እምነትም ተስፋ ስለ ምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” (ዕብራውያን 11:​1) እምነት የምናሳድረው በማናየው ነገር ላይ ነው። የሚታዩ ነገሮች እምነት የሚጠይቁ አይደሉም። ለማይታይ መንፈሳዊ ሀብት ከመድከም ይልቅ ለሚታይ ብልጽግና መሥራት ይቀላል። (ማቴዎስ 19:​21, 22) እንደ “ሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት” ያሉ ብዙ የሚታዩ ነገሮች ፍጽምና የጎደለውን ሥጋችንን በእጅጉ የሚማርኩት ከመሆኑም በላይ እምነታችንን ሊያዳክሙት ይችላሉ።​—⁠1 ዮሐንስ 2:​16

3. አንድ ክርስቲያን ምን ዓይነት እምነት ማዳበር ይኖርበታል?

3 ሆኖም ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል” ብሏል። ሙሴ እንዲህ ዓይነት እምነት ነበረው። ‘ብድራቱን ትኩር ብሎ ከመመልከቱም’ በላይ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአል።” (ዕብራውያን 11:​6, 24, 26, 27) አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነት እምነት ያስፈልገዋል። ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው አብርሃም በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው።

የአብርሃም የእምነት ምሳሌ

4. አብርሃም የነበረው እምነት ሕይወቱን የነካው እንዴት ነው?

4 አብርሃም ለአሕዛብ ሁሉ በረከት የሚሆን የአንድ ዘር አባት እንደሚሆን አምላክ ቃል የገባለት በኡር ሳለ ነበር። (ዘፍጥረት 12:​1–3፤ ሥራ 7:​2, 3) አብርሃም ይህን ተስፋ መሠረት አድርጎ ይሖዋን በመታዘዝ መጀመሪያ ወደ ካራን ከዚያም ወደ ከነዓን ሄዷል። ወደ ከነዓን ከሄደ በኋላ ይሖዋ ምድሪቱን ለአብርሃም ዘር እንደሚሰጥ ቃል ገባ። (ዘፍጥረት 12:​7፤ ነህምያ 9:​7, 8) ይሁን እንጂ ይሖዋ ቃል ከገባለት ነገር መካከል አብዛኛው የሚፈጸመው ከእሱ ሞት በኋላ ነበር። ለምሳሌ ያህል አብርሃም ራሱ ለመቃብር ቦታነት ከገዛው ከማክጴላ ዋሻ በስተቀር በከነዓን ምድር የራሱ የሆነ ቦታ አልነበረውም። (ዘፍጥረት 23:​1–20) ያም ሆኖ ግን በይሖዋ ቃል ላይ እምነት ነበረው። ከሁሉም በላይ ደግሞ “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ” በእምነት ይጠባበቅ ነበር። (ዕብራውያን 11:​10) እንዲህ ዓይነቱ እምነት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ጠብቆታል።

5, 6. የአብርሃም እምነት ይሖዋ ከገባለት ቃል ጋር በተያያዘ ሁኔታ የተፈተነው በምን መንገድ ነው?

5 ይህ ሁኔታ በተለይ የአብርሃም ዘር ታላቅ ሕዝብ ይሆናል ከሚለው ተስፋ ጋር በተያያዘ በግልጽ ታይቷል። ይህ ተስፋ እንዲፈጸም አብርሃም ልጅ ያስፈልገው ነበር። አንድ ልጅ ለመውለድ ረጅም ጊዜ ጠብቋል። አምላክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃል ሲገባለት አብርሃም ስንት ዓመቱ እንደነበረ አናውቅም፤ ሆኖም ረጅም መንገድ ተጉዞ ወደ ካራን ሲሄድ ይሖዋ ገና ልጅ አልሰጠውም ነበር። (ዘፍጥረት 11:​30) አብርሃም በካራን ብዙ ‘ሀብትና አገልጋዮች ያገኘ’ በመሆኑ ረዘም ላለ ጊዜ ተቀምጦ ነበር ማለት ነው፤ ወደ ከነዓን ሲሄድ ደግሞ እሱ 75 ዓመት ሞልቶት የነበረ ሲሆን ሣራ ደግሞ 65 ዓመት ሆኗት ነበር። በዚያን ጊዜም ቢሆን ልጅ አልወለዱም። (ዘፍጥረት 12:​4, 5 የ1980 ትርጉም) ሣራ በ70ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ስትደርስ ከዚያ በኋላ ለአብርሃም ልጅ ልትወልድለት እንደማትችል አድርጋ ደመደመች። በመሆኑም በዘመኑ የነበረውን ልማድ በመከተል ባሪያዋን አጋርን ለአብርሃም ሰጠችውና ከእሷ ልጅ ወለደ። ሆኖም ቃል የተገባለት ልጅ ይህ አልነበረም። ውሎ አድሮ አጋርና ልጅዋ እስማኤል ከቤት እንዲወጡ ተደረገ። ያም ሆኖ ግን አብርሃም ስለ እነሱ በመጸለዩ ይሖዋ እስማኤልን እንደሚባርከው ቃል ገብቶለታል።​—⁠ዘፍጥረት 16:​1–4, 10፤ 17:​15, 16, 18–20፤ 21:​8–21

6 አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ መጀመሪያ ቃል ከተገባላቸው ከብዙ ጊዜ በኋላ የ100 ዓመቱ አብርሃምና የ90 ዓመቷ ሣራ ይስሐቅ የተባለ ወንድ ልጅ ወለዱ። ምንኛ ተደስተው ይሆን! እነዚህ በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት “ምውት” የነበረው አካላቸው አዲስ ሕይወት ማፍራቱ እንደ ትንሣኤ የሚቆጠር ነበር። (ሮሜ 4:​19–21) ለረጅም ጊዜ ጠብቀዋል፤ ሆኖም የተገባው ቃል በመጨረሻ ሲፈጸም ተክሰዋል።

7. እምነት ከጽናት ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

7 የአብርሃም ምሳሌ እምነት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ መሆን እንደሌለበት ያሳስበናል። ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ እምነትን ከጽናት ጋር አያይዞ ገልጾታል:- “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። . . . እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።” (ዕብራውያን 10:​36–39) ብዙዎች የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ለረጅም ጊዜ ተጠባብቀዋል። አንዳንዶች በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ሲጠባበቁ ኖረዋል። ጠንካራ እምነታቸው ጠብቆ አቆይቷቸዋል። ልክ እንደ አብርሃም እነሱም ሽልማቱን ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ይቀበላሉ።​—⁠ዕንባቆም 2:​3

አምላክን መስማት

8. በዛሬው ጊዜ አምላክን የምንሰማው እንዴት ነው? ይህ እምነታችንን የሚያጠነክረውስ ለምንድን ነው?

8 ቢያንስ ቢያንስ አራት ነገሮች የአብርሃምን እምነት አጠንክረውታል፤ እነዚሁ ነገሮች እኛንም ሊረዱን ይችላሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ የተናገረውን በመከተል ‘አምላክ እንዳለ የሚያምን’ መሆኑን አሳይቷል። በመሆኑም በይሖዋ ቢያምኑም እንኳ በቃሉ እምነት ካልነበራቸው በኤርምያስ ዘመን የነበሩ አይሁዶች የተለየ ነበር። (ኤርምያስ 44:​15–19) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ‘በልባችሁ በጨለማ ስፍራ እንደሚበራ መብራት ነው’ ሲል ጴጥሮስ በገለጸው በመንፈስ አነሳሽነት ባስጻፈው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያነጋግረናል። (2 ጴጥሮስ 1:​19) መጽሐፍ ቅዱስን በጥሞና ስናነብ ‘የእምነትን ቃል እንመገባለን።’ (1 ጢሞቴዎስ 4:​6፤ ሮሜ 10:​17) በተጨማሪም በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች “ታማኝና ልባም ባሪያ” የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሥራ ላይ በማዋልና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በመረዳት ረገድ መመሪያ የሚሆነንን መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ ይሰጠናል። (ማቴዎስ 24:​45–47) እምነታችን ጠንካራ እንዲሆን ከፈለግን በእነዚህ መንገዶች ይሖዋን መስማት ይኖርብናል።

9. በክርስቲያናዊው ተስፋ ከልብ ማመናችን ምን ውጤት አለው?

9 የአብርሃም እምነት ከተስፋው ጋር በጣም የተቆራኘ ነበር። “የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ።” (ሮሜ 4:​18) ሊረዳን የሚችለው ሁለተኛው ነገር ይህ ነው። ይሖዋ ‘አጥብቀው ለሚፈልጉት ዋጋ እንደሚሰጥ’ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ እንደክማለንና’ ሲል ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​10) በክርስቲያናዊው ተስፋ ከልባችን የምናምን ከሆነ ልክ እንደ አብርሃም መላ አኗኗራችን እምነታችንን የሚያሳይ ይሆናል።

ከአምላክ ጋር መነጋገር

10. እምነታችንን የሚያጠነክረው ምን ዓይነት ጸሎት ነው?

10 አብርሃም ከአምላክ ጋር ይነጋገር ነበር፤ እምነቱን ያጠነከረለት ሦስተኛው ነገር ይህ ነበር። ዛሬ እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘውን የጸሎት ስጦታ በመጠቀም ከይሖዋ ጋር መነጋገር እንችላለን። (ዮሐንስ 14:​6፤ ኤፌሶን 6:​18) ኢየሱስ “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” የሚለውን ጥያቄ ያቀረበው ዘወትር የመጸለይን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ነው። (ሉቃስ 18:​8) እምነት የሚገነባ ጸሎት ምንም ሳይታሰብበት እንዲሁ በደመ ነፍስ የሚቀርብ አይደለም። ጥልቅ ትርጉም ያለው ነው። ለምሳሌ ያህል ከባድ ውሳኔዎች ከፊታችን በሚደቀኑበት ጊዜ ወይም ከባድ ውጥረት ውስጥ ስንገባ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባችን በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠ሉቃስ 6:​12, 13፤ 22:​41–44

11. (ሀ) አብርሃም ልቡን ለአምላክ በመክፈቱ ብርታት ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ከአብርሃም ተሞክሮ ምን ልንማር እንችላለን?

11 አብርሃም ይሖዋ የተስፋውን ዘር ሳይሰጠው ዕድሜው እየገፋ በመሄዱ የተሰማውን ጭንቀት ለአምላክ አካፍሎት ነበር። ይሖዋ አጽናናው። ውጤቱስ ምን ነበር? አብርሃም “በእግዚአብሔር አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት።” ከዚያም ይሖዋ ምልክት በመስጠት የተናገራቸው የሚያጽናኑ ቃላት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ አረጋገጠለት። (ዘፍጥረት 15:​1–18) በጸሎት ልባችንን ለይሖዋ ብንከፍትለት፣ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚሰጠውን ማጽናኛ ብንቀበልና በሙሉ እምነት ብንታዘዘው ይሖዋም በምላሹ እምነታችንን ያጠነክርልናል።​—⁠ማቴዎስ 21:​22፤ ይሁዳ 20, 21

12, 13. (ሀ) አብርሃም የይሖዋን መመሪያ በተከተለ ጊዜ የተባረከው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹ ተሞክሮዎች እምነታችንን ሊያጠነክሩት ይችላሉ?

12 የአብርሃምን እምነት ያጠነከረው አራተኛ ነገር አብርሃም የአምላክን መመሪያ በተከተለ ጊዜ ይሖዋ የሰጠው ድጋፍ ነበር። አብርሃም ሎጥን ከወራሪዎቹ ነገሥታት ለማስጣል በሄደበት ጊዜ ይሖዋ ድል እንዲጎናጸፍ አድርጎታል። (ዘፍጥረት 14:​16, 20) አብርሃም ዘሩ በሚወርሰው ምድር ላይ እንደ እንግዳ ሆኖ በኖረበት ጊዜ ይሖዋ በቁሳዊ ነገሮች ባርኮታል። (ከዘፍጥረት 14:​21–23 ጋር አወዳድር።) የአብርሃም መጋቢ ለይስሐቅ የምትስማማውን ሚስት ለማግኘት ያደረገውን ጥረት ይሖዋ አሳክቶለታል። (ዘፍጥረት 24:​10–27) አዎን፣ ይሖዋ ‘አብርሃምን በሁሉ ባርኮታል።’ (ዘፍጥረት 24:​1) በዚህም የተነሳ እምነቱ በጣም ከመጠንከሩም በላይ ከይሖዋ አምላክ ጋር በጣም የተቀራረበ ዝምድና ሊኖረው በመቻሉ ይሖዋ “ወዳጄ” ብሎ ጠርቶታል።​—⁠ኢሳይያስ 41:​8፤ ያዕቆብ 2:​23

13 ዛሬ እኛ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይችላልን? አዎን። ልክ እንደ አብርሃም ትእዛዛቱን በማክበር ይሖዋን ብንፈትነው እኛንም ይባርከናል፤ ይህ ደግሞ እምነታችንን ያጠነክረዋል። ለምሳሌ ያህል የ1998 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርትን በጥቂቱ ብንመለከት ብዙዎች ይሖዋ ምሥራቹን እንዲሰብኩ የሰጠውን ትእዛዝ በማክበራቸው በእጅጉ እንደተባረኩ መረዳት እንችላለን።​—⁠ማርቆስ 13:​10

በዛሬው ጊዜ የታየ እምነት

14. ይሖዋ በመንግሥት ዜና ቁጥር 35 የተካሄደውን ዘመቻ የባረከው እንዴት ነው?

14 በሚልዮን የሚቆጠሩ ምሥክሮች በቅንዓትና በጋለ መንፈስ በመሥራታቸው በጥቅምት 1997 በዓለም ዙሪያ የተካሄደው የመንግሥት ዜና ቁጥር 35 ዘመቻ በጣም ስኬታማ ሊሆን ችሏል። በጋና የተከናወነው ሁኔታ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል። በአራት ቋንቋዎች 2.5 ሚልዮን የሚሆኑ ቅጂዎች የተሰራጩ ሲሆን በውጤቱም 2,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው ጥያቄ አቅርበዋል። በቆጵሮስ ሁለት ምሥክሮች የመንግሥት ዜና እያሰራጩ እያለ አንድ ቄስ ሲከተላቸው ተመለከቱ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለእሱም አንድ የመንግሥት ዜና ቅጂ ሊሰጡት ሲሉ ቅጂውን ቀደም ሲል የወሰደ መሆኑን ከገለጸላቸው በኋላ “ትራክቱ ልዩ መልእክት የያዘ በመሆኑ ትራክቱን ያዘጋጁትን ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ” አላቸው። በዴንማርክ 1.5 ሚልዮን የመንግሥት ዜና ቅጂዎች የተሰራጩ ሲሆን ጥሩ ውጤቶችም ተገኝተዋል። በዚሁ አገር በሕዝብ ግንኙነት ውስጥ የምትሠራ አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ትራክቱ ለሁሉም ሰው የሚሆን መልእክት ያዘለ ነው። ለመረዳት የማያስቸግር ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ለማወቅ የሚያነሳሳና ፍላጎት የሚቀሰቅስ ነው። በእርግጥም ዒላማውን መትቷል!”

15. በማንኛውም ስፍራ የሚገኙ ሰዎችን ለማነጋገር የተደረገውን ጥረት ይሖዋ እንደባረከው የሚያሳዩት የትኞቹ ተሞክሮዎች ናቸው?

15 በ1998 በቤታቸው ላሉ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሥፍራ ለሚገኙ ሰዎች ለመስበክ ጥረት ተደርጓል። በኮትዲቭዋር አንድ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ወደብ ላይ በቆሙ 322 መርከቦች ውስጥ ገብተው ሰብከዋል። ይህን ዘዴ በመጠቀም 247 መጻሕፍት፣ 2,284 መጽሔቶች፣ 500 ብሮሹሮችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ትራክቶች ከማበርከታቸውም በላይ መርከበኞቹ በባሕር ላይ በሚጓዙበት ጊዜ ሊመለከቷቸው የሚችሉ የቪዲዮ ካሴቶች ሰጥተዋቸዋል። በካናዳ አንድ ምሥክር የመኪና አካል ወደሚሠራበት አንድ ድርጅት ሄደ። ባለቤቱ ፍላጎት በማሳየቱ ወንድም ለአራት ሰዓት ተኩል እዚያው ቆየ፤ እርግጥ በየመሃሉ ደንበኞች ይመጡ ስለነበር ምሥክርነት ለመስጠት የቻለው ለአንድ ሰዓት ገደማ ብቻ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ለማጥናት ዝግጅት አደረጉ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ጥናታቸውን ሳይጀምሩ እኩለ ሌሊት ይሆን ነበር፤ ከዚያም ጥናታቸውን የሚጨርሱት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ነበር። ፕሮግራሙ በጣም አስቸጋሪ ሆኖባቸው እንደነበረ መገመት ይቻላል፤ ሆኖም ጥሩ ውጤት ተገኝቶበታል። ሰውየው እሁድ እሁድ ድርጅቱን ዘግቶ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ወሰነ። አሁን እሱም ሆነ ቤተሰቡ ጥሩ እድገት እያደረጉ ነው።

16. አምላክ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹርና እውቀት የተባለው መጽሐፍ በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ውጤታማ መሣሪያዎች መሆናቸውን የትኞቹ ተሞክሮዎች ያሳያሉ?

16 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹርና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ አሁንም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ኃይለኛ መሣሪያዎች ሆነው ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። በኢጣሊያ አውቶቡስ ስትጠብቅ የነበረች አንዲት መነኩሲት የመንግሥት ዜና ወሰደች። በሚቀጥለውም ቀን እንዲሁ ቀርበው አነጋገሯትና አምላክ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ወሰደች። ከዚያ በኋላ በየቀኑ በአውቶቡስ ፌርማታው ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የሚቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስታደርግ ቆየች። ከአንድ ወር ተኩል በኋላ ከገዳም ወጥታ ወደ አገሯ ወደ ጓቲማላ ተመልሳ ጥናቷን ለመቀጠል ወሰነች። በማላዊ የምትኖር ሎቢና የተባለች አንዲት ለእምነቷ ቀናኢ የሆነች ሴት ልጆቿ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በመጀመራቸው ተበሳጭታ ነበር። ያም ሆኖ ልጆቿ አጋጣሚ ባገኙ ጊዜ ሁሉ ለእናታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያካፍሉ ነበር። ሎቢና ሰኔ 1997 እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ስትመለከት “የሚመራ እውቀት” የሚለው አነጋገር ከነከናት። በሐምሌ ወር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። በነሐሴ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝታ ስብሰባውን በጠቅላላ በደንብ ተከታተለች። በዚሁ ወር መጨረሻ ቤተ ክርስቲያኗን ትታ በመውጣት ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆነች። ኅዳር 1997 ተጠመቀች።

17, 18. የማኅበሩ ቪዲዮዎች ሰዎች መንፈሳዊ ነገሮችን “እንዲያዩ” በመርዳት ረገድ ጠቃሚ መሆናቸው የተረጋገጠው እንዴት ነው?

17 የማኅበሩ ቪዲዮዎች ብዙዎች መንፈሳዊ ነገሮችን “እንዲመለከቱ” ረድተዋቸዋል። በሞሪሺየስ የሚኖር አንድ ሰው በቤተ ክርስቲያኑ በነበረው መከፋፈል የተነሳ ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቆ ወጣ። አንድ ሚስዮናዊ በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን የተባለውን ቪዲዮ በመጠቀም በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን አንድነት አሳየው። ሰውየው በመገረም “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች አንደኛውን በገነት ውስጥ አይደል እንዴ ያላችሁት!” ሲል ተናገረ። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። በጃፓን የምትኖር አንዲት እህት አማኝ ላልሆነው ባሏ የይሖዋ ምሥክሮች—⁠ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውን ቪዲዮ ስታሳየው ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ተነሳሳ። በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን የተባለውን ቪዲዮ ሲመለከት የይሖዋ ምሥክር የመሆን ፍላጎት አደረበት። መጽሐፍ ቅዱስ—⁠የእውነትና የትንቢት መጽሐፍ የተባለው ሦስት ተከታታይ ክፍሎች ያሉት ቪዲዮ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርግ ረዳው። በመጨረሻም የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል የተባለው ቪዲዮ ይሖዋ ሕዝቡ የሰይጣንን ጥቃት እንዲቋቋሙ እንደሚያጠነክራቸው እንዲገነዘብ አድርጎታል። ሰውየው ጥቅምት 1997 ተጠመቀ።

18 እነዚህ ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ከተገኙት እጅግ በርካታ ተሞክሮዎች ጥቂቶቹ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ሕያው እምነት እንዳላቸውና ይሖዋ እንቅስቃሴያቸውን በመባረክ ይህን እምነታቸውን እያጠነከረው እንዳለ ያሳያሉ።​—⁠ያዕቆብ 2:​17

በዛሬው ጊዜ እምነት አዳብሩ

19. (ሀ) እኛ ከአብርሃም በተሻለ ሁኔታ ላይ የምንገኘው እንዴት ነው? (ለ) ባለፈው ዓመት የኢየሱስን መሥዋዕታዊ ሞት ለማክበር ምን ያህል ሰዎች ተሰብስበው ነበር? (ሐ) ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር ያስመዘገቡት የትኞቹ አገሮች ናቸው? (ከገጽ 12 እስከ ገጽ 15 ያለውን ሰንጠረዥ ተመልከት።)

19 በዛሬው ጊዜ እኛ በብዙ መንገዶች ከአብርሃም በተሻለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ይሖዋ ለአብርሃም የገባውን ቃል ሁሉ እንደፈጸመ እናውቃለን። የአብርሃም ዝርያዎች ከነዓንን ወርሰዋል፤ ታላቅ ሕዝብም ሆነዋል። (1 ነገሥት 4:​20፤ ዕብራውያን 11:​12) ከዚህም በላይ አብርሃም ከካራን ከወጣ ከ1,971 ዓመታት ገደማ በኋላ የእሱ ዝርያ የሆነው ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ በውኃ ተጠመቀ። ከዚያም በራሱ በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በመጠመቅ መሲሕ ሆነ፤ በዚህ መንገድ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ የአብርሃም ዘር ሆኗል። (ማቴዎስ 3:​16, 17፤ ገላትያ 3:​16) በ33 እዘአ ኒሳን 14 ቀን ኢየሱስ ሕይወቱን በእሱ ለሚያምኑ ቤዛ አድርጎ አቀረበ። (ማቴዎስ 20:​28፤ ዮሐንስ 3:​16) በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን በእሱ መባረክ ይችላሉ። ባለፈው ዓመት ኒሳን 14 ቀን 13,896,312 ሰዎች ይህን አስደናቂ የፍቅር መግለጫ ለማክበር ተሰብስበው ነበር። ታላቁ ቃል አክባሪ ይሖዋ ትክክለኛነቱ በሚገባ ተረጋግጧል!

20, 21. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች በአብርሃም ዘር ራሳቸውን የባረኩት እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜስ ራሳቸውን እየባረኩ ያሉት እንዴት ነው?

20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከሥጋዊ እስራኤላውያን አንስቶ ከብሔራት የተውጣጡ ብዙዎች በአብርሃም ዘር በማመን ቅቡዓን የአምላክ ልጆች ከመሆናቸውም በላይ የአንድ አዲስ መንፈሳዊ “የእግዚአብሔር እስራኤል” አባሎች ሆነዋል። (ገላትያ 3:​26–29፤ 6:​16፤ ሥራ 3:​25, 26) በሰማይ የአምላክ መንግሥት ተባባሪ ገዥዎች በመሆን የማይጠፋ መንፈሳዊ ሕይወት የማግኘት የተረጋገጠ ተስፋ ነበራቸው። በዚህ መንገድ የሚባረኩት 144,000 ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል የቀሩት ጥቂቶች ናቸው። (ራእይ 5:​9, 10፤ 7:​4) ባለፈው ዓመት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ በመካፈል የዚህ ቁጥር አባላት መሆናቸውን እንደሚያምኑ የመሠከሩት 8,756 ነበሩ።

21 በዛሬው ጊዜ ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች በራእይ 7:​9–17 ላይ በትንቢት የተነገረላቸው “እጅግ ብዙ ሰዎች” ናቸው። በኢየሱስ በኩል ራሳቸውን ስለሚባርኩ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። (ራእይ 21:​3–5) በ1998 በስብከቱ ሥራ የተካፈሉት 5,888,650 ሰዎች ይህ ሕዝብ በእርግጥም “እጅግ ብዙ” መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። በተለይ ሩስያና ዩክሬይን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ሪፖርት ማድረጋቸው በጣም የሚያስደስት ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ሪፖርትም በጣም የሚያስደንቅ ነው፤ በነሐሴ ወር 1,040,283 አስፋፊዎች ሪፖርት አድርገዋል! እነዚህ አገሮች ባለፈው ዓመት ከ100,000 በላይ አስፋፊዎች ሪፖርት ካደረጉት 19 አገሮች ሦስቱ ብቻ ናቸው።

በቅርቡ ፍጻሜውን የሚያገኝ ተስፋ

22, 23. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ልባችንን ማጽናት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ እንደጠቀሳቸው እምነት የለሽ ሰዎች ሳይሆን እንደ አብርሃም መሆናችንን ልናረጋግጥ የምንችለው እንዴት ነው?

22 በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ይሖዋ የገባው ቃል ምን ያህል ፍጻሜውን እንዳገኘ ልብ እንዲሉ የሚያደርግ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ በ1914 በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ በመገኘት የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በዙፋኑ ላይ ተቀምጧል። (ማቴዎስ 24:​3፤ ራእይ 11:​15) አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ የአብርሃም ዘር በሰማይ እየገዛ ነው! ያዕቆብ በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ታገሡ፣ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና” ብሏቸው ነበር። (ያዕቆብ 5:​8) አሁን ይህ የክርስቶስ መገኘት እውን ሆኗል! አሁን ልባችንን የምናጸናበት የበለጠ ምክንያት አለን!

23 አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ቋሚ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ትርጉም ባለው ጸሎት ዘወትር እንዲታደስ እናድርግ። ቃሉን በመታዘዝ ምንጊዜም የይሖዋን በረከት የምናገኝ እንሁን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጳውሎስ እንደጠቀሳቸው እምነታቸው እንደደከመባቸውና እንደሞተባቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ አብርሃም እንሆናለን። እጅግ ቅዱስ ከሆነው እምነታችን ሊነጥለን የሚችል ነገር አይኖርም። (ይሁዳ 20) ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በ1999 የአገልግሎት ዓመትም ሆነ ለዘላለም እንዲህ ዓይነት አቋም እንዲኖራቸው እንጸልያለን።

[መልሱ ምንድን ነው?]

◻ በዛሬው ጊዜ አምላክን ልንሰማ የምንችለው እንዴት ነው?

◻ ለአምላክ ትርጉም ያለው ጸሎት ማቅረብ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

◻ የይሖዋን መመሪያ በታዛዥነት የምንከተል ከሆነ እምነታችን የሚጠነክረው እንዴት ነው?

◻ በዓመታዊው ሪፖርት (ከገጽ 12 እስከ ገጽ 15) ላይ ይበልጥ ትኩረት የሚስቡ ሆነው ያገኘሃቸው ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው?

[በገጽ 12-15 ላይ የሚገኝ ግራፍ]

የ1998 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት።)

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋን ቃል የምንሰማ ከሆነ በገባው ቃል ላይ ያለን እምነት ይታደሳል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎት ስንካፈል እምነታችን ይጠነክራል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ