በፍርድ ሸለቆ የተወሰደ የቅጣት እርምጃ
“አሕዛብ . . . ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና።”—ኢዩኤል 3:12
1. ኢዩኤል ብዙ ሰዎች “በፍርድ ሸለቆ” ተሰብስበው ያየው ለምንድን ነው?
“የብዙ፣ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ”! እነዚህን ስሜት ቀስቃሽ ቃላት የምናነበው ኢዩኤል 3:14 ላይ ነው። እነዚህ ብዙ ሰዎች የተሰበሰቡት ለምንድን ነው? “የእግዚአብሔር ቀን . . . ቀርቧልና” በማለት ኢዩኤል መልሱን ይሰጠናል። ይህ የይሖዋ ትክክለኛነት የሚረጋገጥበት፣ የተቋቋመውን የክርስቶስ ኢየሱስ መንግሥት አንቀበልም ባሉ በጣም ብዙ ሰዎች ላይ የቅጣት እርምጃ የሚወሰድበት ታላቅ ቀን ነው። በመጨረሻ በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሱት “አራቱ መላእክት” ገትረው የያዟቸውን “አራቱን የምድር ነፋሳት” ይለቁና “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል።”—ራእይ 7:1፤ ማቴዎስ 24:21
2. (ሀ) ይሖዋ የቅጣት እርምጃ የሚወሰድበት ቦታ የ“ኢዮሣፍጥ ሸለቆ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢዮሣፍጥ ጥቃት በተሰነዘረበት ጊዜ ተገቢ የሆነ እርምጃ የወሰደው እንዴት ነው?
2 ይህ የቅጣት እርምጃ የሚወሰድበት ቦታ ኢዩኤል 3:12 ላይ የ“ኢዮሣፍጥ ሸለቆ” ተብሏል። በይሁዳ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ በነበረው ዘመን ይሖዋ ጥሩ ንጉሥ ከሆነው ከኢዮሣፍጥ ጎን በመቆም በዚህ ሸለቆ የቅጣት እርምጃ ወስዷል። ኢዮሣፍጥ ማለት “ይሖዋ ፈራጅ ነው” ማለት ነው። በዚያ ዘመን የተፈጸመውን ሁኔታ ብንመረምር በዚህ በዘመናችን ሊፈጸም የተቃረበውን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ለመረዳት እንችላለን። ዘገባው በ2 ዜና መዋዕል ምዕራፍ 20 ላይ ይገኛል። በዚህ ምዕራፍ በቁጥር 1 ላይ “የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ” እንደመጡ እናነባለን። ኢዮሣፍጥ ምን አደረገ? ያደረገው ነገር የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ሁሉ ከሚያደርጉት ነገር የተለየ አልነበረም። “አምላካችን ሆይ፣ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው” ብሎ ከልቡ በመጸለይ የይሖዋን መመሪያ ጠየቀ።—2 ዜና መዋዕል 20:12
ይሖዋ ለጸሎት ምላሽ ይሰጣል
3. አይሁዳውያን ከጎረቤት ብሔራት ጥቃት በተሰነዘረባቸው ጊዜ ይሖዋ ምን መመሪያ ሰጣቸው?
3 “የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው” እንዳሉ ይሖዋ መልሱን ሰጠ። (2 ዜና መዋዕል 20:13) ታላቁ ጸሎት ሰሚ አምላክ በዛሬው ጊዜ ‘በታማኝና ልባም ባሪያው’ እንደሚጠቀም ሁሉ በዚያን ጊዜ ለተሰበሰቡት ሰዎች መልስ እንዲሰጥለት የሕዚኤል ለተባለው ሌዋዊ ነቢይ ሥልጣን ሰጥቶት ነበር። (ማቴዎስ 24:45) እንዲህ እናነባለን:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል:- ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፣ አትደንግጡም። . . . እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ . . . ተሰለፉ፣ ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፣ አትደንግጡም፣ ነገም ውጡባቸው።”—2 ዜና መዋዕል 20:15-17
4. ይሖዋ ሕዝቦቹ የጠላቶቻቸውን ግድድር በመጋፈጥ በኩል ዝም ብለው እንዲመለከቱ ሳይሆን ንቁ እንዲሆኑ የፈለገባቸው በምን መንገድ ነው?
4 ይሖዋ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና ሕዝቡ እጃቸውን አጣምረው ቁጭ እንዲሉና በተአምር ሲያድናቸው እንዲመለከቱ አላደረገም። የጠላታቸውን ግድድር በመቋቋም ረገድ ቅድሚያውን ወስደው ሊያደርጉት የሚገባ ነገር ነበር። ንጉሡና “የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር” በማለዳ ተነስተው በታዛዥነት ወራሪዎቹን ጭፍሮች ለመገናኘት ወጡ። በመንገድም ላይ እንዳሉ ንጉሡ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፣ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፣ ነገሩም ይሰላላችኋል” በማለት ቲኦክራሲያዊ መመሪያና ማበረታቻ ሰጣቸው። (2 ዜና መዋዕል 20:20) በይሖዋ ማመን! በነቢያቱ ማመን! ጠላቶቻቸውን ድል የሚነሱበት ቁልፍ ይህ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋን አገልግሎት በትጋት በምንፈጽምበት ጊዜ ይሖዋ እምነታችን በድል አድራጊነት እንዲወጣ እንደሚያደርግ ፈጽሞ አንጠራጠር!
5. ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋን በማወደሱ በንቃት የሚካፈሉት እንዴት ነው?
5 በኢዮሣፍጥ ዘመን ይኖሩ እንደነበሩት አይሁዳውያን እኛም ‘ፍቅራዊ ደግነቱ ለዘላለም በመሆኑ ይሖዋን ማወደስ ይኖርብናል።’ ይሁን እንጂ ይህን ውዳሴ የምናቀርበው እንዴት ነው? የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት በመስበክ ነው! በዚያ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን “ዝማሬውንና ምሥጋናውን” ማሰማት እንደጀመሩ እኛም እምነታችንን በሥራ እናሳያለን። (2 ዜና መዋዕል 20:21, 22) አዎን፣ ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚዘጋጅበት በአሁኑ ጊዜ ይህን የመሰለ ከፍተኛ ዋጋ ያለው እምነት እናሳይ! የተጓዝንበት መንገድ በጣም ረዥም መስሎ የታየን እንኳን ቢሆን ከፍተኛ ችግር ባለባቸው የምድር ክፍሎች የሚኖሩ ድል አድራጊ ወንድሞቻችን እንደሚያደርጉት ለመጽናትና በእምነታችን ንቁ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የ1998 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ሪፖርት እንዳደረገው በስደት፣ በዓመፅ፣ በድርቅና በኢኮኖሚ ችግር ክፉኛ በተመቱ አንዳንድ አገሮች ታማኝ ወንድሞቻችን በጣም አስደናቂ የሆነ ጭማሪ በማግኘት ላይ ናቸው።
ይሖዋ ሕዝቡን ያድናል
6. በዛሬው ጊዜ ጠንካራ እምነት መገንባት ታማኝ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
6 ይሁዳን የከበቧት አምላካዊ ባሕርያት የሌላቸው ብሔራት የአምላክን ሕዝቦች ለመዋጥ ቢነሱም የይሖዋ አገልጋዮች ግን በአርዓያነት የሚጠቀስ እምነት በማሳየት የይሖዋን ውዳሴ ዘምረዋል። እኛም ዛሬ ይህን የመሰለ እምነት ለማሳየት እንችላለን። መላ ሕይወታችን ለይሖዋ ውዳሴ በምናከናውነው ሥራ የተሞላ ከሆነ መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን መሰሪ በሆኑት የሰይጣን የተንኮል ዘዴዎች የማይደፈር ይሆናል። (ኤፌሶን 6:11) ጠንካራ እምነት ከኖረን ወራዳ በሆኑ መዝናኛዎች፣ በፍቅረ ንዋይና በዙሪያችን ያለው እየሞተ ያለ ዓለም በተጠናወተው የግድየለሽነት መንፈስ አንሸነፍም። እንዲህ ያለው የማይበገር እምነት ‘በተገቢው ጊዜ’ የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ ዘወትር በመመገብ ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ ጋር በታማኝነት እያገለገልን እንድንቀጥል ያስችለናል።— ማቴዎስ 24:45
7. የይሖዋ ምሥክሮች ለተሰነዘሩባቸው የተለያዩ ጥቃቶች ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
7 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው እምነታችን በማቴዎስ 24:48-51 ላይ የተጠቀሰውን “ክፉ ባሪያ” መንፈስ የሚያንጸባርቁ ሰዎች ከሚያናፍሱት የጥላቻ ዘመቻ ይጠብቀናል። በአሁኑ ጊዜ ከሃዲዎች ይህን ትንቢት በሚያስገርም ሁኔታ በመፈጸም በበርካታ አገሮች የውሸት ፕሮፓጋንዳ ከመንዛትም አልፎ ተርፎ ከፖለቲካ ሰዎች ጋር ይመሳጠራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ተገቢ ሆኖ ሲገኝ በፊልጵስዩስ 1:7 ላይ እንደተገለጸው ‘ምሥራቹን ለመከላከልና ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ’ ለማድረግ የሚያስችላቸውን እርምጃ ወስደዋል። ለምሳሌ ያህል መስከረም 26 ቀን 1996 ስትራስቡርግ ላይ ያስቻለው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ዘጠኝ ዳኞች ከግሪክ አገር በቀረበላቸው አንድ ጉዳይ ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች ‘የታወቁ ሃይማኖቶች’ ከሚባሉት መካከል የሚካተቱና” የሐሳብ፣ የሕሊናና የእምነት ነጻነት እንዲሁም እምነታቸውን ለሌሎች ሰዎች የማሳወቅ መብት ያላቸው ናቸው የሚል ብይን በአንድ ድምፅ ሰጥተዋል። ስለ ከሃዲዎቹ ግን የአምላክ ፍርድ እንዲህ ይላል:- “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፣ ደግሞ:- የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።”—2 ጴጥሮስ 2:22
8. በኢዮሣፍጥ ዘመን ይሖዋ በሕዝቡ ጠላቶች ላይ የቅጣት ፍርዱን ያስፈጸመው እንዴት ነበር?
8 በኢዮሣፍጥ ዘመን ይሖዋ ሕዝቡን ሊያጠቁ በፈለጉ ሰዎች ላይ የቅጣት እርምጃ ወስዷል። እንዲህ እናነባለን:- “ይሁዳን ሊወጉ በወጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ። የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ፣ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ።” (2 ዜና መዋዕል 20:22, 23) አይሁዳውያን ይህን ሥፍራ የበራካ ሸለቆ ብለው ጠሩት። በራካ ማለት “በረከት” ማለት ነው። በዘመናችንም ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ የሚወስደው የቅጣት እርምጃ ለሕዝቦቹ በረከት ያመጣላቸዋል።
9, 10. የይሖዋን የቅጣት ፍርድ መቀበል የሚገባቸው ሰዎች እነማን ናቸው?
9 በዘመናችን የይሖዋን የቅጣት ፍርድ የሚቀበሉት እነማን ናቸው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ወደ ኢዩኤል ትንቢት መለስ ማለት አለብን። ኢዩኤል 3:3 ‘ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ስለሰጡና ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ስለሸጡ’ የሕዝቡ ጠላት ስለሆኑ ሰዎች ይናገራል። አዎን፣ የአምላክን አገልጋዮች እዚህ ግቡ የማይባሉ ሰዎች፣ ልጆቻቸውንም ለጋለሞታ ከሚሰጥ ወይም ለአንድ ገንቦ ወይን ከሚከፈል ዋጋ የማይበልጡ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ለዚህ ነገር በኃላፊነት መጠየቃቸው አይቀርም።
10 መንፈሳዊ ግልሙትና የሚፈጽሙም ቢሆኑ በእኩል ደረጃ የጥፋት ፍርድ ሊቀበሉ ይገባል። (ራእይ 17:3-6) በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ አንዳንድ ቀሳውስት በቅርብ ጊዜያት እንዳደረጉት የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖችን በመጎትጎት የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲያሳድዱና ሥራቸውን እንዲያግዱ የሚያደርጉ ሰዎች ከፍተኛ ነውር ይፈጽማሉ። ይሖዋ እንዲህ ያለውን የሃይማኖትና የፖለቲካ ሽርክና በሚፈጽሙ ሁሉ ላይ አፋጣኝ የቅጣት እርምጃ ይወስዳል።—ኢዩኤል 3:4-8
‘ጦርነትን ቀድሱ’
11. ይሖዋ ጠላቶቹን ወደ ጦርነት እንዲወጡ የሚገዳደረው እንዴት ነው?
11 ቀጥሎ ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚከተለውን የጦርነት ጥሪ ለአሕዛብ እንዲያቀርቡ እንዳዘዛቸው እናነባለን:- “ለሰልፍ ተዘጋጁ፤ ኃያላንን አስነሱ፤ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም።” (ኢዩኤል 3:9) ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጦርነት አዋጅ ነው። ለጽድቅ ጦርነት የተነገረ አዋጅ ነው። የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች ለሐሰት ፕሮፓጋንዳ መልስ ለመስጠትና ውሸትን በእውነት ለመከላከል በመንፈሳዊ የጦር እቃዎች ይጠቀማሉ። (2 ቆሮንቶስ 10:4፤ ኤፌሶን 6:17) በቅርቡ ‘ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ የተባለውን የአርማጌዶን የጽድቅ ጦርነት ይቀድሳል። የአምላክን ልዕልና የሚቃወሙትን ሁሉ ከምድር ገጽ ፈጽሞ ያስወግዳል። በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦቹ በጦርነቱ አይካፈሉም። ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ” ለማድረግ ቀጥቅጠዋል። (ኢሳይያስ 2:4) በአንፃሩ ግን ይሖዋ ብሔራት ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ይገዳደራቸዋል። “ማረሻችሁን ሰይፍ፣ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ” ይላቸዋል። (ኢዩኤል 3:10) ያለ የሌለ መሣሪያቸውን ይዘው እንዲዘምቱ ይጋብዛቸዋል። ይሁን እንጂ ጦርነቱም ሆነ ድሉ የይሖዋ ስለሆነ ብሔራት አይሳካላቸውም!
12, 13. (ሀ) ቀዝቃዛው ጦርነት ቢያበቃም ብዙ ብሔራት የጦረኛ ስሜት ያላቸው መሆኑን ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ብሔራት ያልተዘጋጁት ለየትኛው ነገር ነው?
12 በ1990ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ብሔራት ቀዝቃዛው ጦርነት እንዳበቃ ተናግረዋል። ታዲያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነኛ ግብ የሆነው ሰላምና ፀጥታ ተገኝቷልን? በፍጹም አልተገኘም! በቡሩንዲ፣ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣ በኢራቅ፣ በላይቤርያ፣ በሩዋንዳ፣ በሶማሊያና በቀድሞዋ ዩጎዝላቭያ በቅርብ ጊዜያት የተፈጸሙት ሁኔታዎች ምን ያሳዩናል? ኤርምያስ 6:14 እንደሚለው “ሰላም ሳይሆን:- ሰላም፣ ሰላም ይላሉ።”
13 በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የነበሩ ጦርነቶች ቢያቆሙም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት በጣም የተወሳሰቡ የጦር መሣሪያዎችን በማምረት እርስ በርሳቸው በመፎካከር ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ የኑክሊየር መሣሪያዎች ማከማቸታቸውን ቀጥለዋል። ሌሎች ደግሞ ብዙ ሕዝብ ሊያጠፉ የሚችሉ ኬሚካዊና ባክቴሪኦሎጂካዊ መሣሪያዎችን ያመርታሉ። እነዚህ ብሔራት አርማጌዶን ወደተባለው ምሳሌያዊ ቦታ ሲሰበሰቡ “ደካማውም:- እኔ ብርቱ ነኝ ይበል። እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፣ ቸኩላችሁ ኑ፣ ተሰብሰቡ” በማለት ይገዳደራቸዋል። እዚህ ላይ ኢዩኤል ጣልቃ በመግባት “አቤቱ፣ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ” በማለት ይሖዋን ይማጸናል።—ኢዩኤል 3:10, 11
ይሖዋ የራሱ የሆኑትን ይጠብቃል
14. የይሖዋ ኃያላን እነማን ናቸው?
14 የይሖዋ ኃያላን እነማን ናቸው? አምላካችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 280 ጊዜ ያህል ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ’ ተብሎ ተጠርቷል። (2 ነገሥት 3:14) ይህ ሠራዊት የይሖዋን ትእዛዝ ለመፈጸም በተጠንቀቅ የሚጠባበቀው የሰማይ መላእክት ጭፍራ ነው። ሶርያውያን ኤልሳዕን ለመያዝ ቢፈልጉም ለምን እንደማይሳካላቸው ይሖዋ የኤልሳዕን ሎሌ ዓይኖች እንዲከፈቱ በማድረግ አሳይቷል:- “እነሆም፣ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።” (2 ነገሥት 6:17) ኢየሱስ “ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት” እንዲልክለት አባቱን መጠየቅ ይችል እንደነበረ ተናግሯል። (ማቴዎስ 26:53) ኢየሱስ በአርማጌዶን የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ የሚያደርገውን ግልቢያ ሲገልጽ ራእይ እንዲህ ይላል:- “በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቁጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል።” (ራእይ 19:14, 15) ይህ ምሳሌያዊ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ‘ታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ መጥመቂያ’ ተብሎ ጉልህ በሆነ መንገድ ተገልጿል።—ራእይ 14:17-20
15. ይሖዋ በብሔራት ላይ የሚያነሣውን ጦርነት ኢዩኤል የገለጸው እንዴት ነው?
15 ታዲያ ይሖዋ የራሱን ኃያላን እንዲያወርድ ኢዩኤል ያቀረበውን ልመና የሚፈጽመው እንዴት ነው? በእነዚህ ሥዕላዊ ቃላት በተገለጸው መሠረት ነው:- “አሕዛብ ይነሱ፣ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ፤ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፤ ክፋታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈስሶአል። የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፣ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፣ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ።”—ኢዩኤል 3:12-16
16. ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን ከሚያስፈጽምባቸው ሰዎች መካከል እነማን ጭምር ይገኛሉ?
16 ኢዮሣፍጥ ማለት “ይሖዋ ፈራጅ ነው” ማለት እንደመሆኑ አምላካችን ይሖዋ የቅጣት እርምጃ በመውሰድ የራሱ ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ ያደርጋል። ትንቢቱ የሚፈረድባቸው ሰዎች ‘በፍርድ ሸለቆ ያሉ ብዙ ሕዝብ’ እንደሆኑ ይገልጻል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የሐሰት ሃይማኖት ደጋፊዎች ሆነው የቆዩ ሰዎች ቢኖሩ ከእነዚህ ብዙ ሕዝብ መካከል ይሆናሉ። በተጨማሪም በሁለተኛው መዝሙር ውስጥ የተገለጹት ‘ይሖዋን በፍርሐት ከማገልገል’ ይልቅ የዚህን ዓለም ብልሹ ሥርዓት የመረጡ ‘ብሔራት፣ ወገኖች፣ የምድር ነገሥታትና ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች’ ከሚጠፉት መካከል ይሆናሉ። ‘ልጁን ለመሳም’ ፈቃደኛ አይደሉም። (መዝሙር 2:1, 2, 11, 12 NW) ኢየሱስ የይሖዋ ተባባሪ ንጉሥ መሆኑን አይቀበሉም። ከዚህም በላይ ጥፋት እንዲወርድባቸው ምልክት ከሚደረግባቸው ሰዎች መካከል ይህ ታላቅ ግርማ የተጎናጸፈ ንጉሥ “ፍየሎች” ናቸው ብሎ የሚፈርድባቸውን ሰዎች ይጨምራል። (ማቴዎስ 25:33, 41) ይሖዋ በሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚጮህበት ጊዜ ሲደርስ የእርሱ ተባባሪ የሆነው የነገሥታት ንጉሥ ፍርዱን ለመፈጸም ይዘምታል። ሰማይና ምድር ይናወጣሉ! ይሁን እንጂ “እግዚአብሔር ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ” እንደሚሆን ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።—ኢዩኤል 3:16
17, 18. ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች እነማን ናቸው? ምንስ ሁኔታዎች አግኝተው ይደሰታሉ?
17 ራእይ 7:9-17 የኢየሱስ ደም ባለው ቤዛዊ ኃይል በማመናቸው ምክንያት ‘ከታላቁ መከራ በሕይወት ስለተረፉ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ይናገራል። በኢዩኤል ትንቢት የተገለጹት ብዙ ሕዝቦች በይሖዋ ቀን በፍርድ ሸለቆ የቅጣት እርምጃ ሲወሰድባቸው እነዚህ ግን ጥበቃ ይደረግላቸዋል። ኢዩኤል ከጥፋቱ ለሚተርፉት ሰዎች እንዲህ ይላል:- “እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን [ከፍ ያለው የአምልኮ ቦታው ማለት ነው] የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”—ኢዩኤል 3:17
18 ከዚያ በኋላ ትንቢቱ የሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ግዛት “የተቀደሰች ትሆናለች፣ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም” ይላል። (ኢዩኤል 3:17) ፍጥረት ሁሉ በንጹሕ አምልኮ አንድ ስለሚሆን በዚህ ሰማያዊ መንግሥት ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ክፍል እንግዶች አይኖሩም።
19. የአምላክ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜ ያላቸውን ገነታዊ ደስታ ኢዩኤል የገለጸው እንዴት ነው?
19 በአሁኑ ጊዜ እንኳን በምድር ላይ በሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች መካከል የተትረፈረፈ ሰላም ሰፍኗል። አንድ ሕዝብ ሆነው ከ230 በሚበልጡ አገሮችና ከ300 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች ፍርዱን በማወጅ ላይ ናቸው። ኢዩኤል ብልጽግናቸውን በሚከተሉት ውብ ትንቢታዊ ቃላት ገልጿል:- “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠባጥባሉ፣ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፣ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጎርፋሉ።” (ኢዩኤል 3:18) አዎን፣ ይሖዋ በምድር ላይ በሚኖሩ አወዳሾቹ ላይ አስደሳች በረከቶችንና ብልጽግና፣ እንዲሁም ውድ የሆነ የእውነት ምንጭ በብዛት ማፍሰሱን ይቀጥላል። የይሖዋ ልዕልና በፍርድ ሸለቆ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል። በተቤዣቸው ሕዝቦቹ መካከል ለዘላለም ሲኖር ሕይወት ደስታ የሞላበት ይሆናል።—ራእይ 21:3, 4
ታስታውሳለህን?
◻ በኢዮሣፍጥ ዘመን ይሖዋ ሕዝቡን ያዳነው እንዴት ነበር?
◻ በ“ፍርድ ሸለቆ” ውስጥ የቅጣት ፍርድ እንዲቀበሉ ይሖዋ የሚፈርድባቸው እነማንን ነው?
◻ የአምላክ ኃያላን እነማን ናቸው? በመጨረሻው ጦርነት ወቅትስ ምን ሚና ይኖራቸዋል?
◻ የታመኑ አምላኪዎች ምን ዓይነት ደስታ ያገኛሉ?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሁዳ ‘ሰልፉ የአምላክ እንጂ የአንተ ስላልሆነ አትፍራ’ ተብሎ ነበር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ‘ማረሻቸውን ሰይፍ ለማድረግ እንዲቀጠቅጡ’ በመንገር ጠላቶቹን ይገዳደራቸዋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ከታላቁ መከራ የሚተርፉ እጅግ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይናገራል