የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 9/1 ገጽ 25-29
  • ይሖዋ ዐለት ሆኖልኛል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ዐለት ሆኖልኛል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መንፈሳዊ ቤተሰብ ማግኘት
  • ብቸኛ አቅኚ
  • ስደትንና የግዞትን ኑሮ በጽናት መቋቋም
  • ተቃውሞ እያለ የተገኘ ጭማሪ
  • ይሖዋ፣ “መድኃኒቴ”
  • በደረሰብኝ ከባድ መከራ ተፈተንኩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ‘መሻገር’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ቸል የተባለው የሙት ልጅ አፍቃሪ አባት አገኘ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ለይሖዋ የሚገባውን መስጠት ቲሞሊዮን ቫሲሊዮ እንደተናገረው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 9/1 ገጽ 25-29

ይሖዋ ዐለት ሆኖልኛል

ኢማኑኤል ሊዮኑዳኪስ እንደተናገረው

እናቴ “በውሳኔህ የምትጸና ከሆነ ቤቱን ለቀህ መሄድ አለብህ” ስትል አምርራ ተናገረችኝ። ስለ አምላክ መንግሥት ሙሉ ጊዜ ለመስበክ ወስኜ ነበር። ሆኖም በተደጋጋሚ መታሰሬ ቤተሰቦቼ ስማቸው እንደጎደፈ ሆኖ እንዲሰማቸው አደረገ።

ወላጆቼ ትሑትና አምላክን የሚፈሩ ነበሩ። በግሪኳ ቀርጤስ ደሴት ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው ዱሊአና በሚባል መንደር ይኖሩ የነበረ ሲሆን እኔም በ1908 የተወለድኩት በዚሁ መንደር ነው። አምላክን መፍራትና ማክበር እንዳለብኝ ከልጅነቴ ጀምረው አስተምረውኛል። ምንም እንኳ አስተማሪዎችም ሆኑ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄሶች መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው አይቼ ባላውቅም ለአምላክ ቃል ፍቅር ነበረኝ።

አንድ ጎረቤታችን በሲ ቲ ራስል የተዘጋጁትን ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ የተባሉትን ስድስት ጥራዞችና ዘ ሃርፕ ኦቭ ጎድ የተባለውን መጽሐፍ ካነበበ በኋላ ያገኛቸውን ዓይን የሚገልጡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች በአድናቆት አካፈለኝ። እነዚህ መጻሕፍት በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ በነበሩት በይሖዋ ምሥክሮች የታተሙ ነበሩ። በአቴንስ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ አንድ መጽሐፍ ቅዱስና የተለያዩ መጻሕፍትን በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ። ከዚህ ጎረቤታችን ጋር ወደ ይሖዋ በመጸለይና በሻማ ብርሃን በእነዚህ ጽሑፎች እገዛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማጥናት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እናመሽ የነበረው ትዝ ይለኛል።

አዲስ ያገኘሁትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለሌሎች ማካፈል ስጀምር እድሜዬ 20 ዓመት ሲሆን በአቅራቢያችን ባለ መንደር በሚገኝ ትምህርት ቤት አስተማሪ ነበርኩ። ወዲያው በዱሊአና የምንገኝ አራታችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ዘወትር አንድ ላይ መሰብሰብ ጀመርን። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሰሙ ለመርዳት ትራክቶችን፣ ቡክሌቶችን፣ መጻሕፍትንና መጽሐፍ ቅዱሶችን እናሰራጭ ነበር።

በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስም ከተቀበሉት በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ነበርን። (ኢሳይያስ 43:​10) በቀጣዩ ዓመት አዲሱን ስማችንንና ትርጉሙን ለባለሥልጣናት በማሳወቁ ዘመቻ ተካፈልን። ይህ ደግሞ ለዚህ ሲባል የተዘጋጀውን ቡክሌት በአካባቢያችን ለሚገኙ ቄሶች፣ ዳኞች፣ ፖሊሶችና የንግድ ሰዎች ማደልን የሚጨምር ነበር።

እንደተጠበቀው ቄሶች የስደት ማዕበል ቀሰቀሱ። ለመጀመሪያ ጊዜ ተያዝኩና 20 ቀን እንድታሰር ተፈረደብኝ። ከእስር ተለቅቄ ብዙም ሳልቆይ በድጋሚ ተያዝኩና አንድ ወር እንድታሰር ተፈረደብኝ። ዳኛው መስበካችንን ማቆም እንዳለብን ሲነግሩን “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት በሥራ 5:​29 ላይ በሚገኙት ቃላት መልስ ሰጠን። ከዚያም በ1932 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ተወካይ በዱሊአና የሚገኘውን አነስተኛ ቡድናችንን የጎበኘ ሲሆን በዚሁ ጉብኝት ወቅት አራታችንም ተጠመቅን።

መንፈሳዊ ቤተሰብ ማግኘት

በስብከቱ ሥራ የበለጠ ማከናወን ስለፈለግኩ የአስተማሪነት ሥራዬን ለቀቅሁ። ይህ ነገር እናቴን በጣም አናደዳት። ቤቱን ለቅቄ እንድሄድ ጠየቀችኝ። አቴንስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ ፈቃድ በቀርጤስ ኢራቅሊዮን ከተማ የሚገኝ አንድ ወንድም በደስታ አስጠጋኝ። ስለዚህ ነሐሴ 1933 በትውልድ መንደሬ የሚገኙ ወንድሞችና አንዳንድ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች አውቶቡስ ጣቢያ ድረስ መጥተው ሸኙኝ። ይህ ዕለት የማይረሳ ነበር፤ በድጋሚ መቼ እንደምንተያይ ስለማናውቅ ሁላችንም ተላቅሰን ተለያየን።

በኢራቅሊዮን አፍቃሪ ከሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመርኩ። ከሌሎች ሦስት ወንድሞችና ከአንዲት እኅት ጋር በየጊዜው ለጥናትና ለአምልኮ እንገናኝ ነበር። ኢየሱስ የሰጠው የሚከተለው ተስፋ በራሴ ላይ ሲፈጸም ለማየት ችያለሁ:- “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን . . . ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” (ማርቆስ 10:29, 30) በከተማዋና በአቅራቢያዋ በሚገኙ መንደሮች እንድሰብክ ተመደብኩ። ከተማዋን ከሸፈንኩ በኋላ በኢራቅሊዮን እና በላሲቲዮን ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች መስበክ ቀጠልኩ።

ብቸኛ አቅኚ

ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው መንደር ብዙ ሰዓት በእግሬ እጓዝ ነበር። ከዚህም በላይ ጽሑፎች ጊዜያቸውን ጠብቀው ስለማይደርሱን በአንድ ጊዜ በርካታ ኪሎ የሚመዝን ጽሑፍ ተሸክሜ ለመጓዝ እገደድ ነበር። የማድርበት ስለሌለኝ በመንደሩ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ቡና ቤት እገባና የመጨረሻው የቡና ቤቱ ደንበኛ ጠጥቶ እስኪወጣ ድረስ (አብዛኛውን ጊዜ እስከ እኩለ ሌሊት ማለት ነው) ጠብቄ አንድ ረዥም ሶፋ ላይ እተኛለሁ። ከዚያም በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ባለቤቱ መጠጥ መሸጥ ከመጀመሩ በፊት በሌሊት እነሳለሁ። የምተኛባቸው ሶፋዎች የቁንጫ መፈንጫ ናቸው።

ምንም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ቀዝቃዛ ቢሆንም የወጣትነት ጉልበቴን ለይሖዋ በመስጠቴ ደስተኛ ነበርኩ። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያለው ሰው ሳገኝ በዚህ ሕይወት አድን አገልግሎት ለመቀጠል ባደረግኩት ውሳኔ እንድገፋበት ያበረታታኛል። ከዚህም በተጨማሪ ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ ጋር ስገናኝ መንፈሴ ይታደሳል። ከኢራቅሊዮን ከተማ ርቄ እንደምሰብክበት ርቀት መጠን ከ20 እስከ 50 ለሚሆኑ ቀናት ከተለየኋቸው በኋላ እንደገና አገኛቸዋለሁ።

አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ በኢራቅሊዮን የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እኅቶቼ በዚያን ዕለት ምሽት የዘወትር ስብሰባቸውን እንደሚያደርጉ ትዝ ብሎኝ የተሰማኝን የብቸኝነት ስሜት እስከ አሁን አልረሳውም። ላያቸው በጣም ከመናፈቄ የተነሳ ከእነሱ ርቄ ያለሁበትን 25 ኪሎ ሜትር በእግሬ ለመጓዝ ወሰንኩ። እንደዚያ በፍጥነት ተራምጄ አላውቅም። በዚያን ዕለት ምሽት ከወንድሞቼ ጋር ተገናኝቼ አስደሳች ጊዜ ማሳለፌና ለብዙ ጊዜ የሚሆነኝን መንፈሳዊ ስንቅ ማግኘቴ እንዴት የሚያጽናና ነበር!

በትጋት ለመስበክ ያደረኩት ጥረት ብዙም ሳይቆይ ፍሬ ማፍራት ጀመረ። እንደ ሐዋርያት ዘመን ሁሉ ‘ይሖዋ የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእኛ ላይ መጨመሩን ቀጠለ።’ (ሥራ 2:​47) በቀርጤስ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄድ ጀመር። አሁን አብረውኝ የሚያገለግሉ ስላገኘሁ እንደበፊቱ ብቸኝነት አይሰማኝም። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የነበረብንን ችግርና ይደርስብን የነበረውን ኃይለኛ ተቃውሞ በጽናት ተወጥተናል። የዘወትር ምግባችን ዳቦ ሲሆን ለዳቦው ማባያ የሚሆን ነገር የምናገኘው የምንሰብክላቸው ሰዎች ጽሑፍ ወስደው በምትኩ እንደ እንቁላል፣ የወይራ ፍሬ ወይም አትክልት ከሰጡን ብቻ ነው።

በቀርጤስ ደቡባዊ ምሥራቅ በምትገኘው ኢራፔትራ ከተማ ለሚኖር ሚኖስ ኮኪናኪስ ለሚባል አንድ የጨርቃ ጨርቅ ነጋዴ መሰከርኩለት። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ያላሰለሰ ጥረት ባደርግም የሥራው ጠባይ ስለሚያሯሩጠው ጊዜ ማግኘት አልቻለም። ሆኖም በመጨረሻ ጥናቱን በቁምነገር መቀጠል እንዳለበት ከወሰነ በኋላ በሕይወቱ ውስጥ አስደናቂ ለውጦችን አደረገ። እሱም በጣም ቀናተኛና ጎበዝ የምሥራቹ ሰባኪ ሆነ። ኮኪናኪስ ጋር ተቀጥሮ ይሠራ የነበረው የ18 ዓመቱ ኢማኑኤል ፓታራኪስ በእነዚህ ለውጦች በመነካቱ ወዲያው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ እንዲሰጠው ጠየቀ። ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ሲያደርግና በመጨረሻም ሚስዮናዊ ሲሆን በማየቴ በጣም ነው የተደሰትኩት።a

በዚህ ጊዜ በተወለድኩበት መንደር የሚገኘው ጉባኤ ማደጉን የቀጠለ ሲሆን 14 አስፋፊዎች ነበሩት። እኅቴ ደስፒና የላከችልኝ ደብዳቤ የደረሰኝ ዕለት የተሰማኝን ስሜት ፈጽሞ አልረሳውም። ደብዳቤው እሷ እና ወላጆቼ እውነትን እንደተቀበሉና ተጠምቀው የይሖዋ አምላኪዎች እንደሆኑ የሚገልጽ ነበር!

ስደትንና የግዞትን ኑሮ በጽናት መቋቋም

የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የስብከት እንቅስቃሴያችንን ከፍተኛ ውድመት እንደሚያስከትል የአንበጦች መቅሰፍት ስለተመለከተችው ጨፍልቃ ልታጠፋን ቆርጣ ተነሳች። መጋቢት 1938 አንድ የሕዝብ ባለሥልጣን ፊት ቀረብኩና በአስቸኳይ አካባቢውን ለቅቄ እንድሄድ አዘዘኝ። የስብከት ሥራችን በእርግጥ ጠቃሚ እንደሆነና በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዘዘው ሥራ መሆኑንም ገለጽኩለት።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20፤ ሥራ 1:​8

በሚቀጥለው ቀን በከተማው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድኩ። ለሕዝብ አደገኛ እንደሆንኩ ተነገረኝና ከኤጂያን ደሴቶች አንዷ በሆነችው በአሞርጎስ ለአንድ ዓመት በግዞት እንድቆይ ተፈረደብኝ። ከጥቂት ቀናት በኋላ እጄ በካቴና ተጠፍሮ በጀልባ ወደዚህች ደሴት ተወሰድኩ። በአሞርጎስ ደሴት አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። ከስድስት ወር በኋላ አንድ ሌላ የይሖዋ ምሥክር ወደዚህች ደሴት በግዞት መላኩን ስሰማ ምን እንደተሰማኝ ልትገምቱ ትችላላችሁ! ይህ ሰው ማን ይሆን? በቀርጤስ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዬ ሚኖስ ኮኪናኪስ ነበር። መንፈሳዊ ጓደኛ በማግኘቴ የተሰማኝ ደስታ ከፍተኛ ነበር! ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እዚያው አሞርጎስ አጠመቅሁት።b

ወደ ቀርጤስ ከተመለስኩ በኋላ ብዙም ሳልቆይ በድጋሚ ተያዝኩና በዚያች ደሴት ላይ ወደምትገኘው ኒያፐሊስ ከተማ በግዞት ተወሰድኩ። የስድስት ወር ግዞቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ ደግሞ ተይዤ ለአሥር ቀን ታሰርኩ። ከዚያም ኮሚኒስቶች ብቻ ይታሰሩባት ወደነበረችው ደሴት ተላክሁ። “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ አነጋገር ምን ያህል እውነት እንደሆነ ለማስተዋል ችያለሁ።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:12

ተቃውሞ እያለ የተገኘ ጭማሪ

ከ1940-44 ባለው ጀርመን ግሪክን በተቆጣጠረችበት ወቅት የስብከት እንቅስቃሴያችን ሙሉ በሙሉ የቆመ ያህል ሆኖ ነበር። ሆኖም በግሪክ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደገና ስለተደራጁ የስብከት እንቅስቃሴያችንንም እንደ አዲስ ጀመርን። ቀደም ሲል የባከነውን ጊዜ ለማካካስ በማሰብ በመንግሥቱ ሥራ በቅንዓትና በትጋት እንሠራ ነበር።

እንደጠበቅነው ሃይማኖታዊ ተቃውሞ እንደገና ተቀሰቀሰ። ብዙውን ጊዜ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት ሕጉን ለእነሱ እንደሚመቻቸው ለማጣመም ተንኮል ይሠሩ ነበር። በአንድ መንደር አንድ ቄስ የሕዝብ ረብሻ እንዲነሳብን አደረገ። ቄሱ ራሱ ከልጁ ጋር ሆኖ ይደበድበኝ ጀመር። የአገልግሎት ጓደኛዬን በመንደሩ ወደሚገኝ አደባባይ እየጎተቱ ሲወስዱት እኔ ከድብደባው ለማምለጥ ዘልዬ አንድ ቤት ውስጥ ገባሁ። ረብሸኞቹም የአገልግሎት ጓደኛዬን ወደ አደባባዩ ከወሰዱት በኋላ ጽሑፉን ቀዳደዱበት፤ አንዲት ሴት ቤቷ ሰገነት ላይ ቆማ “ግደሉት!” እያለች ትጮህ ነበር። በመጨረሻም አንድ ዶክተርና በዚያ ያልፍ የነበረ አንድ ፖሊስ ደርሰውልን አስጣሉን።

ከዚያም በ1952 እንደገና ተያዝኩና አራት ወር በግዞት እንድቀመጥ የተፈረደብኝ ሲሆን እነዚህን ወራት በቀርጤስ ካስቴሊ ኪሳሞስ በሚባል ቦታ አሳለፍኩ። ከዚያ በኋላ ጉባኤዎችን እንድጎበኝና በመንፈሳዊ እንዳበረታታ ስልጠና ተሰጠኝ። በዚህ የተጓዥነት ሥራ ሁለት ዓመት ካገለገልኩ በኋላ የእኅቴ ሞክሼ የሆነች ዴስፒና የምትባል ታማኝ ክርስቲያን እኅት አገባሁ። አሁንም ታማኝ የይሖዋ አምላኪ ነች። ከሠርጋችን በኋላ እስከ አሁን ድረስ እያገለገልኩባት ባለችው ቀርጤስ በምትገኘው ሐንያ ከተማ ልዩ አቅኚ ሆኜ ተመደብኩ።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው 70 የሚያክሉ ዓመታት 8,300 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋትና 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላትን የቀርጤስ ደሴት በአብዛኛው ሸፍኛለሁ። ከሁሉም በላይ ያስደሰተኝ በዚህች ደሴት በ1930ዎቹ በጣም ጥቂት የነበረው የምሥክሮቹ ቁጥር ዛሬ ከ1,100 በላይ መድረሱ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት እንዲቀስሙና ስለወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ እንዲጨብጡ የመርዳት አጋጣሚ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።

ይሖዋ፣ “መድኃኒቴ”

ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እንዲያውቁ መርዳት ጽናትና ትዕግሥት የሚጠይቅ መሆኑን ከተሞክሮ ተምሬአለሁ። እነዚህን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያት ይሖዋ በልግስና ይሰጣል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው 67 ዓመታት በሚከተሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስል ነበር:- “በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጦም።” (2 ቆሮንቶስ 6:4, 5) በተለይ አገልግሎት በጀመርኩባቸው ዓመታት የነበረኝ የኢኮኖሚ ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነበር። ሆኖም ይሖዋ እኔንም ሆነ ቤተሰቤን አልጣለም። ይሖዋ ዘወትር ደጋፊያችንና ረዳታችን መሆኑን በተግባር አሳይቶናል። (ዕብራውያን 13:5, 6) በጎቹን በመሰብሰብ ረገድም ይሁን ለእኛ የሚያስፈልገንን ነገር በማሟላት የይሖዋን ክንድ ብዙ ጊዜ አይተናል።

ወደኋላ መለስ ብዬ ስመለከት በመንፈሳዊ አነጋገር ምድረ በዳው እንዳበበ አያለሁ፤ ይህ ደግሞ ድካሜ መና እንዳልቀረ ያመለክታል። የወጣትነት ጉልበቴን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቅሜበታለሁ። ከሌላ ከማንኛውም ሥራ ይበልጥ ትልቅ ትርጉም ያለው በሙሉ ጊዜ ያከናወንኩት አገልግሎት ነው። አሁን ዕድሜዬ ቢገፋም ‘በወጣትነት ዕድሜያቸው ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ’ ወጣቶችን በሙሉ ልብ ማበረታታት እችላለሁ።​—⁠መክብብ 12:​1

አሁን የ91 ዓመት ሰው ብሆንም በየወሩ በስብከቱ ሥራ ከ120 ሰዓት በላይ አሳልፋለሁ። በየቀኑ በ1:​30 እነሳና በየመንገዱ፣ በየሱቁና በየመናፈሻው እመሰክራለሁ። በየወሩ በአማካይ 150 መጽሔቶች አበረክታለሁ። የመስማትና የማስታወስ ችግር ሕይወትን አስቸጋሪ እያደረጉብኝ ቢሆንም የመንፈሳዊ ወንድሞቼና እኅቶቼ ማለትም ትልቁ መንፈሳዊ ቤተሰቤ እንዲሁም የሁለቱ ሴት ልጆቼ ቤተሰቦች ድጋፍ አልተለየኝም።

ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ ላይ መታመንን ተምሬአለሁ። ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን “ዓለቴ፣ አምባዬ፣ መድኃኒቴ” መሆኑን በተግባር አይቻለሁ።​—⁠መዝሙር 18:2

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የኢማኑኤል ፓታራኪስን የሕይወት ታሪክ በኅዳር 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 22-7 ላይ ተመልከት።

b ሚኖስ ኮኪናኪስን በሚመለከት ከሕግ አንጻር ስለተገኘው ድል ለማንበብ መስከረም 1, 1993 የወጣውን መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 27-31 ተመልከት። ሚኖስ ኮኪናኪስ ጥር 1999 ሕይወቱ አልፏል።

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከታች:- ከባለቤቴ ጋር፤ በስተግራ:- በ1927፤ በተቃራኒው ገጽ:- በ1939 ከግዞት እንደተመለስኩ በአክሮፖሊስ ከሚኖስ ኮኪናኪስ (በስተግራ) እና ከአንድ ሌላ ምሥክር ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ