የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“በየቀኑም በገበያ”
ሐዋርያው ጳውሎስ የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ ሲል የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሟል። የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘት “በምኩራብ ከአይሁድና . . . በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር” ይነጋገር ነበር።—ሥራ 17:17
ይህን የመሰለው ቅንዓት ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ሆኗል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ምሥክሮች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ በቅንዓት ሲረዱ የተለያዩ ዓይነት ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ቀጥሎ የቀረበው ከአውስትራሊያ የተገኘ ተሞክሮ ይህንን ያሳያል።
ሲድ እና ሃሮልድ፣ ሲድኒ ውስጥ በአንድ የባቡር ጣቢያ አቅራቢያ በየተራ በየሳምንቱ ለአምስት ቀናት የተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ዘርግተው ያስተዋውቃሉ። በዚህ መንገድ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማካፈል ከጀመሩ ወደ አምስት ዓመት አካባቢ ሆኗቸዋል። የ95 ዓመቱ አዛውንት ሲድ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “መኪና መንዳት ያቆምኩት 87 ዓመት ሲሞላኝ ነበር። ለሕዝብ የሚሰጠው የምሥክርነት ሥራ ያስደስተኝ ስለነበር በጉዳዩ አዘንኩ። አንድ ቀን ካቱምባ ውስጥ ጎብኚዎች በሚበዙበት ኤኮ ፖይንት በተባለ ቦታ አቅራቢያ ሳለሁ አንድ ሰዓሊ የተፈጥሮ ውበት የሚያንፀባርቁ ስዕሎችን ዘርግቶ ሲሸጥ ተመለከትኩ። ስዕሎቹን ተመለከትኩና በአእምሮዬ ‘በአገልግሎት ቦርሳዬ ውስጥ ከእነዚህ ይልቅ የተሻሉ ስዕሎች አሉኝ፤ ያውም በጣም በርካሽ ዋጋ የሚገኙ!’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ እንደጠረጴዛ ያለ ነገር ለማዘጋጀትና ጎብኚዎች በሚበዙበት ቦታ ለአላፊ አግዳሚው የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሰራጩአቸውን ማራኪ ስዕሎች ያሏቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለማበርከት ወሰንኩ።
“ከአራት ዓመት በፊት ቦታ ቀይሬ ወደ ሲድኒ ሄድኩ፤ በዚያ ሃሮልድ ከእኔ ጋር ይሠራ ጀመር። ጽሑፍ ዘርግተን በምናስተዋውቅበት ቦታ የምንሆነውና በየጉባኤዎቻችን የምናገለግለው በየተራ ነበር። የሰማንያ ሦስት ዓመቱ ሃሮልድ እንዲህ ይላል:- “ከሰኞ እስከ ዓርብ ባለው ጊዜ ውስጥ ቤታቸው የሚገኙት ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ በዚህ መንገድ የመንግሥቱን መልእክት ማካፈላችን ሰዎች በሚገኙበት ቦታ እንድንገኝ አስችሎናል። የተሻለ ውጤት ማግኘታችንም እሙን ነው። እኛ የምናበረክተው የጽሑፍ መጠን በአገራችን ውስጥ በጣም ከፍተኛ ነው።”
“ምንም እንኳ ባለፉት ዓመታት አራት ወይም አምስት የተለያዩ ቦታዎች ብንቀያይርም ሰዎች ማን መሆናችንንና የት ቦታ እንደምንገኝ ለማወቅ ጊዜ አይወስድባቸውም” ሲል ሲድ ተናግሯል። “አንዳንድ ሰዎች ጽሑፍ ለማግኘት ወደ እኛ ይመጣሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲመለሱላቸው የሚፈልጉ ጥያቄዎች አሏቸው። አንዳንዶች ደግሞ ለጥቂት ደቂቃዎች ለማውራት ብለው ይመጣሉ። ተመላልሶ መጠየቅ የማደርግላቸው ሰዎች ወደ እኔ የሚመጡት በዚህ ጊዜ ብቻ ነው” ሲል ሣቅ እያለ ገልጿል።
ሃሮልድ በማከል “ብዙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ፍላጎት አላቸው” ብሏል። “ከእኛ ጽሑፍ በማግኘታቸውና ለጥያቄዎቻቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ መስጠት በመቻላችን ምክንያት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አራት ሰዎች ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ማጥናት ጀምረዋል። እነዚህን የመሳሰሉ ተሞክሮዎች በጣም ያበረታቱናል።”
እንደ ሲድ እና ሃሮልድ እንዲሁም በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አስፈላጊ የሆነ መልእክታቸውን ለማዳረስ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚቻለውን ዘዴ ሁሉ ይጠቀማሉ። በዚህም መንገድ ‘ወንጌሉ’ “በዓለም ሁሉ” መሰበኩን ቀጥሏል።—ማቴዎስ 24:14