የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ተቃዋሚ የነበረ ሰው እውነትን ተማረ
ስለ ላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በዜና ማሰራጫዎች ብዙ ተዘግቧል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ እንዲሁም ከዚያ የሚልቁት ተፈናቅለዋል። ይህን የመሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ቀጥሎ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን መቀበላቸውን ቀጥለዋል።
ጄምስ ከአሥር ዓመቱ አንስቶ በሉተራን ቤተ ክርስቲያን ተምሯል። ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታሳትመው ጋዜጣ አዘጋጅ በነበረበት ጊዜ አጋጣሚውን የይሖዋ ምሥክሮችን የሚነቅፍ ነገር እየጻፈ ለማውጣት ተጠቅሞበታል። እንዲህ ያደርግ የነበረው ግን ጭራሽ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቶ ሳያውቅ ነው።
ከጊዜ በኋላ ጄምስ የቤተ ክርስቲያኑ ጋዜጣ አዘጋጅ መሆኑን አቆመና የተዋጣለት የሞቴል ባለንብረት ሆነ። አንድ ቀን በሞቴሉ እንግዳ መቀበያ አካባቢ ተቀምጦ ሳለ ጥሩ አለባበስ ያላቸው ሁለት እህቶች ቀርበው አነጋገሩት። ሥርዓታማ የሆነ አለባበሳቸውን ተመልክቶ እንዲገቡ ጋበዛቸው። ሆኖም የመጡበትን ዓላማ ሲገልጹለት “ሥራ በጣም ስለሚበዛብኝ ለመነጋገር ጊዜ የለኝም” አላቸው። ምሥክሮቹ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ኮንትራት እንዲገባ ሐሳብ ሲያቀርቡለት ከእነርሱ ለመገላገል ስለፈለገ ብቻ በነገሩ ተስማማ። መጽሔቶቹ ለ12 ወራት ያክል በአድራሻው ይመጡለት የነበረ ቢሆንም አንድም ጊዜ ከታሸጉበት ወረቀት እንኳ አውጥቶ ሳያያቸው በአንድ ፕላስቲክ ቦርሳ ውስጥ ይጨምራቸው ነበር።
የእርስ በርስ ጦርነቱ እየተፋፋመ መጣ። በመሆኑም ጄምስ ጥቃት እንደተጀመረ ወዲያውኑ ሸሽቶ ለማምለጥ እንዲችል በቦርሳ ውስጥ ገንዘብና ውድ ንብረቶችን ከትቶ አሰናዳ። አንድ ቀን ጠዋት ከጓሮው በር አጠገብ የእጅ ቦምብ ፈነዳ፤ በዚህ ጊዜ በድንጋጤ ቦርሳውን አፈፍ አድርጎ ሕይወቱን ለማዳን እግሬ አውጪኝ አለ። በሺዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ሲቪሎች ጋር በመሆን በሚሸሹበት ጊዜ በርካታ የፍተሻ ጣቢያዎችን አልፈው ይሄዱ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ምንም ጥፋት የሌለባቸው ሰላማውያን ሰዎች በግፍ ንብረታቸውን ይዘረፉና ይገደሉ ነበር።
ጄምስ በመጀመሪያው የፍተሻ ጣቢያ ላይ ጥቂት ጥያቄዎች ከቀረቡለት በኋላ ቦርሳውን እንዲከፍት ታዘዘ። ቦርሳውን ከፍቶ በውስጡ የያዘውን ነገር ሲመለከት ዓይኑን ማመን አቃተው። የያዘው ቦርሳ ውድ ንብረቶቹን ያስቀመጠበት አለመሆኑን ሲያይ ክው አለ። ለካስ በድንጋጤ ይዞት የሸሸው ያልተከፈቱት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች የተጠራቀሙበትን ቦርሳ ነበር። ይሁን እንጂ ወታደሩ መጽሔቶቹን ከተመለከተና ከአድራሻው ላይ ስሙን ካነበበ በኋላ “አሃ፣ አንተ የይሖዋ ምሥክር ነህ። እናንተ እንደማትዋሹ ስለምናውቅ ጥረታችን እናንተን ለመያዝ አይደለም” ሲል ተናገረ። ወታደሩ ከቦርሳው ውስጥ ጥቂት መጽሔቶችን ከወሰደ በኋላ ጄምስን መንገዱን እንዲቀጥል ነገረው።
በተለያዩ ዘጠኝ የፍተሻ ጣቢያዎች ተመሳሳይ ነገር አጋጠመው። ሁሉም አዛዦች ጄምስ የይሖዋ ምሥክር ስለመሰላቸው ምንም ጉዳት ሳይደርስበት እንዲያልፍ ፈቀዱለት። በዚህ ጊዜ ጄምስ ውድ ንብረቶቹን ይዞ ባለመምጣቱ በጣም ተደሰተ፤ ምክንያቱም ያለጥርጥር ለንብረቱ ብለው ይገድሉት እንደነበር ካየው ሁኔታ ተገንዝቧል።
ከዚያም የመጨረሻውና እጅግ አስፈሪ የሆነው ፍተሻ ጣቢያ ሲደርስ በአካባቢው በርካታ አስከሬኖች በማየቱ ከፍተኛ ፍርሃት አደረበት። ከፍርሃቱ የተነሳ ይሖዋን ተማጸነው። አምላክ ከዚህ የግድያ ቀጣና በሕይወት እንዲተርፍ ከረዳው በቀሪው የሕይወት ዘመን በሙሉ እሱን እንደሚያገለግለው በጸሎት ገለጸ።
ጄምስ ቦርሳውን ከፍቶ ለወታደሮቹ አሳያቸው፤ በዚህ ጊዜም እንደገና “እኛ የምንፈልገው እነዚህን ሰዎች አይደለም” ብለው ተናገሩ። ከዚያም ወደ እርሱ እየተመለከቱ “ከኮረብታው ሥር የሚኖር ወንድምህ አለ፤ እርሱ ጋ ሂድና በዚያ ቆይ” አሉት። በዚህ ጊዜ ጄምስ ለይሖዋ ምሥክሮች የነበረው አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ጄምስ ወዲያውኑ ከዚህ ወንድም ጋር ተገናኘና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህa በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ተደረገ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ በአካባቢው ጥቃት ስለተሰነዘረ ከዚያም ሸሽቶ ለመሄድ ተገደደ። በዚህ ጊዜ ጄምስ ወደ ጫካ ሲሸሽ የያዘው ነገር ቢኖር ለዘላለም መኖር መጽሐፉን ብቻ ነበር! ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሳይገናኝ ባሳለፋቸው 11 ወራት ውስጥ መጽሐፉን አምስት ጊዜ ከዳር እስከ ዳር አጠናው። መጨረሻ ላይ ወደ ከተማው ተመልሶ መሄድ በቻለ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ቀጠለና ፈጣን እድገት አደረገ። ከአጭር ጊዜ በኋላ የተጠመቀ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር በታማኝነት በማገልገል ላይ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ።