ጄሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ብዙዎችን ያወዛገበ ሰው
ሚያዝያ 8, 1546 የተካሄደው የትሬንት ጉባኤ የላቲኑ ቩልጌት ትርጉም “[በካቶሊካዊት] ቤተ ክርስቲያን ጸድቋል . . . ከእንግዲህ ማንም ሰው በምንም ዓይነት ምክንያት ይህን ትርጉም ጨርሶ አልቀበልም ሊል ይቅርና ለመቀበል ሊያቅማማ እንኳን አይገባውም” ሲል ደንግጓል። የቩልጌት ትርጉም የተጠናቀቀው ከዚህ ጊዜ አንድ ሺህ ዓመታት ቀደም ብሎ ቢሆንም ትርጉሙም ሆነ ተርጓሚው ጄሮም ለረጅም ዘመን የውዝግብ ምክንያት ሆነው ኖረዋል። ጄሮም ማን ነበር? እርሱም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ አወዛጋቢ የሆኑት ለምንድን ነው? የእርሱስ ሥራ ዛሬ ባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?
ወደ ምሁርነት ለመድረስ ያደረገው መሻሻል
የጄሮም የላቲን ስም ዩሴቢየስ ሂራንመስ ነው። የተወለደው በ346 እዘአ በዛሬው የኢጣሊያና የስሎቫኒያ ድንበር አቅራቢያ ትገኝ በነበረችውና የሮማ ግዛት በሆነችው በዳልማሺያ ባለችው በስትሪደን ነው።a ወላጆቹ በመጠኑም ቢሆን ደህና ኑሮ ስለነበራቸው በሮም ስመ ጥር ከነበረው የስዋሰው ምሁር ዶናተስ ዘንድ እንዲማር አድርገውት ነበርና የገንዘብን ጥቅም የቀመሰው ገና በልጅነቱ ነበር። ጄሮም የስዋሰው፣ ንግግር የማሳመርና የፍልስፍና ተሰጥዎ ያለው ተማሪ ነበር። በዚህ ወቅት ግሪክኛ ማጥናትም ጀምሮ ነበር።
ጄሮም በ366 እዘአ ከሮም ከወጣ በኋላ በብዙ ቦታዎች ሲንከራተት ቆይቶ በመጨረሻ በአክዋላ ኢጣሊያ መኖር ጀመረ። ከብሕትውና ንድፈ ሐሳብ ጋር የተዋወቀው በዚህ ቦታ ሳለ ነበር። በዚህ ራስን ሙሉ በሙሉ የመካድ ሐሳብ የተማረከው ጄሮምና ሌሎችም ወዳጆቹ በቡድን ሆነው የብሕትውናን የሕይወት ጎዳና በመኮትኮት ጥቂት ዓመታት አሳልፈዋል።
በ373 እዘአ ግን በአንድ ያልታወቀ ምክንያት ተረብሸው ቡድኑ ተበተነ። ግራ የተጋባው ጄሮምም በምሥራቅ በኩል በቢታኒያ፣ በገላትያና በኪልቅያ ሲንከራተት ቆይቶ በመጨረሻው ወደ ሶሪያ አንጾኪያ ሄደ።
ረጅም የሆነው ጉዞ ኃይሉን አሟጦበት ነበር። የተዳከመውና ጤንነቱ የተቃወሰው ጄሮም ኃይለኛ ትኩሳት ይዞት ነበር። “አቤቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አንተ በተዓምር ባደረሰኝ። ያችው ጤናማ እያለሁም ደካማ የሆነችው ሰውነቴ አሁን ይባስ ደቅቃለች” ሲል ለአንድ ጓደኛው ጽፏል።
ሕመሙ፣ ብቸኝነቱና በውስጡ ያለው የተመሰቃቀለ ሐሳብ እንዳይበቃው ደግሞ ጄሮም ሌላ ችግር ማለትም መንፈሳዊ ችግር ገጠመው። በሕልሙ ‘ተጎትቶ በአምላክ ፍርድ ወንበር ፊት’ ሲቀርብ ተመለከተ። ጄሮም ማንነቱን እንዲገልጽ በተጠየቀ ጊዜ “ክርስቲያን ነኝ” ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ጠያቂው “ዋሽተሃል፤ አንተ የሲሴሮ ተከታይ እንጂ የክርስቶስ ተከታይ አይደለህም” ሲል መለሰለት።
እስከዚያ ጊዜ ድረስ የጄሮም ምኞት የጥንቶቹን አረማዊ ሥነ ጽሑፎች ማጥናት እንጂ የአምላክን ቃል ማጥናት አልነበረም። “በሕሊናዬ እሳት ተሰቃየሁ” ሲል ገልጿል። ጄሮም ስህተቱን ለማረም በሕልሙ “አቤቱ ጌታ ሆይ፣ ከአሁን ወዲህ ዓለማዊ መጻሕፍት በእጄ ቢገቡ ወይም ባነባቸው አንተን እንደካድኩ ይቆጠር” ሲል ቃል ገብቷል።
ከጊዜ በኋላ ግን ጄሮም በሕልም ለፈጸምኩት ቃለ መሐላ በተጠያቂነት መያዝ የለብኝም ሲል ተከራክሯል። የሆነ ሆኖ ቢያንስ በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ የገባውን ቃል ለመፈጸም ቆርጦ ነበር። በመሆኑም ጄሮም ከአንጾኪያ ወጥቶ በሶሪያ በረሃ በካልኪስ ለብቻው መኖርን መረጠ። እንደ ባሕታዊ በመኖር መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን በማጥናት ራሱን አስጠምዶ ነበር። ጄሮም “የአምላክን መጻሕፍት የማነብበው ካሁን ቀደም የሰዎችን መጻሕፍት ካነበብኩበት እጅግ በሚልቅ ቅንዓት ነው” ሲል ተናግሯል። የአካባቢውን የሲሪያክ ቋንቋ ከመማሩም በላይ ወደ ክርስትና በተለወጠ አንድ አይሁዳዊ ረዳትነት የዕብራይስጥ ቋንቋ ማጥናት ጀምሮ ነበር።
ከሊቀ ጳጳሱ የተቀበለው ተልዕኮ
አምስት ዓመት ከሚያህል የምንኩስና ኑሮ በኋላ ጄሮም በጥናቱ ለመቀጠል ወደ አንጾኪያ ተመለሰ። ይሁን እንጂ እዚያ ሲደርስ ቤተ ክርስቲያኒቱ በጣም ተከፋፍላ ነበር። እርግጥ ጄሮም ገና በበረሃ እያለም “ቤተ ክርስቲያኒቱ በሦስት ጎራ ተከፍላለች፤ ሦስቱም ደግም ለየራሳቸው ሊያደርጉኝ ይፈልጋሉ” ሲል ምን ቢያደርግ እንደሚሻል ሊቀ ጳጳስ ዳማሰስ ምክር እንዲሰጡት አቤት ብሎ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ግን የአንጾኪያ ጳጳሳት ነን ይሉ ከነበሩት ከሦስቱ ሰዎች ከአንዱ ማለትም ከፖሊነስ ጋር ለመወገን ወሰነ። ጄሮም ከፖሊነስ ሹመቱን ለመቀበል የሚስማማው ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉለት ብቻ እንደሆነ ገልጾ ነበር። አንደኛው የምንኩስና ምኞቱን ይገፋበት ዘንድ ከተፈቀደለት ነው። ሁለተኛ ደግሞ ለአንድ የተወሰነ ቤተ ክርስቲያን የቅስና አገልግሎት እንዲያቀርብ ምንም ዓይነት ግዴታ ውስጥ የማይገባ ከሆነ ብቻ መሆኑ ተናግሯል።
ጄሮም በ381 እዘአ ከፖሊነስ ጋር ወደ ቁስጥንጥንያ ጉባኤ የሄደ ሲሆን ከዚያም በኋላ በዚያው አብሮት ወደ ሮም ተጉዟል። ሊቀ ጳጳሱ ዳማሰስ የጄሮምን ምሁራዊ ችሎታና የቋንቋ ክሕሎት ለማስተዋል ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ጄሮም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የዳማሰስ የግል ጸሐፊ ሆኖ የመሥራት ከፍተኛ ክብር ያለው ቦታ አገኘ።
ጄሮም ጸሐፊ ከሆነ በኋላም ቢሆን የሚያወዛግቡ ነገሮች ከማድረግ ወደ ኋላ አላለም። እንዲያውም ያየውን ነገር የሚያልፍ አይመስልም። ለምሳሌ ያህል ቅንጦት በበዛበት በሊቀ ጳጳሱ ቤተ መንግሥት የብሕትውና ኑሮ መኖሩን ቀጥሎ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የእርሱን ቁጥብ አኗኗር በማወደስና የካህናቱን ዓለማዊ ቅንጦት በግልጽ በማውገዙ ጄሮም ብዙ ጠላቶች አፍርቷል።
ጄሮምን የሚተቹት ሰዎች ቢኖሩም የሊቀ ጳጳሱን ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ነበር። ሊቀ ጳጳሱ ጄሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ምርምሩ እንዲቀጥል የሚያበረታቱበት ጥሩ ምክንያት ነበራቸው። በወቅቱ ሥራ ላይ የዋሉ በርካታ የላቲን ትርጉሞች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ግን በግዴለሽነት የተተረጎሙ ሲሆኑ በጣም ጉልህ ስህተቶች ነበሩባቸው። ሌላው ለዳማሰስ አሳሳቢ የነበረው ነገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ምሥራቃዊና ምዕራባዊ ግዛት እየከፋፈለ መምጣቱ ነበር። በምሥራቅ ካሉት መካከል ላቲን የሚያውቁት ጥቂት ሲሆኑ በምዕራብ ካሉት ደግሞ ግሪክኛ የሚያውቁት እጅግ ጥቂት ነበሩ።
በመሆኑም ሊቀ ጳጳስ ዳማሰስ የወንጌሎች አዲስ የላቲን ትርጉም እንዲሠራ ጓጉተው ነበር። ዳማሰስ የፈለጉት የመጀመሪያውን ግሪክኛ በትክክል የሚያንጸባርቅ ነገር ግን ማራኪና ግልጽ በሆነ ላቲን የተቀመጠ ትርጉም እንዲዘጋጅ ነው። እንዲህ ያለውን ትርጉም ሊያዘጋጁ ከሚችሉት ጥቂት ምሁራን መካከል አንዱ ደግሞ ጄሮም ነበር። የግሪክ፣ ላቲንና ሲሪያክ ቋንቋዎችን ጠንቅቆ የሚያውቀውና በቂ የዕብራይስጥ ቋንቋ እውቀት የነበረው ጄሮም ለዚህ ሥራ ሙሉ ብቃት ነበረው። በመሆኑም ጄሮም ከዳማሰስ የተሰጠውን ተልዕኮ ተቀብሎ የሚቀጥሉትን ከ20 የሚበልጡ ዓመታት የሚፈጀውን ፕሮጄክት ተያያዘው።
ውዝግቡ እየተካረረ ሄደ
ጄሮም ወንጌሎቹን የተረጎመው በፍጥነት ቢሆንም ግልጽ የሆነና ምሁራዊ ዘዴ ተከትሏል። በወቅቱ የነበሩትን የግሪክኛ ቅጂዎች በሙሉ በማወዳደር ከግሪክኛው ጽሑፍ ጋር እንዲቀራረብ ለማድረግ ሲል በላቲን ጽሑፉ ስልትም ሆነ ይዘት ላይ ማስተካከያዎችን አድርጓል።
የጄሮም የአራቱ ወንጌሎች ትርጉም በግሪክ ሰፕቱጀንት ላይ እንደተመሠረተው የላቲኑ መዝሙረ ዳዊት እትሙ በአብዛኛዎቹ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል። ያም ሆኖ ግን የሚነቅፉት አልጠፉም። ጄሮም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንዳንድ የተናቁ ፍጥረታት የጥንቶቹን አዋቂዎችና የመላውን ዓለም ሐሳብ በመቃወም በወንጌል ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ሐሳቦች ለማረም እንደሞከርኩ አድርገው በነገር ያዋክቡኛል።” እንዲህ ያለው ውግዘት ሊቀ ጳጳሱ ዳማሰስ በ384 እዘአ ከሞቱ በኋላ እየከረረ ሄዶ ነበር። ጄሮም ከአዲሱ ሊቀ ጳጳስ ጋር የነበረው ግንኙነት እምብዛም ስለነበር ከሮም ለመውጣት ወሰነ። አሁንም ወደ ምሥራቅ አቀና።
የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁር ለመሆን ያደረገው መሻሻል
በ386 እዘአ ጄሮም የቀረውን የሕይወት ዘመኑን ባሳለፈበት በቤተ ልሔም ተቀመጠ። የመኳንንት ቤተሰብ የሆነችውን ባለጠጋዋን ሴት ፓውላን ጨምሮ ጥቂት ታማኝ ተከታዮች ነበሩት። ፓውላ ከጄሮም ስብከት የተነሣ የምንኩስና ኑሮ ጀምራ ነበር። በእርሷ የገንዘብ ድጋፍና በጄሮም አመራር አንድ ገዳም ተቋቁሞ ነበር። በዚያ ሆኖ በምሁራዊ ሥራው በመግፋት በሕይወቱ የደከመበትን ታላቅ ሥራ ለማጠናቀቅ ችሏል።
ጄሮም በፍልስጤም ምድር መኖሩ የዕብራይስጥ ቋንቋ ችሎታውን እንዲያሻሽል አጋጣሚ ሰጥቶታል። ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑትን የቋንቋውን ዘርፎች እንዲያስተውል ይረዱት ዘንድ በርካታ አይሁዳውያን አስተማሪዎች ቀጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ የአስተማሪ እርዳታ እያለም እንኳ ቀላል አልነበረም። ጄሮም የጥብርያዶሱን አስተማሪውን ባራኒናስን በሚመለከት “ባራኒናስ ጨለማን ተገን እያደረገ መጥቶ እንዲያስተምረኝ ስል ያልደረሰብኝ ችግርና ያላወጣሁት ወጪ አልነበረም” ብሏል። በሌሊት የሚያጠኑት ለምን ነበር? ባራኒናስ ከአንድ “ክርስቲያን” ጋር ለሚፈጥረው ቅርርብ የአይሁድ ማኅበረሰብ ያለውን አመለካከት ስለሚያውቅ ፈርቶ ነበር!
በጄሮም ዘመን የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚናገሩ አሕዛብ የጉሮሮ ድምፆችን በትክክል ስለማይጠሩ አይሁዶች ብዙ ጊዜ ያሾፉባቸው ነበር። ያም ሆኖ ግን ጄሮም ከብዙ ጥረት በኋላ እነዚህን ድምፆች ሊለምዳቸው ችሏል። በተጨማሪም ጄሮም ብዙ የዕብራይስጥ ቃላትን በላቲን ሆሄያት ጽፏል። ይህም ቃላቱን እንዲያስታውሳቸው ብቻ ሳይሆን በጊዜው የነበረውን የዕብራይስጥ አደማመፅ ጠብቆ ለማቆየትም ረድቶታል።
የጄሮም ከፍተኛው ውዝግብ
ሊቀ ጳጳስ ዳማሰስ፣ ጄሮም ምን ያህሉን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲተረጉም እንደፈለጉ ግልጽ አልነበረም። ሆኖም ጄሮም ጉዳዩን እንዴት እንደተመለከተው የሚያጠራጥር ነገር የለም። ጄሮም ትኩረትን ሁሉ እዚያ ላይ አድርጎና ቆርጦ ተነሥቶ ነበር። በውስጡ የነበረው ምኞት “ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚጠቅምና ለትውልድ ለመተላለፍ የሚበቃ” ሥራ ማከናወን ነበር። በመሆኑም የመላውን መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ የላቲን ትርጉም ለማዘጋጀት ቆርጦ ነበር።
ጄሮም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመተርጎም መሠረት ለማድረግ ያሰበው የሴፕቱጀንትን ትርጉም ነበር። ይህ በመጀመሪያ በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የግሪክኛ ትርጉም በብዙዎች ዘንድ በቀጥታ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ ተደርጎ ይታይ ነበር። በመሆኑም ሰፕቱጀንት በወቅቱ በነበሩት ግሪክኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች ዘንድ በሰፊው ይሠራበት ነበር።
ይሁንና ጄሮም በሥራው እየገፋ ሲሄድ በግሪክኛ ቅጂዎችም መካከል በላቲን ጽሑፎች እንደገጠመው ዓይነት አንዳንድ እርስ በርሳቸው የማይደጋገፉ ነገሮች አግኝቷል። ይህ ጄሮም ተስፋ እንዲቆርጥ የሚፈታተነው ሌላ ችግር ነበር። በመጨረሻ አስተማማኝ የሆነ ትርጉም ለማዘጋጀት ከፍተኛ አድናቆት የተቸረውን የሰፕቱጀንት ትርጉም ጨምሮ የግሪክኛ ቅጂዎችን በመተው በቀጥታ ወደ መጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥ ጽሑፎች መሄድ እንዳለበት ወሰነ።
ይህ ውሳኔ ተቃውሞ አስነሣ። አንዳንዶችም ጄሮምን ጥቅሱን የሚያጣምም፣ አምላክን የማያከብር፣ ለአይሁዶች ሲል የቤተ ክርስቲያንን ወግ የሚተው ብለውታል። በወቅቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ግንባር ቀደም ሃይማኖታዊ ምሁር የሆነው አውጉስቲን ሳይቀር ጄሮም ወደ ሰፕቱጀንት ትርጉም እንዲመለስ እንዲህ ሲል ተማጽኖታል:- “የአንተ ትርጉም በብዙ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ መነበብ ከጀመረ በቅዱሳን ጽሑፎች ንባብ በላቲንና በግሪክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ልዩነት ተፈጥሮ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ነገር ይሆናል።”
አዎን፣ የአውጉስቲን ፍርሃት በምዕራቡ ክፍል ያሉት አብያተ ክርስቲያናት በዕብራይስጥ ጽሑፎች ላይ የተመሠረተውን የጄሮምን የላቲን ትርጉም ከተጠቀሙና በምሥራቅ ያሉት የግሪክ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ የሰፕቱጀንትን ትርጉም ከተጠቀሙ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትከፋፈላለች የሚል ነበር።b ከዚህም በተጨማሪ አውጉስቲን ጄሮም ብቻ ለሚደግፈው ትርጉም ሲባል የሰፕቱጀንትን ትርጉም ገሸሽ መደረጉን በሚመለከት ያለውን ቅሬታ አሰምቷል።
ጄሮም ለእነዚህ ሁሉ ተቃዋሚዎች የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ጄሮም የሰዎች ትችት ብዙም ደንታ የማይሰጠው ሰው ስለነበረ እነዚህን ተቺዎች ከጉዳይም አልጣፋቸው። ሥራውን ቀጥታ ከዕብራይስጡ መሥራቱን የቀጠለ ሲሆን በ405 እዘአ የላቲን መጽሐፍ ቅዱሱን አጠናቀቀ። ዓመታት ሲያልፉ የትርጉም ሥራው ቩልጌት የሚል ስም ያተረፈ ሲሆን ይህም በብዙሐኑ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ትርጉም ማለት ነው። (በላቲን ቩልጋቱስ ማለት “የተለመደ ማለትም የታወቀ ማለት ነው”)
ዘላቂነት ያላቸው ውጤቶች
የጄሮም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም አንድን ነባር ትርጉም በማሻሻል የተሠራ አይደለም። ለመጪዎቹ ትውልዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትንና ትርጉም ጎዳና የቀየሰ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት “ቩልጌት ከሁሉ የላቀና ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ የአራተኛው መቶ ዘመን የሥነ ጽሑፍ ሥራ ሆኖ ይኖራል” ብለዋል።
ጄሮም በነገር ይዋጋ የነበረና ጠበኛ ባሕርይ ያለው ሰው ቢሆንም ብቻውን ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚደረገውን ምርምር እንደገና በመንፈስ አነሳሽነት ወደ ተጻፈው የዕብራይስጥ ጽሑፍ መርቷል። በቅን ልቦና ተነሣስቶ ዛሬ ፍጹም የማናገኛቸውን የጥንቶቹን የዕብራይስጥና የግሪክኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች አጥንቷል፣ አመሳክሯል። የእርሱ ሥራ ለአይሁዳውያኑ ማሶሪቶችም መቅድም ነበር። በመሆኑም አማራጭ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐረጎችን አቀማመጥ ለማወዳደር ቩልጌት እጅግ ጠቃሚ ማመሳከሪያ ነው።
የአምላክን ቃል የሚያፈቅሩ ሰዎች እጅግ ኃይለኛ የሆነውን ባሕርይውን ወይም ሃይማኖታዊ አመለካከቶቹን ቸል ብለው ያልፏቸዋል ማለት ባይሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነውና ብዙዎችን ያወዛገበው ይህ ሰው ያሳየውን ትጋት የተሞላበት ጥረት ያደንቃሉ። አዎን፣ ጄሮም ግቡን ከዳር አድርሷል። “ለትውልድ ለመተላለፍ የሚበቃ” ነገር አዘጋጅቷል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጄሮም ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች የዘመን ስሌትና ቅደም ተከተል በተመለከተ ሁሉም ታሪክ ጸሐፊዎች አንድ ዓይነት ሐሳብ የላቸውም።
b የኋላ ኋላ የጄሮም ትርጉም በምዕራቡ የሕዝበ ክርስትና ክፍል መሠረታዊ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ሰፕቱጀንት ግን እስከ ዛሬም ድረስ በምሥራቁ የሕዝበ ክርስትና ክፍል ይሠራበታል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቤተ ልሔም የሚገኘው የጄሮም ሐውልት
[ምንጭ]
Garo Nalbandian
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከላይ በስተግራ፣ የዕብራይስጥ ጥንታዊ ቅጂዎች:- Courtesy of the Shrine of the Book, Israel Museum, Jerusalem፤ ከታች በስተግራ፣ የሲሪያክ ጥንታዊ ቅጂዎች:- Reproduced by kind permission of The Trustees of the Chester Beatty Library, Dublin፤ ከላይ መሃል፣ የግሪክኛ ጥንታዊ ጽሑፎች:- Courtesy of Israel Antiquities Authority