መንፈሳዊውን ብርሃን ‘እስከ ምድር ጫፍ’ ለማድረስ የበኩሉን አድርጓል
ሐዋርያው ጳውሎስ መንፈሳዊውን ብርሃን ‘እስከ ምድር ጫፍ’ ለማዳረስ አገልግሏል። በውጤቱም ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ብዙ ሰዎች አማኞች ሆነዋል።’—ሥራ 13:47, 48፤ ኢሳይያስ 49:6
የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዊልያም ሎይድ ቤሪም ሕይወቱን በሙሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ያከናወነው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ይህን መንፈሳዊ ብርሃን የማዳረስ ጥልቅ ፍላጎት እንደነበረው የሚያሳይ ነው። ወንድም ቤሪ በሃዋይ በመካሄድ ላይ በነበረ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ንግግር እያቀረበ ሳለ ሐምሌ 2, 1999 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ሎይድ ቤሪ የተወለደው በኒው ዚላንድ ታኅሣሥ 20, 1916 ነበር። ቀደም ሲል እናቱና አባቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በሚያሰራጫቸው የሲ ቲ ራስል ጽሑፎች ላይ የሚወጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በጉጉት ይከታተሉ ነበር። በመሆኑም ወንድም ሎይድ ቤሪ ያደገው ለአምላክ ባደረ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ ነበር።
ወንድም ቤሪ ስፖርትና ትምህርት ይወድድ የነበረና በሳይንስ ትምህርትም የዲግሪ ማዕረግ ያለው ቢሆንም ዋናው ትኩረቱ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያርፍ አድርጓል። በመሆኑም ጥር 1, 1939 በአውስትራሊያ በሚገኘው የማኅበሩ ቢሮ ውስጥ የቤቴል ቤተሰብ አባል በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። መንግሥት በ1941 በማኅበሩ ላይ እገዳ ከጣለ በኋላም ቢሆን ወንድም ቤሪ የቢሮ ሥራ በመሥራት ያገለገለ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ለመሰል አማኞች ማበረታቻዎችን እንዲጽፍ ይመደብ ነበር። በሕዝባዊ አገልግሎትም ቀዳሚ በመሆን ግሩም ምሳሌ ትቷል።
በየካቲት 1942 ወንድም ቤሪ አንዲት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ አገባ። አፍቃሪ የሆነችው ሚስቱ ሜልባ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በተለያዩ የምድር ክፍሎች አብራው በመዘዋወር በታማኝነት አገልግላለች። በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ11ኛው ክፍል ገብተው መማራቸው ከአገራቸው ውጪ ባለው መስክ ለማገልገል የሚያስችላቸው ትልቅ እርምጃ ነበር። የተመደቡት ብዙዎች ‘የምድር ጫፍ’ አድርገው በሚቆጥሩት በጃፓን ነበር። በኅዳር 1949 እዚያ ከደረሱ በኋላ የወደብ ከተማ በሆነችው በኮቤ በሚስዮናዊነት ማገልገል ጀመሩ። በዚያን ወቅት በጃፓን ምሥራቹን በመስበክ ላይ የነበሩት 12 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ወንድም ቤሪ የአዲሱን መኖሪያውን ቋንቋና ባህርይ በማጥናት ለቀጣዮቹ 25 ዓመታት ከጃፓን ሕዝብ ጋር ያገለገለ ሲሆን ለእነሱ ጥልቅ ፍቅር አድሮበታል። ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ’ ላላቸው ሰዎች የነበረው ፍቅር እያደገ ለሄደው በጃፓን የነበረው ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር ግልጽ ነበር። ይህም በዚያ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ ለአሥርተ ዓመታት ውጤታማ በሆነ መንገድ በበላይ ተመልካችነት ለማስተዳደር አስችሎታል።
በ1975 አጋማሽ ላይ በጃፓን ወደ 30,000 የሚጠጉ ምሥክሮች በነበሩበት ጊዜ ቤሪና ባለቤቱ ወደ ኒው ዮርክ፣ ብሩክሊን ተዛወሩ። ወንድም ቤሪ በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል በመሆን እንዲያገለግል ተጋበዘ። (ሮሜ 8:16, 17) በጽሑፍ ሥራ የነበረው ተሞክሮ በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ በተሰጠው አዲስ የሥራ ምድብ ጠቃሚ ድርሻ እንዲኖረው አስችሎታል። እንዲሁም በቅርንጫፍ ቢሮና በዓለም አቀፍ ሥራ ያካበተው ተሞክሮ የአስተዳደር አካል የኅትመት ኮሚቴ አባል በመሆን ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ ለማበርከት አስችሎታል።
በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ወንድም ቤሪ ለሩቅ ምሥራቅና በዚያ ለሚኖሩ ሰዎች ልዩ ፍቅር ነበረው። የጊልያድ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ሆኑ የቤቴል ቤተሰብ አባላት በንግግሮቹና በሚሰጣቸው ሐሳቦች በሚስዮናዊነት ሥራ ስላገለገሉ በርካታ ወንድሞች የሚገልጹ አስደሳች ታሪኮችን እንደሚያካትት እርግጠኞች ነበሩ። ወንድም ቤሪ የግል ተሞክሮዎቹን በጋለ ስሜት በሚናገርበት ጊዜ ‘እስከ ምድር ጫፍ’ የሚከናወነው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ለአድማጮቹ ሕያው ሆኖ ይታያቸዋል። ከእነዚህ ተሞክሮዎች ውስጥ ጥቂቶቹ በመስከረም 15, 1960 መጠበቂያ ግንብ ላይ ታትሞ በወጣው የሕይወት ታሪኩ ላይ ተጠቅሰዋል።
ወንድም ቤሪ “ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ” ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት የነበረው ፍላጎት ‘የክርስቶስ ተባባሪ ወራሽ’ በሚሆንበትም ጊዜ እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን። ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረና ለአምላክ ሕዝቦችም ልባዊ ፍቅር የነበረው መንፈሳዊ ሰው መሆኑን የሚያውቁ ሁሉ እሱን በማጣታቸው እንደሚያዝኑ የተረጋገጠ ነው። ቢሆንም ወንድም ቤሪ እስከ ምድራዊ ሕይወቱ ማብቂያ ድረስ የታመነ ሆኖ በመጽናቱ ደስተኞች ነን።—ራእይ 2:10
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሎይድ ቤሪና ጆን ባር በ1988 “ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል” (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ታትሞ በወጣበት ጊዜ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የ11ኛው ክፍል ተመራቂዎች ከ40 ዓመታት በኋላ በጃፓን ሲገናኙ