ከሁሉ በተሻለው የሕይወት መንገድ አንድ መሆን
የዓለም ሕዝብ ቁጥር እያሻቀበ መሄዱን ከቀጠለ በቅርቡ በምድር ላይ የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ስድስት ቢልዮን ይደርሳል። ሁሉም ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ ቢሆንም ጠቢብና አፍቃሪ የሆነ አንድ አባት የሚቆጣጠረው የአንድ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል መሆናቸውን የሚያውቁ ግን አይመስልም። በብሔራት፣ በተለያዩ ዘሮችና ባሕሎች መካከል ያለው መከፋፈልና ግጭት ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ካለው የዓለም ሁኔታ አንጻር ሲታይ ዓለም አቀፋዊ አንድነት ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይመስል ነገር ነው። ዘ ኮሉምቢያ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ (እንግሊዝኛ) እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አንድ ላይ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው ለሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ ዘመናዊው ዓለም ሊሰጥ የሚችለው አንድም መልስ የለውም።”
ይሁን እንጂ በምድር ነዋሪዎች መካከል አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ አዲስ ሐሳብ ማፍለቅ አይጠይቅም። ወደ አንድነት የሚያደርሰው ጎዳና በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። ይህም ምድርንና በእርሷ ላይ ያለውን ሕይወት በጠቅላላ በፈጠረው አምላክ አምልኮ ላይ ያተኮረ ነው። የሐሳብ፣ የዓላማና የሕይወት ጎዳና እውነተኛ አንድነት በአምላክ ሕዝቦች መካከል አሁንም አለ። በ233 አገሮች የሚገኙ ከአምስት ሚልዮን ተኩል በላይ የሆኑት እነዚህ ሕዝቦች የአምላክ የሕይወት መንገድ ከሁሉ የላቀ መንገድ ነው በሚለው የጸና አቋማቸው አንድ ሆነዋል። ልክ እንደ መዝሙራዊው “አቤቱ፣ መንገድህን ምራኝ፣ በእውነትህም እሄዳለሁ” ብለው ይጸልያሉ።—መዝሙር 86:11
እንዲህ ያለውን በንጹሕ አምልኮ አማካኝነት የሰዎችን አንድ መሆን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ ከረዥም ጊዜ በፊት ትንቢት ተናግሮ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፣ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን።”—ኢሳይያስ 2:2, 3
የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው አንድነት በዓይነቱ ልዩ ነው። በዓለም ዙሪያ ከ87,000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች ታቅፈው በየሳምንቱ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ ይመገባሉ። (ማቴዎስ 24:45-47) ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ ከ1998 አጋማሽ አንስቶ እስከ 1999 መግቢያ ድረስ በዓለም ዙሪያ “የአምላክ የሕይወት መንገድ” የተባለ ሦስት ቀን የፈጀ ትልቅ ስብሰባ በማድረግ በሌላ መንገድ አንድ መሆናቸውን አሳይተዋል። ስብሰባዎቹ ከተደረጉባቸው አገሮች መካከል በአሥራ ሦስቱ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የተደረገ ሲሆን በእነዚህም ስብሰባዎች ላይ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ልዑካን ተገኝተዋል። በተቀሩት ቦታዎች የተደረጉት ስብሰባዎች ግን የአውራጃ ስብሰባ ተብለው ይታወቃሉ። ሆኖም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ በመንፈሳዊ ጥሩ ነገሮች የሞሉበት አንድ ዓይነት ፕሮግራም ቀርቧል።
ፊታቸው በደስታ የፈካና ማራኪ አለባበስ ያላቸው ልዑካን ከይሖዋ ለመማር ወደ ስብሰባ አዳራሾችና ስታዲዮሞች ሲጎርፉ መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ነው! በሚቺጋን፣ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የተገኘች አንዲት ልዑክ የሰጠችው አስተያየት ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል። እንዲህ አለች:- “ከዓለም ዙሪያ ማለትም ከቼክ ሪፑብሊክ፣ ከባርባዶስ፣ ከናይጄሪያ፣ ከሃንጋሪ፣ ከእንግሊዝ፣ ከሆላንድ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ እና ከሌሎች የተለያዩ አገሮች የመጡ ወንድሞች እየተቃቀፉ ሰላምታ ሲሰጣጡ መመልከት በጣም የሚያስደስት ነበር! ስምም ሆነው በአንድነት የተሰበሰቡት ወንድሞች አንዳቸው ለሌላውና ለታላቁ አምላካቸው ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው የደስታ እንባ ሲያነቡ መመልከት በጣም የሚያስደስት ነበር።” የሚቀጥለው ርዕስ በመላው ምድር የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተገኙበትን የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም ይከልሳል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.