የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ምሥክሮቹ ለፈረንሳይ ሕዝብ መልዕክታቸውን አደረሱ
በፈረንሳይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከዓርብ ጥር 29, 1999 ጠዋት ጀምሮ እስከ እሁድ ድረስ የፈረንሳይ ሕዝብ ሆይ፣ ተታልለሃል! የሚል ርዕስ ያለውን ትራክት 12 ሚልዮን ቅጂዎች መጀመሪያ በመንገድ ላይ ከዚያም ከቤት ወደ ቤት በግለት ሲያሰራጩ ሰንብተዋል። ይህን ዘመቻ ማድረግ ለምን አስፈለገ?
ይህ ዘመቻ ያስፈለገበት ምክንያት ዓርብ ጠዋት በፓሪስ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል። አንድ የምሥክሮቹ ቃል አቀባይ እንዲህ በማለት ገልጿል:- “ይህን ዘመቻ ለማድረግ የተነሣነው ማንነታችንን በትክክል ለማሳወቅና ስለ እኛ የተሰራጩትን ስም የሚያጠፉ መግለጫዎች ለማስቆም ነው። ትችት ለመቀበል ፈቃደኞች ነን፣ ሆኖም ከእንግዲህ ስማችንን የሚያጎድፉ የሐሰት ወሬዎችንና አስተያየቶችን እያዳመጥን ዝም አንልም።”
የይሖዋ ምሥክሮች እምነት በፈረንሳይ ካሉት የክርስትና ሃይማኖቶች መካከል በትልቅነቱ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ብዙ ምሥክር ልጆች በትምህርት ቤት ሲሰደቡና ሲንገላቱ ኖረዋል። አዋቂዎችም በሃይማኖታቸው ምክንያት ከሥራ እንዲወጡ ተደርጓል እንዲሁም ዛቻ ደርሶባቸዋል። ይባስ ብሎ በሚያገኙት ሃይማኖታዊ መዋጮ ላይ የ60 በመቶ ቀረጥ መጣሉ ለማመን የሚያስቸግር ነው። ዘመቻው ይህን መድልዎ አስመልክቶ ምን ነገር አከናውኗል?
ትራክቱ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “በፈረንሳይ የሚኖሩት 250,000 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችና ተባባሪዎቻቸው ከ1900 ጀምሮ በፈረንሳይ ሲንቀሳቀስ የኖረው የክርስትና ሃይማኖታቸው ከ1995 ወዲህ ሐቀኝነት በጎደለው መንገድ ከሌሎች አደገኛ መናፍቃን ቡድኖች ጋር መፈረጁን ይቃወማሉ። . . . እንዲሁም ያለማቋረጥ የሚደርስባቸውን መንገላታት ይቃወማሉ።” በፈረንሳይ በሚገኙ ምሥክሮች ላይ የተሰነዘሩት የሐሰት ክሶችና የእነርሱን ስም ለማጥፋት የተነሱ ሰዎች በሕዝቡ ዘንድ የተዛባ አመለካከት ለመፍጠር የተጠቀሙባቸው መሰሪ ዘዴዎች ተጋልጠዋል። ትራክቱ እንዲህ በማለት ይደመድማል:- “ዛሬ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችና ተባባሪዎቻቸው በአውሮፓ ውስጥ ይኖራሉ። የወንጌልን ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎች በመጠበቅ በዜግነት የሚኖሩባቸውን መንግሥታት ሕግ ያከብራሉ። የፈረንሳይ ሕዝብ ሆይ፣ እውነታው ይህ ነው። ሐቁን የማሳወቅ ግዴታ አለብን!”
ፈጣን የሆነ አዎንታዊ ምላሽ
በመጀመሪያው ቀን በሚልዮን የሚቆጠሩ ትራክቶች ተሠራጭተዋል። በፓሪስ ብቻ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከ7,000 የሚበልጡ ምሥክሮች ከ1.3 ሚልዮን በላይ ትራክቶች በሰዎች እጅ እንዲገቡ አድርገዋል። በእርግጥም ያን ያህል ቁጥር ያላቸው ምሥክሮች ትራክት ሲያድሉ ማየት ለሰዎቹ አዲስ ነገር ነበር። አገር አቀፍ ስርጭት ያላቸውን እንዲሁም የከተማዋን ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ለዚህ ዘመቻ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ለ ፕሮግሬ ደ ሊዮ የተባለው ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ይህ እርምጃ . . . አላግባብ የተሠራበት አንድ ቃል እንዳለ ግልጽ አድርጓል። ላለፉት አሥር ዓመታት ‘መናፍቅ’ የሚለው ቃል የነበረው አንድምታ . . . ብልሹ፣ አደገኛና ጎጂ የሚል ነበር። . . . የይሖዋ ምሥክሮች ግን ኅብረተሰቡን የሚያውክ አደገኛ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች አይደሉም።”
የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያውቁ ሰዎች ምሥክሮቹ ሰላማዊ ባሕርይና ኅብረተሰቡ ለሚመራባቸው ሥርዓቶች የጠለቀ አክብሮት እንዳላቸው ይገነዘባሉ። በመሆኑም በመንገድ ላይ የነበሩ ብዙ ሰዎች በዘመቻው ለተካፈሉት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች ያላቸውን አድናቆትና ድጋፍ ገልጸዋል። ሰዎች ስለ ትራክቱ ምስጋናቸውን ለመግለጽ የላኳቸው የስልክ ጥሪዎች፣ የፋክስና የደብዳቤ መልእክቶች መድረስ የጀመሩት ወዲያውኑ ነበር። ከሁሉም በላይ ቅን የሆኑ ሰዎች ከፈጠራና ትርጉም የለሽ አስተያየቶች በተቃራኒ ስለ ምሥክሮቹ እውነታውን ለመስማት አጋጣሚውን አግኝተዋል፤ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት እምነታቸው በመጥፎ ሲነሳባቸው የነበሩት ደግሞ ስሜታቸውን ለመግለጽ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል።