የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 7/15 ገጽ 29-31
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • “መልካም ለማድረግ አትታክቱ“
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የጉባኤውን ሰላምና ንጽሕና መጠበቅ
    የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ‘በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩ ያሉትን አክብሯቸው’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 7/15 ገጽ 29-31

የአንባብያን ጥያቄዎች

በ2 ተሰሎንቄ 3:​14 ላይ ‘ምልክት ማድረግ’ [NW] ተብሎ የተጠቀሰው ነገር መደበኛ የሆነ የጉባኤ አሠራር ነው ወይስ ክርስቲያኖች በሥርዓት ከማይሄዱ ወንድሞች ለመራቅ በግል የሚወስዱት እርምጃ ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የጻፈላቸው መልእክት የጉባኤው ሽማግሌዎች በእንዲህ ዓይነቱ ‘ምልክት የማድረግ’ ተግባር ግልጽ ሚና እንዳላቸው ያሳያል። ሆኖም ከዚያ በኋላ ግለሰብ ክርስቲያኖች ‘ምልክት የማድረጉን’ እርምጃ ይደግፋሉ። ይህንም የሚያደርጉት መንፈሳዊ ዓላማዎችን በአእምሯቸው ይዘው ነው። ጳውሎስ ይህን ምክር ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠበት ወቅት የነበረውን መቸት መመርመራችን ጉዳዩን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችለናል።

ጳውሎስ ወንዶችንም ሴቶችንም አማኞች እንዲሆኑ በመርዳት የተሰሎንቄ ጉባኤ እንዲመሠረት አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ሥራ 17:​1-4) ከዚያም እነርሱን ለማመስገንና ለማበረታታት ከቆሮንቶስ ሆኖ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ አስፈላጊውን ምክርም ሰጥቷቸዋል። ‘በጸጥታ እንዲኖሩ፣ ለራሳቸው ጉዳይ እንዲጠነቀቁና በእጃቸው እንዲሠሩ’ አሳስቧቸዋል። አንዳንዶች በዚህ መንገድ እየተመላለሱ ስላልነበሩ ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏቸዋል:- “ወንድሞች ሆይ፣ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው።” በግልጽ መረዳት እንደምንችለው በመካከላቸው ምክር የሚያስፈልጋቸው ‘ያለ ሥርዓት የሚሄዱ’a ክርስቲያኖች ነበሩ።​—⁠1 ተሰሎንቄ 1:​2-10፤ 4:​11፤ 5:​14

ከተወሰኑ ወራት በኋላ ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ወደፊት ስለሚገኝበት ጊዜ ተጨማሪ ሐሳቦች በማከል ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ሁለተኛውን ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ “ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፣ በሰው ነገር እየገቡ” ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ሰዎች በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ተጨማሪ መመሪያ ሰጥቷል። ጳውሎስ ትጉ ሠራተኛ በመሆን የተወውን ምሳሌም ሆነ አንድ ሰው ራሱን ለመደገፍ መሥራት እንዳለበት የሰጠውን ግልጽ መመሪያ የሚጻረር አካሄድ ነበራቸው። (2 ተሰሎንቄ 3:​7-12) ጳውሎስ አንዳንድ እርምጃዎች እንዲወሰዱ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። እነዚህ እርምጃዎች የሚወሰዱት ሽማግሌዎች በሥርዓት ለማይሄዱት ሰዎች ተግሣጽ ወይም ምክር ከሰጡ በኋላ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:-

“ወንድሞች ሆይ፣ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ . . . እናዛችኋለን። እናንተ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፣ ይህን ተመልከቱት [“ምልክት አድርጉበት፣” NW]፣ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።”​—⁠2 ተሰሎንቄ 3:​6, 13-15

ስለዚህ ተጨማሪ እርምጃዎቹ በሥርዓት ከማይሄዱት ሰዎች መለየትን፣ በእነርሱ ላይ ምልክት ማድረግንና ከእነርሱ ጋር አለመተባበርን፣ ሆኖም እንደ ወንድም መገሰጽን ያጠቃልላሉ። የጉባኤው አባላት እነዚህን እርምጃዎች የሚወስዱት ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲኖሩ ነው? ይህን ግልጽ ለማድረግ ጳውሎስ በዚህ ረገድ ትኩረት ያላደረገባቸውን ሦስት ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት።

1. ክርስቲያኖች ፍጽምና እንደሌላቸውና ሊሳሳቱ እንደሚችሉ እናውቃለን። ቢሆንም የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ፍቅር ስለሆነ ሌሎች የፈጸሟቸውን ስህተቶች ተገንዝበን ይቅር እንድንላቸው ግድ ይለናል። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን በበርናባስና በጳውሎስ መካከል እንደተከሰተው ሁሉ ከስንት አንዴ በቁጣ ይገነፍል ይሆናል። (ሥራ 15:​36-40) ወይም አንድ ሰው ከተሰማው የድካም ስሜት የተነሳ ሸካራና ስሜት የሚያቆስሉ ቃላት ይናገር ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ፍቅር በማሳየትና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ በማዋል ከክርስቲያን ባልንጀራችን ጋር አብሮ መኖር፣ መተባበርና መሥራት በመቀጠል ስህተቱን መሸፈን እንችላለን። (ማቴዎስ 5:​23-25፤ 6:​14፤ 7:​1-5፤ 1 ጴጥሮስ 4:​8) ጳውሎስ በ2 ተሰሎንቄ ላይ እየተናገረ የነበረው ስለ እንዲህ ዓይነቱ ስህተት እንዳልነበረ ግልጽ ነው።

2. ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን፣ አካሄዱና ዝንባሌው ጥሩ ካልሆነ ሌላ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በራሱ አነሳሽነት ገደብ ለማበጀት ስለሚመርጥበት ሁኔታ እየተናገረ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል ለመዝናኛ ወይም ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ ትኩረት የሚሰጥ ክርስቲያን ሊሆን ይችላል። ወይም አንድ ወላጅ ልጁ ለወላጆቻቸው ከማይታዘዙ፣ አደገኛ አካሄድ ካላቸው ወይም የክርስትናን ሕይወት በጥብቅ ከማይከተሉ ወጣቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ይገድብበት ይሆናል። እነዚህ በምሳሌ 13:​20 ላይ በምናነበው መሠረት በግል የሚደረጉ ውሳኔዎች ናቸው:- “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።”​—⁠ከ1 ቆሮንቶስ 15:​33 ጋር አወዳድር።

3. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ላይ ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ንስሐ ያልገባን ሰው በሚመለከት ለየት ያለ ክብደት ስላለው ጉዳይ ጽፎላቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤው መወገድ ነበረባቸው። ‘ክፉው’ ሰው በምሳሌያዊ አነጋገር ለሰይጣን መሰጠት ነበረበት። ከዚህ በኋላ ታማኝ ክርስቲያኖች እንደዚህ ካሉ ክፉ ሰዎች ጋር መቀላቀል የለባቸውም ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቲያኖች እነዚህን ሰዎች ሰላም ማለት እንኳ እንደሌለባቸው አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:​1-13፤ 2 ዮሐንስ 9-11) ሆኖም ይህም ቢሆን በ2 ተሰሎንቄ 3:​14 ላይ ከሚገኘው ምክር ጋር ዝምድና የለውም።

‘በሥርዓት የማይሄዱ’ ሰዎችን በተመለከተ በ2 ተሰሎንቄ ላይ የተብራራው ጉዳይ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ሁኔታዎች የተለየ ነገርን ያካትታል። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች አሁንም ‘ወንድሞች’ እንደሆኑና ተግሣጽ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም እንደ ወንድሞች መያዝ እንዳለባቸው ጽፏል። በመሆኑም ‘በሥርዓት የማይሄዱ’ ወንድሞችን በሚመለከት የተከሰተው ችግር በክርስቲያኖች መካከል የተፈጠረ የግል ጉዳይ ተደርጎ የሚታይም ሆነ በቆሮንቶስ ከተከሰተው ሥነ ምግባር ከጎደለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ጳውሎስ እንዳደረገው የጉባኤ ሽማግሌዎች የውገዳ እርምጃ ለመውሰድ ጣልቃ እንዲገቡ የሚያስገድድ ክብደት ያለው ጉዳይም አይደለም። ‘በሥርዓት የማይሄዱት’ ወንድሞች በቆሮንቶስ የተወገደው ሰው የፈጸመውን ያህል የከፋ ኃጢአት አልፈጸሙም።

በተሰሎንቄ የነበሩት ‘በሥርዓት የማይሄዱ’ ክርስቲያኖች ጎላ ባለ ሁኔታ ከክርስትና መንገድ ፈቀቅ በማለታቸው ተወቃሾች ነበሩ። የክርስቶስን መመለስ እጅግ ቅርብ አድርገው በማሰባቸውም ሆነ በስንፍናቸው ምክንያት ሥራ አይሠሩም ነበር። በተጨማሪም ‘በማይመለከታቸው ነገር ውስጥ እየገቡ’ ሰላም ይነሱ ነበር። ጳውሎስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ከሰጠው ምክርና ከሌሎች መለኮታዊ ምክሮች ጋር በሚስማማ መንገድ የጉባኤው ሽማግሌዎች በተደጋጋሚ ተግሣጽ ሳይሰጧቸው አይቀርም። (ምሳሌ 6:​6-11፤ 10:​4, 5፤ 12:​11, 24፤ 24:​30-34) ይህም ሆኖ በጉባኤው ላይ ነቀፋ ሊያመጣና ወደ ሌሎች ክርስቲያኖች ሊዛመት የሚችለውን አካሄዳቸውን አላስተካከሉም። ስለዚህ ክርስቲያን ሽማግሌው ጳውሎስ የግለሰቦቹን ስም ሳይጠቅስ የተሳሳተ አካሄዳቸውን በማጋለጥ ሥርዓት አልበኝነታቸው በይፋ እንዲታወቅ አድርጓል።

በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ ክርስቲያኖች በሥርዓት በማይሄዱ ሰዎች ላይ ‘ምልክት’ ማድረጋቸው ተገቢ መሆኑን ለጉባኤው አሳውቋል። ይህም ለጉባኤው በይፋ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠበት አኗኗር ጋር የእነማን ድርጊት እንደሚመሳሰል ግለሰቦች ማስተዋል አለባቸው ማለት ነው። ጳውሎስ “በሥርዓት ከማይሄድ ከማንኛውም ወንድም መራቅ” እንዳለባቸው መክሯቸዋል። ሆኖም ‘እንደ ወንድም መገሠጻቸውን መቀጠል’ ስለነበረባቸው ይህ አባባል ከእንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ሙሉ በሙሉ መራቅ አለባቸው ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በስብሰባዎችና ምናልባትም በአገልግሎት ላይ ክርስቲያናዊ ግንኙነት ማድረጋቸውን ይቀጥሉ ይሆናል። ወንድማቸው ለተሰጠው ተግሣጽ በጎ ምላሽ እንደሚሰጥና ሰላም የሚነሳ አካሄዱን እንደሚተው ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ከእርሱ ‘የሚያፈገፍጉት’ በምን መልኩ ነው? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ይህ ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚመለከት ነበር። (ከገላትያ 2:​12 ጋር አወዳድር።) ከእርሱ ጋር የሚያደርጉትን ማኅበራዊ ግንኙነትና አብረው መዝናናታቸውን ማቆማቸው ሥርዓታማ የሆኑ ሰዎች በእርሱ አካሄድ እንደማይደሰቱ ያስገነዝበው ይሆናል። እርሱ እፍረት ተሰምቶት ለውጥ ባያደርግም እንኳ ቢያንስ ቢያንስ ሌሎች የእርሱን አካሄድ የመማራቸውና እርሱን የመምሰላቸው አጋጣሚ አነስተኛ ይሆናል። የዚያኑ ያህል እነዚህ ግለሰብ ክርስቲያኖች አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል መክሯቸዋል:- “እናንተ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ።”​—⁠2 ተሰሎንቄ 3:​13

ይህ ሐዋርያዊ ምክር አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶች የሚሠሩ ወንድሞቻችንን በንቀት ለመመልከት ወይም በእነርሱ ላይ ለመፍረድ መሠረት እንደማይሆነን ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ዓላማው ከክርስትና መንገድ ጋር ጉልህ በሆነ መንገድ በመቃረኑ ሰላም የሚነሳ አኗኗር የሚከተለውን ሰው መርዳት ነው።

ጳውሎስ ውስብስብ የሆነ አሠራር ለማቋቋም የሚሞክር ይመስል ዝርዝር መመሪያዎችን አልደነገገም። ሆኖም ሽማግሌዎች በሥርዓት የማይሄደውን ወንድም በመጀመሪያ መምከርና ለመርዳት መሞከር እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ይህ ጥረት ካልተሳካላቸውና ግለሰቡ ሥርዓት በሌለው መንገድ መመላለሱን ከቀጠለ እንዲሁም አካሄዱ የመዛመት አዝማሚያ ካለው ሽማግሌዎቹ ጉባኤው ማሳሰቢያ ሊሰጠው እንደሚገባ ይወስኑ ይሆናል። ይህ ዓይነቱ ሥርዓት አልበኝነት ለምን መወገድ እንዳለበት የሚገልጽ ንግግር እንዲቀርብ ዝግጅት ማድረግ ይችላሉ። ስም ጠቅሰው ባይናገሩም እንኳ ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ወንድሞች ያን ዓይነቱን ሥርዓት አልበኝነት በግልጽ ከሚያንጸባርቅ ማንኛውም ወንድም ጋር ያላቸውን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ ተጨማሪ ጥንቃቄ ስለሚያደርጉ ሽማግሌዎች የሚሰጡት የማስጠንቀቂያ ንግግር ጉባኤውን ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳል።

ከጊዜ በኋላ በሥርዓት የማይሄደው ወንድም አካሄዱ አሳፍሮት ለውጥ ለማድረግ እንደሚነሳሳ ተስፋ እናደርጋለን። በጉባኤው ያሉ ሽማግሌዎችና ሌሎች ወንድሞች ግለሰቡ ለውጥ ማድረጉን ሲመለከቱ ከእርሱ ጋር በነበራቸው ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ በራሳቸው አነሳሽነት አበጅተውት የነበረውን ገደብ ለማንሳት በተናጥል ሊወስኑ ይችላሉ።

ነገሩን በዚህ መንገድ ማጠቃለል እንችላለን:- አንድ ሰው በሥርዓት የማይመላለስ ከሆነ የጉባኤው ሽማግሌዎች እርዳታና ምክር በመስጠት ረገድ ቀዳሚ ይሆናሉ። ግለሰቡ አካሄዱ የተሳሳተ መሆኑን መገንዘብ ካቃተውና መጥፎ ተጽእኖ ማሳደሩን ከቀጠለ ሽማግሌዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን አመለካከት ቁልጭ አድርጎ በሚያሳይ ንግግር አማካኝነት ጉባኤውን ማስጠንቀቅ ይፈልጉ ይሆናል። ጉዳዩ አማኝ ካልሆነ ተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ወይም ማንኛውም ዓይነት ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:​39፤ 2 ቆሮንቶስ 6:​14) በዚህ መንገድ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው የጉባኤው ክርስቲያኖች በሥርዓት እንደማይመላለሱ በግልጽ ከሚያሳዩ ሰዎች፣ አሁንም ወንድሞች ቢሆኑም እንኳ ያላቸውን ማኅበራዊ ግንኙነት ለመገደብ በግል ሊወስኑ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የግሪክኛው ቃል ሥርዓት የማያከብሩ ወይም ዲሲፕሊን የማይከተሉ ወታደሮችን እንዲሁም በትምህርት ገበታቸው ላይ የማይገኙ ቸልተኛ ተማሪዎችን ለማመልከት ይሠራበት ነበር።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሥርዓት የማይሄዱትን ቢገስጿቸውም እንኳ መሰል አማኞች አድርገው ይመለከቷቸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ