የግሪክ ፍልስፍና ለክርስትና መዳበር አስተዋጽኦ አድርጓልን?
“ክርስትና አረማዊውን የግሪክና የሮም ባህል የሚቃወም ቢሆንም በርካታ ፍልስፍናዎቻቸውን ወርሷል።” —ዚ ኢንሳይክለፒዲያ አሜሪካና
በ“ክርስቲያናዊ” አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ካሳደሩ ሰዎች መካከል “ቅዱስ” አውግስጦስ አንዱ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ በሚለው መሠረት “የአዲስ ኪዳን ሃይማኖት ከፕላቶንያዊው የግሪክ ፍልስፍና ወግ ጋር ለመዋሃድ የበቃው በአውግስጦስ አማካኝነት ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ የዚህ ውህደት ውጤት ወደ መካከለኛው ዘመን የሮማ ካቶሊክ እምነትና በማንሰራራት ላይ ወደነበረው የፕሮቴስታንት እምነት የተላለፈው በእሱ አማካኝነት ነው።”
አውግስጦስ ትቶት ያለፈው ነገር በእርግጥም እስከ ጊዜያችን ድረስ ዘልቋል። የግሪክ ፍልስፍና በሕዝበ ክርስትና ላይ ስላሳደረው ከፍተኛ ተጽእኖ ሲናገሩ ዳግላስ ቲ ሆልደን እንዲህ ብለዋል:- “የክርስትና ትምህርት ከግሪክ ፍልስፍና ጋር በደንብ ከመዋሃዱ የተነሣ 90 በመቶ የግሪክ አስተሳሰብና 10 በመቶ የክርስትና አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦችን አፍርቷል።”
አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን እንዲህ ያለው ፍልስፍናዊ ተጽእኖ ለጋ የነበረውን ክርስትና እንዳሳደገው፣ ትምህርቱን እንዳዳበረለትና ይበልጥ አሳማኝ እንዳደረገው አጥብቀው ያምናሉ። ይህ እውነት ነውን? የግሪክ ፍልስፍና ተጽእኖውን ያሳደረው እንዴትና መቼ ነበር? በእርግጥ ክርስትናን አዳብሮታል ወይስ በክሎታል?
ከሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አንስቶ እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የተከናወኑ በርካታ ጉዳዮችን ለመገንዘብ የሚከተሉትን አራት እንግዳ ስያሜዎች መመርመሩ እውቀትን የሚጨምር ነው:- (1) “ሄለናዊ የአይሁድ እምነት፣” (2) “ክርስቲያናዊ ሄለናዊነት፣” (3) “ሄለናዊ ክርስትና፣” እና (4) “ክርስቲያናዊ ፍልስፍና።”
“ሄለናዊ የአይሁድ እምነት”
በመጀመሪያ ላይ የሚገኘው “ሄለናዊ የአይሁድ እምነት” እርስ በርሱ የሚቃረን ነው። በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ የተቋቋመው የመጀመሪያው የዕብራውያኑ ሃይማኖት በሐሰት ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች መበከል አልነበረበትም። (ዘዳግም 12:32፤ ምሳሌ 30:5, 6) ይሁን እንጂ ገና ሀ ብሎ ሲጀመር ንጹሕ አምልኮ ዙሪያውን በከበቡት የሐሰት ሃይማኖት ልማዶችና አስተሳሰቦች ይኸውም ግብጻውያንን፣ ከነዓናውያንንና ባቢሎናውያንን ከመሳሰሉ ምንጮች በሚደርስበት ተጽእኖ የመበከል አደጋ ተደቀነበት። የሚያሳዝነው ነገር እስራኤላውያን እውነተኛው አምልኮ እንዲበከል ፈቀዱ።—መሳፍንት 2:11-13
ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ በታላቁ እስክንድር አማካኝነት በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የጥንቷ ፍልስጥኤም በግሪክ ግዛት ሥር ስትሆን ይህ ብክለት ዘላቂ የሆነ መጥፎ ቅርስ ትቶ አልፏል። እስክንድር አይሁዳውያንን እየመለመለ ወደ ሠራዊቱ አስገባ። በአይሁዳውያንና በአዲሱ አስተዳዳሪያቸው መካከል የነበረው ግንኙነት በአይሁድ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። ሄለናዊ አስተሳሰብ በአይሁዳዊ ትምህርት ውስጥ ሰርጾ ገባ። ሊቀ ካህናት ጄሰን የሆሜርን ጥናት ለማስፋፋት ሲል በ175 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ውስጥ የግሪክ ትምህርት ቤት እንዳቋቋመ ይነገርለታል።
በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ይጽፍ የነበረ አንድ ሳምራዊ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ሄለናዊ ታሪክ አስመስሎ ለማቅረብ ሙከራ ማድረጉ ትኩረት የሚስብ ነው። ዮዲትንና ጦቢትን የመሳሰሉ የአይሁዳውያን አዋልድ መጻሕፍት የጾታ ስሜትን የሚያነሣሡ ግሪካዊ አፈ ታሪኮችን የያዙ ናቸው። የግሪክን አስተሳሰብ ከአይሁድ ሃይማኖትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማስማማት የሞከሩ በርካታ አይሁዳውያን ፈላስፋዎች ተነሥተው ነበር።
ይህን በማድረግ ከፍተኛ ታዋቂነትን ያገኘው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው አይሁዳዊው ፊሎ ነው። የፕላቶን (አራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ)፣ የፓይታጎሪያውያንንና የኢስጦኢኮችን መሠረተ ትምህርቶች ተጠቅሟል። የፊሎ አስተሳሰብ በአይሁዳውያን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። በምሁራን ደረጃ የግሪክ አስተሳሰብ ወደ አይሁድ ባህል ሰርጎ የመግባቱን ጉዳይ ጠቅለል አድርገው ሲገልጹ አይሁዳዊው ደራሲ ማክስ ዲመንት እንዲህ ይላሉ:- “በፕላቶንያዊ አስተሳሰብ፣ በአሪስቶትሊያዊ ምርምርና በኢዩክሊዲያን ሳይንስ የዳበረ እውቀት ያላቸው አይሁዳዊ የሆኑ የሃይማኖት ምሁራን ቶራህን ለየት ባለ መንገድ መመርመር ጀመሩ። . . . ለአይሁዳዊ ራእዮች ግሪካዊ ማብራሪያ መስጠታቸውን ቀጠሉ።”
ከጊዜ በኋላ ሮማውያን የግሪክን ግዛት በመቆጣጠር ኢየሩሳሌምን ተረከቡ። ይህ ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ለውጦች እንዲደረጉ መንገድ ከፍቷል። በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የፕላቶን አስተሳሰብ ለማዳበርና ለማቀናበር ጥረት ያደረጉ ፈላስፎች የነበሯቸው ፍልስፍናዊና ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች ወጥ የሆነ ቅርጽ በመያዝ በዛሬው ጊዜ ኒኦፕላቶኒዝም በሚል ጠቅለል ያለ ስም የሚታወቁ ሆነዋል። እነዚህ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በከሃዲዋ ክርስትና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደራቸው አልቀረም።
“ክርስቲያናዊ ሄለናዊነት”
የዘመናችን አቆጣጠር ከጀመረ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ አምስት ምዕተ ዓመታት የተወሰኑ ምሁራን የግሪክ ፍልስፍናና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እውነት ዝምድና እንዳላቸው አስመስለው ለማቅረብ ሞክረው ነበር። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያኒቲ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ክርስቲያን ፈላስፎች ከክርስቶስ በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት የነበሩ ግሪካውያንን የአምላክን እውቀት ለማግኘት በቁርጠኝነት ሆኖም በጭፍን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ኢየሱስ ምን እንደሚመስል ለመገመትና በአረማዊ አስተሳሰብ ከተሞላው ከንቱ አእምሯቸው ክርስትናን ለመፍጠር የሚሞክሩ ሰዎች አድርገው ሊስሏቸው ሞክረው ነበር።”
ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች መካከል ቀዳሚ የነበረው ፕሎቲነስ (205-270 እዘአ) በአብዛኛው የፕላቶን ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ያደረገ ሥርዓት አቋቁሞ ነበር። ፕሎቲነስ ነፍስ ከሥጋ የተለየች ነች የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ አስተዋውቋል። ፕሮፌሰር ኢ ደብልዩ ሆፕኪንስ ፕሎቲነስን አስመልክተው ሲናገሩ “ሃይማኖታዊ ትምህርቱ የክርስትናን አስተሳሰብ በሚያራምዱ መሪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል” ብለዋል።
“ሄለናዊ ክርስትና” እና “ክርስቲያናዊ ፍልስፍና”
ከሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ አንስቶ “ክርስቲያናዊ” ፈላስፎች አረማዊ ምሁራንን ለመማረክ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር” ስለ መራቅ የሰጠውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት እነዚህ አስተማሪዎች በአካባቢያቸው ከሚገኘው ሄለናዊ ባህል ፍልስፍናዊ ትምህርቶችን ቀድተዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:20) የፊሎ አርአያነት መጽሐፍ ቅዱስን ከፕላቶንያዊ አስተሳሰቦች ጋር ለማዋሃድ ይቻላል የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ይመስል ነበር።—ከ2 ጴጥሮስ 1:16 ጋር አወዳድር።
በመሠረቱ ይህ ነገር ትልቅ ተጽእኖ ያሳደረው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ነው። “ክርስቲያን” አስተማሪዎች ክርስትና ከግሪክና ከሮም የሰብዓዊነት ፍልስፍና ጋር የሚስማማ መሆኑን ለማሳየት ሞክረዋል። የእስክንድርያው ክሌመንትና ኦሪጀን (ሁለተኛና ሦስተኛ መቶ ዘመን እዘአ) ኒኦፕላቶኒዝምን “ክርስቲያናዊ ፍልስፍና” ተብሎ ለተሰየመው የፍልስፍና ዓይነት መሠረት አድርገው ተጠቅመውበታል። የሚላኑ ቢሾፕ አምብሮስ (339-397 እዘአ) “ዘመናዊ የሆነውን የግሪክ፣ የክርስትናና የአረማዊ ትምህርቶች እውቀት ከመቅሰሙም በላይ የኒኦፕላቶኒዝም ተከታይ የነበረው የአረማዊው ፕሎቲነስ ሥራዎች የላቀ እውቀት ነበረው።” ምሁራን ለሆኑ ላቲናውያን ክርስትናን በሚጥም መንገድ ለማቅረብ ሞክሯል። አውግስጦስም የእሱን ፈለግ ተከትሏል።
ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ የአሪዮፓጋይቱ ዲዮናስዮስ (ዲዮናስዮስ እውነተኛ ስሙ እንዳልሆነ ይነገራል)፣ ሶሪያዊ መነኩሴ ሳይሆን አይቀርም፣ ኒኦፕላቶኒክ ፍልስፍናን “ከክርስቲያናዊ” ፍልስፍና ጋር ለማዋሃድ ጥረት አድርጓል። አንድ ኢንሳይክለፒዲያ እንዳለው ከሆነ “መጣጥፎቹ አንድ ወጥ የሆነ የኒዮፕላቶኒክ ዝንባሌ በመካከለኛው ዘመን በነበረው በአብዛኛው የክርስትና መሠረተ ትምህርትና መንፈሳዊነት ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ አድርገዋል . . . በዚህም የተነሳ የክርስትና መሠረተ ትምህርት የተለያዩ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ገጽታውን እስከ ዘመናችን ድረስ እንደያዘ ሊቀጥል ችሏል።” ጳውሎስ ‘በሰው ወግ ላይ የተመሠረተ ፍልስፍናንና ከንቱ ማታለያን’ በመቃወም የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ፊት ለፊት የሚቃረን ነው!—ቆላስይስ 2:8
የሚበክሉ ትምህርቶች
“ክርስቲያን ፕላቶንያውያን ለራእዮች ቅድሚያ ይሰጡ እንደነበርና ፕላቶንያዊ ፍልስፍናን ደግሞ የቅዱስ ጽሑፉን ትምህርቶችና የቤተ ክርስቲያንን ወግ ለማስተዋልና ለመከላከል የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ መሣሪያ አድርገው ይመለከቱት” እንደነበር ታውቋል።
ፕላቶ ራሱ በነፍስ አለመሞት ያምን ነበር። ወደ “ክርስቲያናዊ” የሃይማኖት ትምህርት ሰርገው ከገቡት አበይት የሐሰት ትምህርቶች መካከል አንደኛው ነፍስ አትሞትም የሚለው እንደሆነ ግልጽ ነው። ክርስትና በብዙሃኑ ዘንድ ማራኪ እንዲሆን ሲባል ይህን ትምህርት መቀበል ትምህርቱን ትክክለኛ አያደርገውም። ሐዋርያው ጳውሎስ የግሪክ የባህል ማዕከል በሆነችው በአቴና በሚሰብክበት ወቅት ፕላቶንያዊውን የነፍስ መሠረተ ትምህርት አላስተማረም። ከዚያ ይልቅ፣ ምንም እንኳን ግሪካውያን አድማጮቹ የሚናገረውን ነገር ለመቀበል ቢያዳግታቸውም ስለ ትንሣኤ የሚናገረውን ክርስቲያናዊ መሠረተ ትምህርት አስተምሯል።—ሥራ 17:22-32
ከግሪክ ፍልስፍና በተቃራኒ ቅዱሳን ጽሑፎች ነፍስ አንድ ሰው ያለው ነገር ሳትሆን ራሱ ሰውየው መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 ትርጉም) በሞት ጊዜ ነፍስ ከሕልውና ውጭ ትሆናለች። (ሕዝቅኤል 18:4) መክብብ 9:5 እንዲህ ይለናል:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም።” መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ አትሞትም የሚለውን መሠረተ ትምህርት አያስተምርም።
ሌላው አሳሳች ትምህርት ደግሞ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረውን ሥልጣን ማለትም ከአባቱ ጋር እኩል ነው የሚለውን እምነት የሚመለከት ነው። ዘ ቸርች ኦቭ ዘ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “የሥላሴ መሠረተ ትምህርት . . . ከአይሁዳውያንም ሆነ ከክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ፍጹም የተለየ ምንጭ ያለው ነው።” ይህ ምንጭ ምን ነበር? መሠረተ ትምህርቱ “ከዳበረ በኋላ በፕላቶንያዊ አባቶች አማካኝነት በክርስትና ላይ የተቀጠለ ነበር።”
በእርግጥም ጊዜ እያለፈ ሲሄድና ኒኦፕላቶኒዝም በቤተ ክርስቲያን አባቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ሲያይል ለሥላሴ አማኞች ምቹ ሆነላቸው። የሦስተኛው መቶ ዘመን ኒኦፕላቶንያዊ ፍልስፍና ሦስት አካላት ያሉትን አምላክ አንድ አምላክ አስመስሎ በማቅረብ ረገድ የማይጣጣመውን እንዲጣጣም ለማድረግ ያስቻላቸው መስሎ ነበር። በፍልስፍናዊ ማስረጃ አማካኝነት ሦስት አካላት የየራሳቸውን ስብዕና እንደያዙ አንድ አምላክ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ተናገሩ!
ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱሱ እውነት ይሖዋ ብቸኛ እውነተኛ አምላክ መሆኑን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ከእሱ የሚያንስና እሱ የፈጠረው ልጁ መሆኑንና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ አንቀሳቃሽ ኃይሉ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። (ዘዳግም 6:4፤ ኢሳይያስ 45:5፤ ሥራ 2:4፤ ቆላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14) የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ የሚያዋርድና ሰዎችን ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም በላይ ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት ከማይችሉት አምላክ እንዲርቁ የሚያደርግ ነው።
በክርስቲያን አስተሳሰብ ላይ ተጽእኖ ያሳደረው የኒኦፕላቶኒክ ፍልስፍና ሌላኛው ሰለባ ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊው የሺህ ዓመት ተስፋ ነው። (ራእይ 20:4-6) ኦሪጀን የሺህ ዓመት አማኞችን ያወግዝ እንደነበር ይነገራል። ስለ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚናገረውን ይህን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርት አጥብቆ የተቃወመው ለምን ነበር? ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክለፒዲያ “[ኦሪጀን] መሠረተ ትምህርቶቹ የታነጹት በኒኦ-ፕላቶኒዝም ፍልስፍና ላይ በመሆኑ . . . ከሺህ ዓመት አማኞች ጋር ሊወግን አልቻለም” በማለት መልሱን ይሰጣል።”
እውነቱ
ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በሙሉ እውነት ከሆነው ነገር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። ይህ እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች በሙሉ የሚያጠቃልል ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:2፤ ቲቶ 1:1, 14፤ 2 ዮሐንስ 1-4) መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የእውነት ምንጭ ነው።—ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
ይሁን እንጂ የይሖዋ፣ የእውነት፣ የሰው ዘርና የዘላለም ሕይወት ጠላት፣ “ነፍሰ ገዳይ” እና “የሐሰት አባት” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ይህን እውነት ለመበረዝ በተለያዩ የተንኮል ዘዴዎች ተጠቅሟል። (ዮሐንስ 8:44፤ ከ2 ቆሮንቶስ 11:3 ጋር አወዳድር።) የክርስቲያናዊ ትምህርቶችን ይዘትና ባሕርይ ለመለወጥ ከተጠቀመባቸው እጅግ ኃይለኛ መሣሪያዎቹ መካከል የራሱን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁት የግሪክ ፍልስፍና አረማዊ ትምህርቶች ይገኙበታል።
በክርስቲያናዊ ትምህርት ላይ የግሪክ ፍልስፍናን መቀላቀል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመበረዝ የተደረገ ጥረት ሲሆን ያለውን ኃይል የሚያዳክም ከመሆኑም በላይ ለገሮች፣ ለቅኖችና የመማር ፍላጎት ላላቸው እውነት ፈላጊዎች ማራኪ እንዳይሆን የሚያደርግ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:1, 2, 19, 20) በተጨማሪም ጥርት ያለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረተ ትምህርት በመበከል በእውነትና በሐሰት መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ እንዳይታይ አድርጓል።
ዛሬ፣ የጉባኤው ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት እውነተኛው የክርስትና ትምህርት እንደገና ተቋቁሟል። በተጨማሪም እውነትን የሚፈልጉ ቅን ሰዎች እውነተኛውን የክርስቲያን ጉባኤ በሚያፈራቸው ፍሬዎች በቀላሉ ሊለዩት ይችላሉ። (ማቴዎስ 7:16, 20) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ያልተበከሉ የእውነት ውኃዎችን እንዲያገኙ ለመርዳትና በአባታችን በይሖዋ የተዘረጋውን የዘላለም ሕይወት ውርሻ እንዲጨብጡ ለማገዝ የይሖዋ ምሥክሮች ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ናቸው።—ዮሐንስ 4:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:19
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አውግስጦስ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የግሪክ ጽሑፍ:- ኤንሸንት ግሪክ ራይተርስ ከተባለው መጽሐፍ:- Plato’s Phaedo, 1957, Ioannis N. Zacharopoulos, Athens; ፕላቶ:- Musei Capitolini, Roma