“በእውነተኛው ሕይወት” ተደሰት
ይሖዋ አምላክ ዘላለማዊነትን በሰው አእምሮ ውስጥ አስቀምጧል። (መክብብ 3:11) ይህ ውስጣዊ ስሜት የሰው ልጅ በሞት ፊት ምንም ማድረግ እንደማይችል ሆኖ እንዲሰማው ቢያደርገውም የዚያኑ ያህል ደግሞ በውስጡ ከፍተኛ የመኖር ምኞት ይቀሰቅስበታል።
በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ተስፋ ይሰጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር የሆነው ይሖዋ ዘላለማዊነትን በሰው አእምሮ ውስጥ ከተከለ በኋላ ለጥቂት ዓመታት ብቻ ኖሮ እንዲሞት አያደርግም። በዕጣ ፈንታችን መሠረት ለማሠቃየት ብሎ እኛን መፍጠር ከአምላክ ባሕርይ ጋር በቀጥታ የሚጻረር ተግባር ነው። “ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች” ተደርገን አልተፈጠርንም።—2 ጴጥሮስ 2:12
ይሖዋ አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን ለዘላለም የመኖር ምኞት በውስጣቸው ተክሎ በመፍጠር “እጅግ መልካም” ተግባር አከናውኖ ነበር። ለዘላለም መኖር እንዲችሉ አድርጎ ፈጥሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) የሚያሳዝነው ግን የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ነፃ ምርጫቸውን አለ አግባብ ተጠቅመው ፈጣሪ እንዳይፈጽሙ የነገራቸውን ግልጽ ትዕዛዝ በጣሱ ጊዜ የነበራቸውን ፍጽምና አጡ። በዚህም የተነሳ ለዘሮቻቸው አለፍጽምናንና ሞትን አስተላልፈው ሞቱ።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-24፤ ሮሜ 5:12
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት ዓላማና ስለ ሞት ምንነት በግልጽ ይነግረናል። ሙታን “ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ” እንደሌላቸው እንዲሁም “አንዳች እንደማያውቁ” ይገልጻል። (መክብብ 9:5, 10) በሌላ አነጋገር ሙታን በድን ናቸው። ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ስለዚህ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ የተሰወረ ምንም ምሥጢር የለም።—ዘፍጥረት 3:19፤ መዝሙር 146:4፤ መክብብ 3:19, 20፤ ሕዝቅኤል 18:4a
ይሖዋ የዓላማ አምላክ ነው፤ ምድርን “ለከንቱ” አልፈጠራትም። ምድርን የሠራት ገነት በሆነ ሁኔታ ፍጹማን ሰዎች ‘የሚኖሩባት’ ቦታ እንድትሆን ሲሆን አሁንም ቢሆን ይህ ዓላማው አልተለወጠም። (ኢሳይያስ 45:18፤ ሚልክያስ 3:6) ይህንን ዓላማውን እውን ለማድረግ ልጁን ወደ ምድር ላከ። ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ የታመነ በመሆን የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ለመቤዠት የሚቻልበትን መንገድ ከፍቷል። እንዲያውም ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 3:16
ከብዙ ጊዜያት በፊት አምላክ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚፈጥር ቃል ገብቶ ነበር። (ኢሳይያስ 65:17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ይህም ለሰማያዊ ሕይወት የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች መምረጥንም ያካትት ነበር። እነርሱም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሆነው አንድ ማዕከላዊ መስተዳደር ይመሠርታሉ። “በምድር ያሉትን ሁሉ” የሚያስተዳድረውን ይህን መንግሥት መጽሐፍ ቅዱስ “መንግሥተ ሰማያት” ወይም “የእግዚአብሔር መንግሥት” በማለት ይጠራዋል። (ማቴዎስ 4:17፤ 12:28፤ ኤፌሶን 1:10፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3) አምላክ በምድር ላይ ያሉትን አምላክ የለሾች ሁሉ ከደመሰሰና ምድርን ካጸዳ በኋላ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ወይም “አዲስ ምድር” ያመጣል። ይህ፣ አምላክ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ ከሚያመጣው ጥፋት ጠብቆ የሚያተርፋቸውን ሰዎች ይጨምራል። (ማቴዎስ 24:3, 7-14, 21፤ ራእይ 7:9, 13, 14) በትንሣኤ ተስፋ አማካኝነት ከሞት ወደ ሕይወት የሚመለሱ ሰዎች በሕይወት ከሚተርፉት ጋር ይቀላቀላሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
ከዚያም “እውነተኛው ሕይወት”
አምላክ ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚኖረው አስደሳች ሕይወት ማረጋገጫ ሲሰጥ “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ራእይ 21:5) አምላክ ወደፊት ለሰው ዘር የሚያደርጋቸውን አስደናቂ ነገሮች በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ አእምሮ ሙሉ በሙሉ ሊረዳው አይችልም። ኤደንን የመሰለ ገነት በመላው ምድር ላይ ይፈጥራል። (ሉቃስ 23:43) በኤደን እንደነበረው ሁሉ በመጪው ገነትም ውበት የተላበሱ ነገሮች፣ ማራኪ ቀለማት፣ ለመስማት ደስ የሚል ድምፅና ጥሩ ጣዕም ያላቸው ነገሮች ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ያንን ጊዜ በማስመልከት “የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ብሎ ስለሚናገር ድህነትና የምግብ እጥረት ፈጽሞ አይኖርም። (ራእይ 21:4፤ መዝሙር 72:16) በሽታ ለዘላለም ስለሚወገድ “ታምሜአለሁ” የሚል ሰው አይኖርም። (ኢሳይያስ 33:24) አዎን፣ የሰው ልጆች የረዥም ጊዜ ጠላት የሆነው ሞትን ጨምሮ በሽታ የሚያስከትሉ ነገሮች ሁሉ ይወገዳሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ሐዋርያው ዮሐንስ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር የሚተዳደረውን አዲስ የሰው ልጆች ኅብረተሰብ ማለትም የ“አዲስ ምድር” ራእይ ከተመለከተ በኋላ “እንባዎችንም ሁሉ [አምላክ] ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” የሚል ድምፅ ሰማ። ከዚህ መለኮታዊ ተስፋ የተሻለ ለሰው ልጆች መጽናኛና እፎይታ ሊሰጥ የሚችል ምን ነገር ይኖራል?
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ስለሚኖረው ሕይወት መግለጫ ሲሰጥ የሰውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ስለሚያሟሉ ሁኔታዎች ጎላ አድርጎ ይገልጻል። የሰው ልጅ እስከ አሁን ድረስ ቢታገልላቸውም ሊጨብጣቸው ያልቻላቸው ነገሮች ሁሉ በዚያን ወቅት ሙሉ በሙሉ እውን ይሆናሉ። (ማቴዎስ 6:10) ከእነዚህ መካከል አንዱ ጨቋኝ ገዥዎች በሰዎች ላይ በሚያደርሱት እንግልት ምክንያት ፍጻሜውን ሳያገኝ የቀረው ፍትሕ የማግኘት ፍላጎት ነው። (መክብብ 8:9) መዝሙራዊው በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ስለሚኖረው ሁኔታ በትንቢት ሲናገር “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ሰላምም ብዙ ይሆናል” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 72:7፣ ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል
ብዙዎች ከፍተኛ መሥዋዕትነት የከፈሉለት ሌላው ፍላጎት ደግሞ እኩልነት ነው። “በዳግም ፍጥረት” ጊዜ አምላክ መድሎን ከሥሩ ነቅሎ ያጠፋዋል። (ማቴዎስ 19:28 NW) ሁሉም ሰው እኩል ክብር ይኖረዋል። ይህ አንዳንድ አምባ ገነን መንግሥታት በግድ ለማስፈን የሞከሩት ዓይነት እኩልነት አይደለም። በተቃራኒው ግን ስግብግብነትንና ኩራትን ጨምሮ ሰዎች በሌሎች ላይ እንዲሰለጥኑ ወይም ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት እንዲያግበሰብሱ የሚያደርጓቸው የመድሎኝነት መንስኤዎች ይወገዳሉ። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ተንብዮአል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22
በግለሰብም ሆነ በጅምላ በተደረጉ ጦርነቶች ሳቢያ በፈሰሰው ደም የሰው ልጅ ምንኛ ሥቃይ ደርሶበታል! ይህም ከአቤል መገደል አንስቶ በዘመናችን እየተካሄዱ እስካሉት ጦርነቶች ድረስ ዘልቋል። የሰው ልጅ ከዛሬ ነገ ሰላም ይሰፍናል እያለ በከንቱ ለረጅም ጊዜ ሲጠባበቅ ኖሯል! ተመልሳ በምትቋቋመው ገነት ሁሉም ሰው ሰላማዊና ገር ይሆናል፤ “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11
ኢሳይያስ 11:9 “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች” ይላል። በወረስነው አለፍጽምናና በሌሎች ምክንያቶች በዛሬው ጊዜ የእነዚህን ቃላት ምንነት ሙሉ በሙሉ መረዳት ያዳግተናል። ፍጹም የሆነው የአምላክ እውቀት ከእርሱ ጋር እንዴት አንድ እንደሚያደርገንና ይህም ዝምድና የተሟላ ደስታ የሚያስገኘው እንዴት እንደሆነ የምናውቀው ገና ወደፊት ነው። ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ በኃይል፣ በጥበብ፣ በፍትሕና በፍቅር አቻ የማይገኝለት ድንቅ አምላክ እንደሆነ ስለሚነግሩን “የአዲሱ ምድር” ነዋሪዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት እንደሚሰማ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
“እውነተኛው ሕይወት” መምጣቱ የማይቀር ነው—አጥብቀህ ያዘው!
በጣም ጥሩ በሆነ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር ለአንዳንዶች ሕልም ወይም ቅዠት ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ከልብ እምነት ያሳደሩ ሰዎች ይህ ተስፋ ይፈጸማል ብለው በትምክህት ይጠባበቃሉ። ይህ ለሕይወታቸው ልክ እንደ መልሕቅ ነው። (ዕብራውያን 6:19) መልሕቅ አንድ መርከብ ባለበት ረግቶ እንዲቆምና ወዲያ ወዲህ እንዳይል ገትሮ እንደሚይዘው ሁሉ የዘላለም ሕይወት ተስፋም ሰዎች ጽኑና እርግጠኞች እንዲሆኑ እንዲሁም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲጋፈጡና ከዚያም አልፈው እንዲያሸንፉ ይረዳቸዋል።
አምላክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። እንዲያውም የገባውን ቃል እንደማያጥፍ በመሃላ በማረጋገጥ ዋስትና ሰጥቶናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፣ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፣ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ . . . ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፣ በመሐላ በመካከል ገባ።” (ዕብራውያን 6:17, 18) አምላክ ፈጽሞ የማይሽራቸው ‘ሁለቱ የማይለወጡ ነገሮች’ የገባው ቃልና መሐላው ናቸው። የእኛም ተስፋ የተመሠረተው በእነዚህ ላይ ነው።
አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ማሳደር ከፍተኛ ማጽናኛና መንፈሳዊ ጥንካሬ ይሰጣል። የእስራኤል ሕዝብ መሪ የነበረው ኢያሱ እንዲህ የመሰለ እምነት ነበረው። ኢያሱ ለእስራኤላውያን የመሰነባበቻ ቃላት በተናገረ ጊዜ በጣም ሸምግሎ የነበረ ሲሆን የመሞቻውም ቀን መቃረቡን አውቆ ነበር። ሆኖም አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ከነበረው ፍጹም እምነት የመነጨ ጥንካሬና የማይናወጥ ታማኝነት አሳይቷል። ኢያሱ “የምድርን ሁሉ መንገድ” ማለትም መላውን የሰው ዘር ወደ ሞት በሚያደርሰው ጎዳና ላይ እንደተጓዘ ከገለጸ በኋላ “እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም” በማለት ተናገረ። አዎን፣ አምላክ የገባቸውን ተስፋዎች በሙሉ እንደሚጠብቅ ኢያሱ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ገልጿል።—ኢያሱ 23:14
አንተም አምላክ ቃል በገባውና በቅርቡ በሚቋቋመው አዲስ ዓለም ላይ ተመሳሳይ እምነት ማሳደር ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር በማጥናት ይሖዋ ማን እንደሆነና ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ ትምክህት መጣል ያለብህ ለምን እንደሆነ ትረዳለህ። (ራእይ 4:11) አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሌሎች በጥንት ጊዜ የነበሩ የእምነት ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በቅርብ ያውቁት ስለነበር የማይነቃነቅ እምነት ነበራቸው። በሕይወት በነበሩበት ጊዜ “የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል” ባያገኙም እንኳ ጠንካራ ተስፋ ይዘው ኖረዋል። “ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት።”—ዕብራውያን 11:13
ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በተረዳነው መሠረት ምድር ከማንኛውም ዓይነት ክፋት የምትጸዳበት ‘ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን’ እንደቀረበ አውቀናል። (ራእይ 16:14, 16) እንደ ጥንቶቹ የታመኑ ሰዎች በእምነት፣ ለአምላክና “ለእውነተኛው ሕይወት” ባለን ፍቅር በመገፋፋት ወደፊት የሚፈጸሙ ክስተቶችን በልበ ሙሉነት መጠባበቅ ይገባናል። የአዲሱ ዓለም መቅረብ በይሖዋ ለሚያምኑና እርሱን ለሚወዱት ከፍተኛ ማበረታቻ ይሆናቸዋል። የአምላክን ሞገስ ለማግኘትና በቅርቡ ከሚመጣው ታላቅ ቀን እንዲጠብቀን እንዲህ ያለውን እምነትና ፍቅር ማዳበር ይኖርብናል።—ሶፎንያስ 2:3፤ 2 ተሰሎንቄ 1:3፤ ዕብራውያን 10:37-39
ታዲያ ሕይወትን ትወዳለህ? እንዲሁም የወደፊቱን አስደሳች ጊዜ ተስፋ በማድረግ፣ አዎን፣ ዘላለማዊነትን በአእምሮህ በመያዝ ከአሁኑ ጊዜ የተሻለ “እውነተኛ ሕይወት” ማለትም ተቀባይነት ያለው የአምላክ አገልጋይ በመሆን የሚገኘውን ሕይወት ትመኛለህን? ይህን የምትሻ ከሆነ ‘ተስፋችሁን በሚያልፍ ባለ ጠግነት ላይ ሳይሆን በአምላክ ላይ አድርጉ’ በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠንን ጥብቅ ማሳሰቢያ ተከተል። በመቀጠል ጳውሎስ ‘እውነተኛውን ሕይወት ትይዙ ዘንድ’ ለአምላክ ክብር በሚያስገኝ “በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች” ሁኑ በማለት ጽፏል።—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የሚቀርብልህን ግብዣ በመቀበል “የዘላለም ሕይወት” የሚያስገኘውን እውቀት ልትቀስም ትችላለህ። (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን በፍቅር ላይ የተመሠረተ አባታዊ ግብዣ መዝግቦልናል:- “ልጄ ሆይ፣ ሕጌን አትርሳ፣ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።”—ምሳሌ 3:1, 2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ስንሞት ምን እንሆናለን? የተባለውን በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመውን ብሮሹር ተመልከት።