የፍትሕ መጓደል ሊወገድ የማይችል ነውን?
“አሁንም ቢሆን ሰዎች ልባቸው ጥሩ እንደሆነ አምናለሁ። ሆኖም በብጥብጥ፣ በችግርና በሞት በተዋቀረ መሠረት ላይ ተስፋዬን ልገነባ አልቻልኩም።”—አን ፍራንክ
እነዚህ ልብ የሚነኩ ቃላት አን ፍራንክ የምትባል አንዲት የ15 ዓመት አይሁዳዊት ወጣት ከመሞቷ ከጥቂት ጊዜ በፊት በግል ማስታወሻዋ ላይ የጻፈቻቸው ነበሩ። ቤተሰቧ በአምስተርዳም በአንድ ከጣሪያ ሥር ባለ ክፍል ውስጥ ከሁለት ዓመታት በላይ ተሸሽጎ ነበር። አንድ ሰላይ ያሉበትን ቦታ ለናዚዎች በተናገረ ጊዜ የተሻለ ሕይወት ለማየት የነበራት ተስፋ ጨለመ። በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ1945 አን በቤርገን ቤልዘን ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ እንዳለች በተስቦ በሽታ ሞተች። ሌሎች ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ አይሁዳውያንም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባቸዋል።
ሂትለር አንድን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የነበረው ዲያብሎሳዊ ውጥን ባለንበት መቶ ዘመን ከተፈጸሙት የዘር መድሎዎች ሁሉ የከፋው ሊሆን ቢችልም ብቸኛው ግን አይደለም። በ1994 በሩዋንዳ ከግማሽ ሚልዮን የሚልቁ ቱትሲዎች የተጨፈጨፉት “የተለየ” ጎሣ አባላት በመሆናቸው ብቻ ነበር። እንዲሁም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በዘር ማጥፋት ዘመቻ ሳቢያ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ አርመናውያን አልቀዋል።
የፍትሕ መጓደል አስቀያሚ ገጽታዎች
የፍትሕ መጓደል ሲባል የዘር ጭፍጨፋ ማለት ብቻ አይደለም። ማኅበራዊ አድልዎ አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የሰው ዘር ለዕድሜ ልክ ድህነት ዳርጓል። ከዚህም በላይ አንቲ-ስሌቨሪ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ከ200,000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በባርነት ሥር እንደሚገኙ ተናግሯል። ዛሬ በዓለም ላይ በየትኛውም የታሪክ ወቅት ከነበሩት የሚበልጡ ባሪያዎች ሳይኖሩ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች በግልጽ ጨረታ አይሸጡ ይሆናል፤ የሚሠሩበት ሁኔታ ግን በአብዛኛው በጥንት ዘመን ከነበሩት ከብዙዎቹ ባሪያዎች ይበልጥ የከፋ ነው።
በሕግ አንፃር የሚፈጸም የፍትሕ መጓደል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያላቸውን መሠረታዊ መብት ይገፍፋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ1996 ባወጣው ሪፖርት ላይ “በየቀኑ ለማለት ይቻላል በዓለም ውስጥ በሆነ ቦታ ላይ ጭካኔ የተሞላበት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ይፈጸማል” ብሏል። “ይበልጥ ተጠቂ የሆኑት በድህነትና በችግር የሚማቅቁት፣ በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና ስደተኞች ናቸው።” ሪፖርቱ እንዳመለከተው “በአንዳንድ አገሮች መንግሥታዊ ተቋማት በአብዛኛው በመፈራረሳቸው ደካማውን ከጉልበተኛው ለመጠበቅ የሚያስችል ምንም ሕጋዊ ሥልጣን የለም።”
በ1996 ከመቶ በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ታግተው ተሠቃይተዋል። እንዲሁም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በደኅንነት ኃይሎች ወይም በአሸባሪ ቡድኖች ታፍነው በመወሰዳቸው የገቡበት አይታወቅም። ብዙዎቹ ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።
ጦርነት ሲባል ፍትሕ የጎደለው ነገር መሆኑ ምንም ባያጠያይቅም በዛሬው ጊዜ ሁኔታው ይበልጥ እየከፋ ሄዷል። ዘመናዊው ጦርነት ሴቶችንና ሕፃናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ቦታ ሳይመርጡ ከተሞችን በቦምብ በመደብደብ ብቻ የሚከሰት ነገር አይደለም። በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ የግዳጅ ወሲብ መፈጸም የወታደራዊ እንቅስቃሴ አንዱ ክፍል ሆኗል፤ እንዲሁም በርካታ የዓማፂያን ቡድኖች ልጆችን በኃይል ጠልፈው በመውሰድ ገዳዮች እንዲሆኑ ያሰለጥኗቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት “የትጥቅ ትግል በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ “ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ የዓለም ሕዝብ በሚያሳዝን ሁኔታ የሥነ ምግባር አቋሙ እየላሸቀ መጥቷል” ብሏል።
የሰዎች የሥነ ምግባር አቋም መላሸቅ በዘር፣ በማኅበራዊ፣ በሕግም ሆነ በወታደራዊ ጉዳዮች አኳያ የፍትሕ መጓደል እንዲንሰራፋ አድርጓል። በእርግጥ ይህ አዲስ ነገር አይደለም። ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት አንድ ዕብራዊ ነቢይ እንዲህ ሲል ቅሬታውን ገልጿል:- “ሕግ ላልቶአል፣ ፍትሕም ተዛብቶአል፤ ፍርድም በመጣመሙ ምክንያት ኃጢአተኞች ደጋግ ሰዎችን ከብበው ያስጨንቃሉ።” (ዕንባቆም 1:4 የ1980 ትርጉም) የፍትሕ መጓደል ምንጊዜም ተስፋፍቶ ይገኝ የነበረ ቢሆንም 20ኛው መቶ ዘመን ግን የፍትሕ መጓደል ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ ነው።
የፍትሕ መጓደል አሳሳቢ ነገር ነውን?
የፍትሕ መጓደል በተለይ በራስህ ላይ ሲፈጸም ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ትገነዘባለህ። አብዛኛው የሰው ዘር ያለውን በደስታ የመኖር መብት ስለሚነጥቅ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን ስለሚቀሰቅስና እነዚህ ደግሞ በተራቸው የፍትሕ መጓደል እንደተቀጣጠለ እንዲቀጥል ስለሚያደርጉ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው።
ሰላምና ደስታ ከፍትሕ ጋር በማይነጣጠሉበት ሁኔታ የተሳሰሩ ሲሆኑ የፍትሕ መጓደል ግን ተስፋን ያጨልማል እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ አመለካከት እንዳይኖር ያደርጋል። አን ፍራንክ ከደረሰባት አሳዛኝ ሁኔታ እንደተረዳችው ሰዎች ተስፋቸውን በብጥብጥ፣ በችግርና በሞት በተዋቀረ መሠረት ላይ ሊገነቡ አይችሉም። ልክ እንደ እሷ ሁላችንም የተሻለ ነገር እንዲመጣ እንመኛለን።
ይህ ፍላጎት ቅን ልብ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ለሰብዓዊው ኅብረተሰብ በተወሰነ ደረጃ ፍትሕ ለማስፈን እንዲጥሩ አነሳስቷቸዋል። እንዲያውም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ በ1948 የጸደቀው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ደንብ እንደሚከተለው ይላል:- “ሰዎች ሁሉ ነፃና እኩል ክብርና መብት ያላቸው ሆነው ተወልደዋል። የሚያስብ አእምሮና ሕሊና ያላቸው ስለሆኑ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ ይገባል።”
ይህ ጥሩ ሐሳብ ቢሆንም የሰው ልጅ ሰዎች ሁሉ እኩል መብት የሚያገኙበትና እርስ በርሳቸው በወንድማማች መንፈስ የሚተያዩበት ፍትሕ የሰፈነበት ኅብረተሰብ ለማምጣት የነበረው ጉጉት እስከ አሁን ድረስ ግቡን ሊመታ አልቻለም። የተባበሩት መንግሥታት ደንብ በመግቢያው ላይ እንደሚያመለክተው የዚህ ዓላማ ከግብ መድረስ “በዓለም ላይ ነፃነት፣ ፍትሕና ሰላም እንዲሰፍን መሠረት ይጥላል።”
የፍትሕ መጓደል በሰብዓዊው ሕብረተሰብ ውስጥ ሥር የሰደደና በፍጹም ሊወገድ የማይችል ነገር ነውን? ወይስ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለሰላም የሚሆን ጠንካራ መሠረት መጣል ይቻል ይሆን? የሚቻል ከሆነ መሠረቱን መጣልና ሁሉም እንዲጠቀሙ ማድረግ የሚችለው ማን ነው?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
UPI/Corbis-Bettmann