በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማመን የምትችለው ለምንድን ነው?
በሰሜን ምዕራባዊ ግሪክ የምትገኘው የኢፒረስ ንጉሥ ፋይረስ ከሮማ መንግሥት ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ቅራኔ ነበረው። የዚህ ቅራኔ መጨረሻ ምን እንደሚሆን ለማወቅ ካደረበት ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ በደልፊ ወደሚገኘው አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡበታል ወደሚባለው ቤተ መቅደስ ሄደ። ሆኖም የተሰጠው መልስ ቀጥሎ ከተጠቀሱት ሁለት መንገዶች በአንዱ ሊተረጎም ይችላል:- (1) “አንተ የአኩስ ልጅ ሆይ ሮማውያንን ማሸነፍ እንደማትችል ተገልጦልኛል። ለጦርነት ብትዘምትም ምንም ጉዳት ሳያገኝህ በሕይወት ትመለሳለህ።” (2) “አንተን የአኩስ ልጅ ሮማውያን እንደሚያሸንፉ ተገልጦልኛል። ከዘመትክ ትገደላለህ እንጂ ፈጽሞ በሕይወት አትመለስም።” ፋይረስ የመጀመሪያውን ትንበያ መቀበል ስለፈለገ በሮም ላይ ጦርነት አወጀና ከባድ ሽንፈት ደረሰበት።
እንዲህ ዓይነቶቹ ገጠመኞች በድሮ ዘመን ይነገሩ የነበሩ ትንበያዎች የተድበሰበሱና አሻሚ ናቸው እንዲባሉ አድርገዋቸዋል። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢትስ ምን ማለት ይቻላል? አንዳንድ ተቺዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡላቸዋል የሚባሉት ሰዎች ከሚናገሯቸው ትንበያዎች የተሻሉ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። እነዚህ ተቺዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በጣም ብልጣ ብልጥና ነገሮችን ማስተዋል የሚችሉ፣ በአብዛኛው የካህናት ክፍል የሆኑ ግለሰቦች የሰነዘሯቸው ብልጠት የተሞላባቸው ትንበያዎች እንደሆኑ ይገምታሉ። እነዚህ ሰዎች እንዲሁ በተሞክሮ ወይም ባላቸው ልዩ ዝምድና የተነሳ የአንዳንድ ሁኔታዎችን ተፈጥሯዊ አካሄድ አስቀድመው ሊያዩ እንደሚችሉ ይታመናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የያዟቸውን የተለያዩ ገጽታዎች አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡላቸዋል የሚባሉት ሰዎች ከሚናገሯቸው ትንቢቶች ጋር በማነጻጸር ትክክለኛ መደምደሚያዎች ላይ ለመድረስ በተሻለ ሁኔታ የታጠቅን እንሆናለን።
ልዩነቶች የሚታዩባቸው ነጥቦች
እነዚህ ሰዎች የሚናገሯቸው ትንቢቶች መለያ አሻሚነታቸው ነው። ለምሳሌ ያህል በደልፊ ይሰጡ የነበሩት መልሶች ምን ለማለት እንደተፈለገ አይገቡም ነበር። ይህም መልሶቹን የሚተረጉሙ ካህናት እንዲያስፈልጉና እርስ በርስ ሊቃረኑ የሚችሉ ትንታኔዎች እንዲሰጡ በር ከፍቷል። የልድያ ንጉሥ ለሆነው ለክሮይሰስ የተሰጠው መልስ ለዚህ አባባላችን ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። መለኮታዊ ምሥጢር ይገለጥበታል ወደሚባለው ቤተ መቅደስ ሄዶ ስለ ጉዳዩ ሲያማክር “ክሮይሰስ፣ ሐሊስን ተሻግሮ ከሄደ አንድ ኃያል መንግሥት ይደመስሳል” ተብሎ ተነገረው። እንደ እውነቱ ከሆነ የተደመሰሰው ግን የራሱ “ኃያል መንግሥት” ነበር! ክሮይሰስ ቀጰዶቅያን ለመውረር የሐሊስን ወንዝ ተሻግሮ በሄደ ጊዜ በፋርሳዊው ቂሮስ እጅ ሽንፈት ደረሰበት።
ከአረማውያኑ ካህናት ትንበያዎች በተቃራኒ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በትክክለኝነታቸውና በግልጽነታቸው የሚታወቁ ናቸው። የባቢሎንን ውድቀት በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት ለአብነት ያህል ሊጠቀስ ይችላል። ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ ወደ 200 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ሜዶ ፋርስ ባቢሎንን እንዴት ድል እንደሚያደርግ በዝርዝርና በትክክል ትንቢት ተናግሮ ነበር። ትንቢቱ ድል አድራጊው ወገን ቂሮስ ተብሎ እንደሚጠራ ከመግለጹም በላይ መከላከያ የሚሆነውን ጥልቅና ሰፊ ወንዝ የማድረቁን የጦር ስልት እንዲሁም ክፍት በሆነው በር በኩል ወደ ተመሸገው ከተማ እንደሚገቡ አሳውቋል። ይህ ሁሉ በትክክል ተፈጽሟል። (ኢሳይያስ 44:27–45:2) በተጨማሪም ውሎ አድሮ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ ባድማ እንደምትሆን በትክክል ተተንብዮ ነበር።—ኢሳይያስ 13:17-22
በተጨማሪም ነቢዩ ዮናስ ያወጀው ይህ ማስጠንቀቂያ ምን ያህል ግልጽ እንደሆነ ተመልከት:- “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትደመሰሳለች!” (ዮናስ 3:4 የ1980 ትርጉም) እዚህ ላይ አንድም አሻሚ ነገር አይገኝም! መልእክቱ አስደንጋጭና ቀጥተኛ ስለነበረ የነነዌ ሰዎች ወዲያውኑ “እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፣ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ።” በዚያን ወቅት ንስሐ በመግባታቸው ምክንያት ይሖዋ በነነዌ ሰዎች ላይ ጥፋት አላመጣባቸውም።—ዮናስ 3:5-10
አማልክት የገለጡላቸውን ምሥጢር ይናገራሉ የሚባሉት ካህናት የሚናገሯቸው ትንቢቶች ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ያገለግሉ ነበር። ገዥዎችና የጦር መሪዎች የራሳቸውን ጥቅምና ውጥን ለማራመድ የመረጧቸውን ትንታኔዎች መላልሰው በመጥቀስ ትንታኔዎቹን “መለኮታዊ ካባ” ያለብሷቸው ነበር። የአምላክ ትንቢታዊ መልእክቶች ግን የግል ክብር ለማስጠበቅ ታቅደው የተነገሩ አይደሉም።
የይሖዋ ነቢይ የነበረው ናታን ኃጢአት የፈጸመውን ንጉሥ ዳዊትን ከመውቀስ ወደኋላ አለማለቱ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። (2 ሳሙኤል 12:1-12) ዳግማዊ ኢዮርብዓም በአሥሩ የእስራኤል ነገድ ላይ ነግሦ በነበረበት ወቅት ነቢዩ ሆሴዕና አሞጽ ዓመፀኛ የሆነው ንጉሥና ደጋፊዎቹ በከሃዲነታቸውና አምላክን በማያስከብር ተግባራቸው ምክንያት ጥብቅ ወቀሳ ሰንዝረውባቸዋል። (ሆሴዕ 5:1-7፤ አሞጽ 2:6-8) በተለይ ይሖዋ በነቢዩ አሞጽ በኩል ለንጉሡ ያስነገረው ማስጠንቀቂያ በጣም ኃይለኛ ነበር:- “በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ።” (አሞጽ 7:9) በትንቢቱ መሠረት የኢዮርብዓም ቤት ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል።—1 ነገሥት 15:25-30፤ 2 ዜና መዋዕል 13:20
አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ሰዎች ትንቢት የሚያስነግሩት በገንዘብ ነበር። በርከት ያለ ገንዘብ የከፈለ ሰው ለእሱ የሚስማማው ዓይነት ትንቢት ይነገረዋል። ደልፊ ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ሄደው የሚጠይቁ ሰዎች ምንም እርባና ለሌለው መረጃ ብዙ ገንዘብ ይከፍሉ ነበር። እንዲህ በማድረጋቸውም የአፖሎ ቤተ መቅደስና ሌሎች ቤተ መቅደሶች ውድ ዋጋ በሚያወጡ ዕቃዎች እንዲሞሉ አድርገዋል። ከዚህ በተቃራኒ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና ማስጠንቀቂያዎች የሚነገሩት ያለ ክፍያና በማንኛውም ሁኔታ ያለ አድልዎ ነበር። እውነተኛ ነቢይ በገንዘብ ስለማይደለል ባለ ጉዳዩ ያለው ሥልጣን ወይም ሀብት ምንም ይሁን ምን የተለየ ነገር አይደረግም። ነቢይና መስፍን የነበረው ሳሙኤል “ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን እጅ ጉቦ ተቀበልሁ?” ብሎ በቅንነት ሊጠይቅ ችሏል።—1 ሳሙኤል 12:3
ትንበያዎቹን መስማት የሚቻለው በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ስለነበር ሰዎች እነዚህን ትንበያዎች ለመስማት ብዙ መጓዝ ነበረባቸው። አብዛኞቹ ቦታዎች የሚገኙት ኢፒረስ ውስጥ በቶማሩስ ተራራ ላይ እንደሚገኘው ዶዶና እና በተራራማው ማዕከላዊ ግሪክ እንዳለው እንደ ደልፊ ባሉ ቦታዎች ስለነበር አንድ ተራ ሰው ወደዚያ ለመሄድ በጣም ይቸገራል። አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ ቤተ መቅደሶች አማልክትን ማማከር የሚችሉት ሀብታሞችና ባለ ሥልጣኖች ብቻ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ በዓመቱ ውስጥ “የአማልክቱ ፈቃድ” የሚገለጽባቸው ቀናት ውስን ነበሩ። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ አምላክ ትንቢት የሚናገሩ መልእክተኞቹ ሕዝቡ መስማት ያለበትን ትንቢቶች እንዲያውጁ በቀጥታ ወደ እነርሱ ልኳቸዋል። ለምሳሌ ያህል አይሁዶች በግዞት ወደ ባቢሎን ተወስደው በነበረበት ወቅት አምላክ ቢያንስ ሦስት ነቢያት ማለትም ኤርምያስ በኢየሩሳሌም፣ ሕዝቅኤል ከግዞተኞቹ ጋር እንዲሁም ዳንኤል በባቢሎን ግዛት ዋና ከተማ በሕዝቦቹ መካከል እንዲያገለግሉ አድርጎ ነበር።—ኤርምያስ 1:1, 2፤ ሕዝቅኤል 1:1፤ ዳንኤል 2:48
አብዛኛውን ጊዜ ትንበያዎቹ የሚነገሩት በግል ሲሆን ተቀባዩ ለራሱ በሚጠቅመው መንገድ ሊተረጉማቸው ይችል ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ሁሉም ሰው መልእክቱን መስማትና ትርጉማቸውን መረዳት እንዲችል በአብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚነገሩት በይፋ ነበር። ነቢዩ ኤርምያስ የሚያውጀው መልእክት በመሪዎቹም ሆነ በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ቢያውቅም እንኳ በተደጋጋሚ ኢየሩሳሌም ውስጥ በይፋ ተናግሯል።—ኤርምያስ 7:1, 2
በዛሬው ጊዜ፣ አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡላቸዋል የሚባሉ ሰዎች የተናገሯቸው ትንበያዎች የሚታዩት የጥንታዊ ታሪክ ክፍል ተደርገው ነው። ባለንበት አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚያስገኙት ተግባራዊ ጥቅም የለም። እነዚህ ትንበያዎች ከጊዜያችንም ሆነ ከወደፊቱ ጊዜ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ግን ‘ሕያውና የሚሠራ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል’ ክፍል ናቸው። (ዕብራውያን 4:12) እስካሁን የተፈጸሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ይሖዋ ከሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት ግንዛቤ ከማስጨበጣቸውም በላይ ስለ እርሱ ዓላማዎችና ሁለንተናዊ ባሕርይ ዓበይት የሆኑ ገጽታዎችን ይገልጻሉ። በተጨማሪም በቅርቡ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ ጉልህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከፊታችን የሚጠብቀንን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና [ሰማያዊውን መሲሐዊ መንግሥት] አዲስ ምድር [ጻድቅ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ] እንደ [አምላክ] ተስፋ ቃ[ል] እንጠብቃለን።”—2 ጴጥሮስ 3:13
የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢትና የሐሰት ሃይማኖት ትንበያዎችን በተመለከተ ያደረግነው አጭር ንጽጽር ዘ ግሬት አይዲያስ በተባለው መጽሐፍ ላይ ከተገለጸው ቀጥሎ ካለው ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ሳያደርግህ አይቀርም:- “ስለወደፊቱ በማወቅ ረገድ ሟች የሆነው የሰው ልጅ ካለው ችሎታ አንጻር ሲታይ ዕብራውያን ነቢያት ለየት ያሉ ይመስላሉ። እንደ አረማውያን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ጠንቋዮች . . . መለኮታዊ ምሥጢሮችን ለማወቅ የተለያዩ ጥበቦችን ወይም ዘዴዎችን መጠቀም አላስፈለጋቸውም ነበር። . . . አማልክት መለኮታዊ ምሥጢር ይገልጡላቸዋል የሚባሉት ሰዎች እንደሚናገሯቸው ትንቢቶች የተድበሰበሱ አይደሉም። የአምላክን ዓላማ በተመለከተ እርሱ ራሱ ሰዎች መለኮታዊ አመራር የሚያስገኘውን ጥቅም ማስተዋል እንዲችሉ ስለሚፈልግ ቢያንስ ቢያንስ ዓላማው ነገሮችን መግለጥ እንጂ መሸፋፈን አይደለም።”
በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማመን ትችል ይሆን?
የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ማመን ትችላለህ። እንዲያውም ሕይወትህ በይሖዋና እርሱ በገባው ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜ ዙሪያ እንዲያተኩር ማድረግ ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስቀድሞ ፍጻሜያቸውን ያገኙ አሁን ምንም ትርጉም የሌላቸው ትንበያዎች ጥርቅም አይደለም። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ትንቢቶች አሁን በመፈጸም ላይ ናቸው አሊያም በቅርቡ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ካለፈው በመነሳት እነዚህ ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ሙሉ በሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይችላል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ትንቢቶች በጊዜያችን ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ ስለሚያካትቱ በቁም ነገር ብንመለከታቸው እንጠቀማለን።
በኢሳይያስ 2:2, 3 ላይ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በእርግጠኝነት እምነት ማሳደር ትችላለህ:- “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።” ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍ ያለውን የይሖዋ አምልኮ እየተቀበሉና በእርሱ ጎዳና መጓዝ እየተማሩ መሆናቸው የተረጋገጠ ነው። በእርሱ ጎዳና መጓዝ እንድትችል ስለ አምላክ መንገዶች ይበልጥ ለመማር እንዲሁም እርሱንና ዓላማዎቹን በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት ለመቅሰም የሚያስችልህን አጋጣሚ ትጠቀምበታለህ?—ዮሐንስ 17:3
አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መፈጸም በእኛ በኩል ፈጣን እርምጃ እንድንወስድ ያስገድደናል። መዝሙራዊው በቅርቡ የሚፈጸመውን በተመለከተ እንዲህ ሲል በትንቢታዊ መንገድ ዘምሯል:- “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ . . . ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም።” (መዝሙር 37:9, 10) በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚያፌዙትን ጨምሮ በክፉዎች ላይ ከሚመጣው በፍጥነት እየቀረበ ካለው ጥፋት ለመትረፍ ምን ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስልሃል? ይኸው መዝሙር “እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ” ሲል ይመልሳል። (መዝሙር 37:9) በይሖዋ ተስፋ ማድረግ ሲባል ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ሙሉ እምነት መጣልና ሕይወታችንን ከእርሱ የአቋም ደረጃዎች ጋር ማስማማት ማለት ነው።—ምሳሌ 2:21, 22
በይሖዋ ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች ምድርን ሲወርሱ ሕይወት ምን መልክ ይኖረዋል? አሁንም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች አስደሳች የወደፊት ጊዜ እንደተጠበቀላቸው ይገልጻሉ። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራሉ፤ በምድረ በዳ ውኃ፣ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና።” (ኢሳይያስ 35:5, 6) ሐዋርያው ዮሐንስ እነዚህን መንፈስ የሚያረጋጉ ቃላት ጽፏል:- “[ይሖዋ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። በዙፋንም የተቀመጠው:- . . . እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።”—ራእይ 21:4, 5
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ ያምናሉ። እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ ከሰጠው ጥብቅ ምክር ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ:- “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፣ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።” (2 ጴጥሮስ 1:19) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ለወደፊቱ ጊዜ በያዛቸው ግሩም ተስፋዎች እንድትበረታቱ ልባዊ ምኞታችን ነው!
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በደልፊ የሚገኘው ቤተ መቅደስ በጥንቷ ግሪክ በጣም ዝነኛ ነበር።
እንፋሎቱ በውስጧ የሚያነቃቃ ስሜት ይፈጥርባት ነበር
[ሥዕሎች]
ካህኗ ባለ ሦስት እግር ወንበር ላይ ተቀምጣ ትተነብይ ነበር
እርሷ የምትናገራቸው ነገሮች አፖሎ ከሚባለው አምላክ የተገለጡላትን ራእዮች ይዘዋል ተብሎ ይታመን ነበር
[ምንጭ]
ባለ ሦስት እግር ወንበር:- From the book Dictionary of Greek and Roman Antiquities; አፖሎ:- The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ደልፊ በሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚነገሩት ትንበያዎች ፈጽሞ እምነት የሚጣልባቸው አልነበሩም
[ምንጭ]
Delphi, Greece
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱን ዓለም በተመለከተ በያዘው ትንቢት ላይ ሙሉ ትምክህት ልትጥል ትችላለህ