እምነት የሚጣልባቸው ትንቢቶች ለማግኘት የተደረገ ጥረት
ታላቁ እስክንድር በመባል የሚታወቀው የመቄዶንያው ንጉሥ በ336 ከዘአበ ዙፋን ላይ ከወጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በማዕከላዊ ግሪክ በደልፊ ወደሚገኝ አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡበታል ወደሚባለው ቤተ መቅደስ (oracle) ሄደ። ምኞቱ አብዛኛውን የዓለም ክፍል በቁጥጥሩ ስር ማዋል ነበር። ሆኖም ስለ ውጥኑ መሳካት መለኮታዊ ማረጋገጫ ማግኘት ፈለገ። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ከሆነ ወደ ደልፊ በሄደበት ዕለት ትንቢት የምትናገረውን ካህን ማነጋገር አይቻልም ነበር። እስክንድር መልስ ሳያገኝ መሄድ ስላልፈለገ ካህኗ ትንቢት እንድትነግረው ግድ አላት። ሴትዮዋ በብስጭት ስሜት ጮኻ “አቤት አንተ ልጅ፣ የምትረታ ዓይነት አይደለህም!” አለችው። ወጣቱ ንጉሥ የሰጠችውን መልስ እንደ ጥሩ ገድ በመቁጠር በወታደራዊ ዘመቻ ድል እንደሚቀዳጅ የተገባለት ቃል አድርጎ ወሰደው።
ይሁን እንጂ እስክንድር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ትንቢቶች ቢመረምር ኖሮ የሚያደርጋቸውን ዘመቻዎች ውጤት በተመለከተ በጣም የተሻለ መረጃ ማግኘት ይችል ነበር። ትንቢቶቹ እርሱ ስለሚቀዳጃቸው ተከታታይ ድሎች በሚያስገርም ሁኔታ በትክክል ገልጸዋል። በመጨረሻ እስክንድር፣ ዳንኤል ስለ እርሱ የጻፈውን የማየት አጋጣሚ እንዳገኘ በአፈ ታሪክ ይነገራል። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ በዘገበው መሠረት የመቄዶንያው ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የዳንኤልን ትንቢት ምናልባትም ስምንተኛውን ምዕራፍ ሳይሆን አይቀርም አሳይተውታል። (ዳንኤል 8:5-8, 20, 21) ከዚህ የተነሳ ከተማዋ አጥፊ በሆነው የእስክንድር ሠራዊት ከመደምሰስ ልትተርፍ እንደቻለች ተዘግቧል።
ተፈጥሯዊ የሆነ የሰው ፍላጎት
ንጉሥም ሆነ ተራ ሰው፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ የሰው ልጅ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስተማማኝ የሆነ ትንቢት የማግኘት ፍላጎት አለው። የሰው ልጆች ማስተዋል ያለን ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን ያለፈውን ዘመን እንመረምራለን፣ የአሁኑን ጊዜ በንቃት እንከታተላለን በተለይ ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ እንጓጓለን። አንድ የቻይናውያን ብሒል “ከሦስት ቀን በኋላ የሚፈጸሙትን ነገሮች አስቀድሞ ማወቅ የቻለ ሰው ለብዙ ሺህ ዓመት ሀብታም ይሆናል” በማለት ነገሩን በትክክል ያስቀምጠዋል።
በታሪክ ዘመናት በሙሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መለኮታዊ ድጋፍ አላቸው ብለው ያሰቧቸውን ሁሉ በማማከር የወደፊቱን ጊዜ ለማወቅ ጥረት አድርገዋል። የጥንት ግሪኮችን እንደ ምሳሌ ውሰድ። እንደ ደልፊ፣ ዴሎስና ዶዶና የመሳሰሉ ስለ ፖለቲካዊ ወይም ስለ ወታደራዊ አልፎ ተርፎም እንደ ጉዞ፣ ጋብቻና ልጆች ስለ መሳሰሉ የግል ጉዳዮች ጭምር አማልክቶቻቸውን የሚጠይቁባቸው በርካታ ቅዱስ ሥፍራዎች ነበሯቸው። ነገሥታትና የጦር መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የአንድ ጎሳ አባላት እንዲሁም የከተማው ነዋሪ ባጠቃላይ በእነዚህ ቅዱስ ስፍራዎች በሚነገሩ ትንቢቶች አማካኝነት ከመንፈሳዊው ዓለም መመሪያ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር።
አንድ ፕሮፌሰር እንዳሉት ከሆነ ዛሬ “ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጥናት ለማካሄድ የተቋቋሙ ድርጅቶች በድንገት እንደ አሸን ፈልተዋል።” ሆኖም ብዙዎች ብቸኛው የትክክለኛ ትንቢት ምንጭ ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት አይሰጡትም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በትክክል እነርሱ የሚፈልጉትን መረጃ እንደያዘ ማወቅ የሚያስችላቸውን ማንኛውንም አጋጣሚ በግልጽ ይቃወማሉ። እንዲያውም አንዳንድ ሃይማኖታዊ ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ትንቢት አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡላቸዋል የሚባሉት በጥንት ዘመን የነበሩት ሰዎች ከተናገሯቸው ትንበያዎች ጋር እስከ ማመሳሰል ደርሰዋል። እንዲሁም በዘመናችን ያሉ ተጠራጣሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ አንተ ራስህ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶችና አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡላቸዋል የሚባሉት ሰዎች የተናገሯቸውን ትንበያዎች በጥንቃቄ ማወዳደራችን ምን ያስገነዝበናል? ከእነዚህ ትንበያዎች ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ እምነት መጣል ትችላለህን? እንዲሁም በእርግጠኛነት ሕይወትህን በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ዙሪያ መገንባት ትችላለህ?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ እስክንድር ስለሚያገኛቸው ተከታታይ ድሎች ትንቢት ተናግሯል
[ምንጭ]
Cortesía del Museo del Prado, Madrid, Spain
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታላቁ እስክንድር
[ምንጭ]
Musei Capitolini, Roma
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሽፋን: General Titus and Alexander the Great: Musei Capitolini, Roma