ይሖዋ ለታመኑ አገልጋዮቹ የሰጣቸውን ተስፋዎች ይፈጽማል
“የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና።”—ዕብራውያን 10:23
1, 2. ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ ሙሉ ትምክህት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ አገልጋዮቹ በእሱና በሰጠው ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። አንድ ሰው እንዲህ ያለ እምነት ካለው ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ ሙሉ በሙሉ ሊፈጽም እንደሚችል ያምናል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል:- እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል” ይላል።—ኢሳይያስ 14:24
2 “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል” የሚለው አነጋገር ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች ለመፈጸም በመሐላ ማረጋገጡን ያሳያል። ለዚህም ነው ቃሉ እንዲህ ሊል የቻለው:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” (ምሳሌ 3:5, 6) በይሖዋ ስንታመንና በጥበቡም ለመመራት ራሳችንን ስናቀርብ የአምላክ ጥበብ “ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ” ስለሆነች መንገዳችን ያለ ምንም ጥርጥር ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርስ ይሆናል።—ምሳሌ 3:18፤ ዮሐንስ 17:3
በጥንት ዘመን የታየ እውነተኛ እምነት
3. ኖኅ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ እውነተኛ እምነት ለነበራቸው ሰዎች ስላደረጋቸው ነገሮች የሚናገረው ዘገባ የተስፋ ቃሉን እንደሚፈጽም እርግጠኛ ለመሆን እንደሚቻል ያመለክታሉ። ለምሳሌ ያህል ከ4,400 ዓመታት በፊት አምላክ በኖኅ ዘመን የነበረውን ዓለም በጎርፍ እንደሚያጠፋ ለኖኅ ነግሮት ነበር። የሰዎችና የእንስሳት ዘር የሚተርፍበት ትልቅ መርከብ እንዲሠራ ኖኅን አዘዘው። ታዲያ ኖኅ ምን አደረገ? ዕብራውያን 11:7 እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ።” ኖኅ ከዚህ ቀደም ተፈጽሞ በማያውቅ፣ ‘ገና ባልታየ ነገር’ ላይ ይህን የመሰለ እምነት ሊያሳይ የቻለው ለምንድን ነው? አምላክ ከእርሱ በፊት ለነበሩ ሰዎች ያደረገውን ሁሉ እንዲሁም አምላክ የተናገረው ሁሉ ሳይፈጸም እንደማይቀር ያውቅ ስለነበረ ነው። በዚህም ምክንያት የጥፋቱ ውኃ መምጣቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ሆነ።—ዘፍጥረት 6:9-22
4, 5. አብርሃም በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ሊጥል የቻለው ለምንድን ነበር?
4 እውነተኛ እምነት በማሳየት ሌላው ምሳሌ የሚሆነን አብርሃም ነው። ከ3,900 ዓመታት ገደማ በፊት አምላክ አብርሃምን ከሣራ የተወለደለትን አንድያ ልጁን ይስሐቅን እንዲሠዋለት ጠየቀው። (ዘፍጥረት 22:1-10) አብርሃም እንዴት ያለ ምላሽ ሰጠ? ዕብራውያን 11:17 “አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ” ይላል። ይሁን እንጂ በመጨረሻው ቅጽበት ላይ የይሖዋ መልአክ እንዳይሠዋው ከለከለው። (ዘፍጥረት 22:11, 12) አብርሃም እንዲህ ያለውን ለማሰብ እንኳ የሚከብድ ነገር ለማድረግ የተነሳው ለምንድን ነው? ዕብራውያን 11:19 እንደሚለው “እግዚአብሔር [ይስሐቅን] ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው” ስላሰበ ነው። አብርሃም ሙታን ሲነሱ አይቶም ሆነ ከዚያ በፊትም ከሙታን የተነሱ ሰዎች ስለመኖራቸው የሚገልጽ ዘገባ ሳይኖር በትንሣኤ ሊያምን የቻለው ለምንድን ነው?
5 አምላክ ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቃል በገባላቸው ጊዜ ሣራ 89 ዓመት ሆኗት እንደነበረ አስታውሱ። የሣራ ማሕፀን ልጅ ለመጸነስ የማይችል በድን ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል። (ዘፍጥረት 18:9-14) አምላክ ግን የሣራ ማሕፀን ሕያው እንዲሆን ስላደረገ ይስሐቅን ወለደች። (ዘፍጥረት 21:1-3) አብርሃም፣ በድን የሆነውን የሣራን ማሕፀን ሕይወት ሊዘራበት የቻለው አምላክ ይስሐቅንም አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ወደ ሕይወት ሊመልሰው እንደሚችል አውቋል። ሮሜ 4:20, 21 ስለ አብርሃም እንዲህ ይላል:- “ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፣ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፣ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።”
6. ኢያሱ በይሖዋ ላይ ያለውን ትምክህት የገለጸው እንዴት አድርጎ ነበር?
6 ከ3,400 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ኢያሱ የመቶ ዓመት ሰው ከሆነ በኋላና አምላክ ምን ያህል እምነት የሚጣልበት እንደሆነ በሕይወት ዘመኑ ከተመለከተ በኋላ በአምላክ ሊተማመን የቻለበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።”—ኢያሱ 23:14
7, 8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የታመኑ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ለማዳን ምን ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር? ለምንስ?
7 ከ1,900 ዓመታት ገደማ በፊት ትሑት ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች እውነተኛ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ተገንዝበዋል፤ ትምህርቶቹንም ተቀብለዋል። ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ይህን የመሰለ ጽኑ መሠረት በማግኘታቸው ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች አመኑ። ስለዚህም ኢየሱስ፣ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ከዳተኞች በመሆናቸው የተነሣ የአምላክ የቅጣት ፍርድ እንደሚመጣባቸው በተናገረ ጊዜ አመኑት። ሕይወታቸውን ለማዳን ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው በነገራቸው ጊዜም የነገራቸውን ነገር በትክክል ፈጸሙ።
8 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ኢየሩሳሌም በሠራዊት ተከባ ሲመለከቱ መሸሽ እንደሚኖርባቸው ነገራቸው። የሮማ ሠራዊት በ66 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። ወዲያው ግን ባልታወቀ ምክንያት ሮማውያኑ ዘመቻውን አቋርጠው ተመለሱ። ኢየሱስ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ” ብሎ ስለነበረ ክርስቲያኖች ከተማዋን ጥለው የሚሸሹበት ጊዜ መድረሱን የሚያሳይ ምልክት ነበር። (ሉቃስ 21:20, 21) እውነተኛ እምነት የነበራቸው ሁሉ ኢየሩሳሌምንና አካባቢዋን ለቅቀው በመውጣት ደህንነት ወደሚያገኙበት አካባቢ ሸሹ።
እምነት ማጣት ያስከተለው መዘዝ
9, 10. (ሀ) ሃይማኖታዊ መሪዎች በኢየሱስ ላይ እምነት እንደሌላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ይህ እምነት ማጣት ምን አስከትሎ ነበር?
9 እውነተኛ እምነት ያልነበራቸውስ ምን አደረጉ? በዚያው ቦታ ቆዩ እንጂ አልሸሹም። መሪዎቻቸው የሚያድኗቸው መስሎአቸው ነበር። እነዚህ መሪዎችና ተከታዮቻቸውም ቢሆኑ የኢየሱስን መሲሕነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ነበሯቸው። ታዲያ ኢየሱስ የተናገረውን ያልተቀበሉት ለምን ነበር? ልባቸው ክፉና ጠማማ ስለነበረ ነው። ይህ የልባቸው ክፋት ቀደም ሲል ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ካስነሳው በኋላ ተራው ሕዝብ ወደ እርሱ ሲጎርፍ በተመለከቱ ጊዜ ባደረጉት ነገር ገሐድ ወጥቷል። ዮሐንስ 11:47, 48 እንዲህ ሲል ይተርካል:- “የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ [የአይሁዶችን ከፍተኛ ፍርድ ቤት] ሰብስበው:- ምን እናድርግ? ይህ ሰው [ኢየሱስ]፤ ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፣ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ።” ቁጥር 53 እንደሚለው “እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።”
10 ኢየሱስ ሞቶ የነበረውን አልዓዛር በማስነሳቱ እንዴት ያለ አስደናቂ ተአምር ነበር! ይሁን እንጂ የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስ ይህን በማድረጉ እንዲገደል ይፈልጉ ነበር። ይህ ሥር የሰደደ ክፋታቸው አልዓዛርን ለማስገደል በማቀዳቸው ይበልጥ ግልጽ ሆኗል። “የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፣ ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና።” (ዮሐንስ 12:10, 11) እነዚህ ክፉ ካህናት አልዓዛር ከሞት ተነስቶ ሳይውል ሳያድር እንደገና እንዲሞት ፈለጉ! ስለ አምላክ ፈቃድም ሆነ ስለ ተራው ሕዝብ ደህንነት ደንታ አልነበራቸውም። ስለ ማዕረጋቸውና ስለ ግል ጥቅማቸው ብቻ የቆሙ ራስ ወዳዶች ነበሩ። “ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋል።” (ዮሐንስ 12:43) ይሁን እንጂ እምነት የለሾች በመሆናቸው ዋጋቸውን አግኝተዋል። በ70 እዘአ የሮማ ሠራዊት ተመልሰው መጥተው አገራቸውንም ሆነ ሕዝባቸውን አጠፉ። ብዙዎቹም ተገደሉ።
በጊዜያችን እምነት ያሳዩ ሰዎች
11. በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሰዎች እውነተኛ እምነት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነበር?
11 በዚህ መቶ ዘመንም ቢሆን እውነተኛ እምነት የነበራቸው በርካታ ሰዎች ኖረዋል። ለምሳሌ በ1900ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ሰዎች በአጠቃላይ ሰላም የሰፈነበት ጥሩ ጊዜ ይመጣል ብለው ጓጉተው እንደነበረ ታስታውሳላችሁ። በዚያ ዘመን በይሖዋ ላይ እምነት የነበራቸው ሰዎች የሰው ልጅ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ ወደማይታወቅ የመከራ ዘመን ሊገባ እንደተቃረበ ያስጠነቅቁ ነበር። የአምላክ ቃል በማቴዎስ ምዕራፍ 24፣ በ2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 እና በሌሎችም ቦታዎች ላይ የሚተነብየው ይህንን ነው። እነዚህ የእምነት ሰዎች የተናገሩት ነገር በ1914 ከተደረገው አንደኛ የዓለም ጦርነት ጀምሮ በትክክል ተፈጽሟል። በዚያ ጊዜ ዓለም በትንቢት ወደ ተነገረው እጅግ ‘አስጨናቂ ወደሆነው’ የ“መጨረሻ ቀን” ገብቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የይሖዋ አገልጋዮች ሌሎች ያላስተዋሉትን ይህን ሐቅ ሊያውቁ የቻሉት ለምን ነበር? ልክ እንደ ኢያሱ ይሖዋ ከተናገራቸው ነገሮች አንዱ እንኳን መሬት ጠብ እንደማይል ያምኑ ስለነበር ነው።
12. ዛሬ ያሉ አገልጋዮቹ ይሖዋ እንደሚፈጽመው ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑበት ተስፋ የትኛው ነው?
12 በዛሬው ጊዜ በይሖዋ የሚታመኑ የይሖዋ አገልጋዮች በመላው ዓለም ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ሆነዋል። የአምላክ ቃል በተናገረው መሠረት ከተፈጸሙት ሁኔታዎች አምላክ ይህን ዓመፀኛ፣ ምግባረ ብልሹ ሥርዓት የሚያጠፋበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ ያውቃሉ። ስለዚህም “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለው የ1 ዮሐንስ 2:17 ቃል ሲፈጸም የሚመለከቱበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ እርግጠኞች ናቸው። ይሖዋ ይህን ተስፋውን እንደሚፈጽም አገልጋዮቹ ሙሉ በሙሉ ይተማመናሉ።
13. በይሖዋ መታመን የምትችሉት እስከ ምን ድረስ ነው?
13 በይሖዋ መታመን የምትችሉት እስከ ምን ድረስ ነው? በይሖዋ ላይ ፍጹም እምነት መጣል ትችላላችሁ! እርሱን በማገልገላችሁ ምክንያት ሕይወታችሁን ብታጡ እንኳን ከሞት አስነስቶ ከአሁኑ እጅግ የተሻለ ሕይወት ይሰጣችኋል። ኢየሱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “[“በመታሰቢያ፣” NW] መቃብር ያሉቱ ሁሉ [አምላክ የሚያስባቸው ሁሉ ማለት ነው] ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ይወጣሉና።” (ዮሐንስ 5:28, 29) ይህን ሊያደርግ የሚችል ሐኪም፣ የፖለቲካ መሪ፣ ሳይንቲስት፣ ነጋዴ ወይም ሌላ የምታውቁት ሰው አለ? ይህን ሊያደርግ የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ ያለፈው የሰው ልጅ ታሪክ ያረጋግጣል። ይሖዋ ሊያደርገው ይችላል፣ ደግሞም ያደርገዋል!
ለታመኑ ሰዎች የተዘጋጀ አስደሳች ጊዜ
14. የአምላክ ቃል ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አስደናቂ ስለሆነው የወደፊት ጊዜ ምን ተስፋ ይሰጣል?
14 ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” ሲል በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ግዛት ሥር አዲስ ዓለም እንደሚመጣ በእርግጠኝነት ማመልከቱ ነበር። (ማቴዎስ 5:5) ይህም በመዝሙር 37:29 ላይ የሚገኘውን “ጻድቃን ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል አምላክ የሰጠውን ተስፋ የሚያጠናክር ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ አንድ ክፉ አድራጊ በእርሱ እንደሚያምን በተናገረ ጊዜ ኢየሱስ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። (ሉቃስ 23:43) አዎን፣ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ይህ ሰው ከሞት ተነስቶ በምድር ላይ በገነት የመኖር አጋጣሚ እንዲያገኝ ያደርጋል። ዛሬ በይሖዋ መንግሥት ላይ እምነታቸውን የጣሉ ሁሉ “[እግዚአብሔር] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” በተባለላት ገነት ውስጥ ለመኖር ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ራእይ 21:4
15, 16. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት ሰላም የሰፈነበት የሚሆነው ለምንድን ነው?
15 ይህ አዲስ ዓለም ምን እንደሚመስል ለጥቂት ጊዜ በዓይነ ሕሊናችን እንመልከት። እዚያው በመኖር ላይ እንዳለን አድርገን እናስብ። ወዲያውኑ ሰዎች ሁሉ ፍጹም በሆነ ሰላም አንድ ላይ በደስታ ሲኖሩ እንመለከታለን። “ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች” የሚለው የኢሳይያስ 14:7 ትንቢት ተፈጽሞላቸው ተደስተዋል። ይህን ያህል የተደሰቱት ለምን ይሆን? አንደኛ ነገር የቤቶቻቸው በሮች ቁልፍ የሌላቸው መሆናቸውን አስተውሉ። ወንጀልም ሆነ ዓመፅ ስለማይኖር ቁልፍ አያስፈልጋቸውም። የአምላክ ቃል ልክ ይሆናል ብሎ እንደተናገረው ሆኗል:- “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ሚክያስ 4:4
16 ማንኛውም ዓይነት ጦርነት በሕግ የታገደ በመሆኑ ጦርነት የሚባል ነገር አይኖርም። ማንኛውም ዓይነት የጦር መሣሪያ ተቀጥቅጦ የሰላም መሣሪያ ሆኗል። ኢሳይያስ 2:4 ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል:- “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” ደግሞም በዚያን ጊዜ የምንጠብቀው ነገር ይህ ነው! ለምን? ምክንያቱም የአዲሱ ዓለም ነዋሪዎች አምላክን ያገለግሉ በነበረበት በአሮጌው ዓለም ውስጥ ይህን ማድረግ ተምረዋል።
17. በአምላክ መንግሥት ሥር ምን ዓይነት የኑሮ ሁኔታዎች ይሰፍናሉ?
17 ሌላም የምታስተውሉት ነገር አለ። ድህነት ፈጽሞ የለም። በደሳሳ ጎጆ ውስጥ የሚኖር ወይም የተቦጫጨቀ ልብስ የለበሰ ወይም ቤት አጥቶ የሚንከራተት ሰው የለም። እያንዳንዱ ሰው ምቹ የሆነ ቤት፣ የሚያምሩ ዛፎችና አበቦች የበቀሉበት በጥሩ ሁኔታ የተያዘ ርስት አለው። (ኢሳይያስ 35:1, 2፤ 65:21, 22፤ ሕዝቅኤል 34:27) እንዲሁም “በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራራዎች በሰብል ይሸፈኑ” የሚለው የአምላክ ተስፋ ስለተፈጸመና ለሁሉም የሚሆን የተትረፈረፈ ምግብ ስላለ ረሃብ የሚባል ነገር የለም። (መዝሙር 72:16 የ1980 ትርጉም) በአምላክ መንግሥት መሪነት አምላክ በኤደን በነበረው ዓላማ መሠረት ክብራማ የሆነ ገነት በመላዋ ምድር ላይ እየተስፋፋ ነው።—ዘፍጥረት 2:8
18. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሰዎችን የሚያስፈራሩ የትኞቹ ነገሮች ይቀራሉ?
18 በተጨማሪም ሁሉም ሰው ያለው ጉልበትና ጥንካሬ ያስደንቃችኋል። እንዲህ የሆነው አሁን የአካልም ሆነ የአእምሮ ፍጽምና ስላገኙ ነው። በሽታ፣ ሕመም ወይም ሞት ከእንግዲህ ፈጽሞ አይኖርም። በጋሪ ወንበር የሚገፋ ወይም የሆስፒታል አልጋ ቁራኛ የሆነ ሰው ፈጽሞ አይገኝም። ይህ ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ቀርቷል። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) የሚገርመው ደግሞ የሚተናኮሉ አራዊት አለመኖራቸው ነው። በአምላክ ኃይል ሰላማውያን እንዲሆኑ ተደርገዋል!—ኢሳይያስ 11:6-8፤ 65:25፤ ሕዝቅኤል 34:25
19. በአዲሱ ዓለም ውስጥ እያንዳንዱ ቀን ‘አስደሳች’ የሚሆነው ለምንድን ነው?
19 የዚህ አዲስ ዓለም ታማኝ ነዋሪዎች የሚገነቡት ኅብረተሰብ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ጉልበታቸውና ችሎታቸው፣ እንዲሁም የምድር ሀብት የሚውለው ጎጂ ለሆኑ ነገሮች ሳይሆን ገንቢ ለሆኑ ነገሮች፣ ከሌሎች ጋር ለመረዳዳት እንጂ ለመፎካከር መሆኑ ይቀራል። በተጨማሪም ‘ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ ስለሚሆኑ’ የምታገኟቸው ሰዎች በሙሉ የምታምኗቸው ናቸው። (ኢሳይያስ 54:13) ሁሉም ሰው በአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚገዛ በመሆኑ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:9) በእርግጥ በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ መዝሙር 37:11 እንደሚለው በየቀኑ ‘ይደሰታሉ።’
አስደሳች ጊዜ እንደሚመጣ ማረጋገጫ ተሰጥቷል
20. ሰላም በሰፈነበት ጊዜ ለመኖር ምን ማድረግ አለብን?
20 በዚህ ደስታ በሞላበት ጊዜ ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል? ኢሳይያስ 55:6 “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት” በማለት ይነግረናል። ይሖዋን በምንፈልግበት ጊዜ በመዝሙር 143:10 ላይ እንደተገለጸው “አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ” የሚል ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች በይሖዋ ፊት ያለ ነውር ሊመላለሱና ግሩም የሆነ ጊዜ እንደሚመጣ ሊጠባበቁ ይችላሉ። “ቅንነትን ጠብቅ፣ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ፤ የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል።”—መዝሙር 37:37, 38
21, 22. አምላክ ዛሬ በማሰባሰብ ላይ ያለው ነገር ምንድን ነው? ሥልጠናውስ በመካሄድ ላይ ያለው እንዴት ነው?
21 በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ፈቃዱን ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን ከሁሉም ብሔራት እየጠራ ነው። የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስቀድሞ እንደተናገረው እነዚህን ሰዎች ለአዲሱ ምድራዊ ማኅበረሰብ መሠረት እንዲሆኑ እያደረጋቸው ነው:- “በዘመኑም ፍጻሜ [አሁን እኛ በምንኖርበት ዘመን ማለት ነው] . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ [ወደ እውነተኛ አምልኮው]፣ . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።”—ኢሳይያስ 2:2, 3
22 ራእይ 7:9 እነዚህን ሰዎች ‘ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ይላቸዋል። ቁጥር 14 ደግሞ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” ይላል። ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ይተርፋሉ። የአዲሱ ዓለም መሠረት የሚሆኑት እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ሲሆን በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጨመሩ ነው። የታመኑ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሚያገኙት የዘላለም ሕይወት የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና በማግኘት ላይ ናቸው። ይህችን ምድር ወደ ገነት ለመለወጥ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊም ሆነ ሌላ እውቀትና ችሎታ በመማር ላይ ናቸው። ይህ ገነት እውን እንደሚሆን ሙሉ ትምክህት አላቸው፤ ምክንያቱም “የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና።”—ዕብራውያን 10:23
ለክለሳ የሚሆኑ ነጥቦች
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እምነት ማጣት ምን አስከትሎ ነበር?
◻ የአምላክ አገልጋዮች በእሱ ሊታመኑ የሚችሉት እስከ ምን ድረስ ነው?
◻ የታመኑ ሰዎች ምን ዓይነት የወደፊት ጊዜ ይጠብቃቸዋል?
◻ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አስደሳች ሕይወት እንድናገኝ ምን ማድረግ አለብን?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ለአዲሱ ምድራዊ ኅብረተሰብ መሠረት የሚሆኑ ሰዎችን እያሰባሰበ ነው