በተለያዩ አገሮች በመዘዋወር ክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ያገለግላሉ
“ዓለም አቀፍ አገልጋዮች” ወይም “ዓለም አቀፍ ፈቃደኛ ሠራተኞች” ሲባል ሰምተህ ታውቃለህ? በዚህ መስክ የሚሰማሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን በፈቃደኝነት በመሠዋት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማተምና ለማሰራጨት የሚያገለግሉ ሕንፃዎችን በመገንባቱ ሥራ ይካፈላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥባቸውን ለጉባኤና ለትላልቅ ስብሰባዎች የሚያገለግሉ አዳራሾችንም ይገነባሉ። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች በ34 አገሮች ውስጥ በሚካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እየሠሩ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ አገሮች የገንዘብ አቅማቸው ውስን ነው። ክርስቲያናዊውን የወንድማማች ማኅበር በዓለም ዙሪያ በሚያገለግሉበት ጊዜ ምን ተፈታታኝና አስደሳች ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? ስለሚያቀርቡት “ቅዱስ አገልግሎት” ምን ይሰማቸዋል? (ራእይ 7:9, 15 NW ) የዚህን መልስ ለማግኘት በሜክሲኮ የሚያገለግሉ አንዳንድ ፈቃደኛ ሠራተኞች የተናገሩትን እንስማ።
ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜክሲኮ የመጡት በግንቦት 1992 ነበር። ብዙም ሳይቆዩ በሜክሲኮ የሚካሄደውን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በበላይነት የሚመለከተውን ቅርንጫፍ ቢሮ በማስፋፋቱ ሥራ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት ጀመሩ። ፕሮጀክቱ በቅርንጫፍ ቢሮው ለሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች መኖሪያ እንዲሁም ለኅትመትና ለቢሮ ሥራ የሚውሉትን ጨምሮ የ14 አዳዲስ ሕንፃዎችን ግንባታ ያጠቃልላል።
ለዚህ የግንባታ ፕሮጀክት ድጋፍ ለመስጠት ከካናዳ፣ ከታላቋ ብሪታንያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስና ከሌሎች አገሮች የተውጣጡ ከ730 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከመላው ሜክሲኮ ከመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች ጋር በኅብረት ሠርተዋል። ከዚህም በላይ በቅርንጫፍ ቢሮው አካባቢ ከሚገኙ ወደ 1, 600 ከሚጠጉ ጉባኤዎች የተውጣጡ ከ28, 000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ቅዳሜና እሁድ እየመጡ በግንባታው ሥራ ተካፍለዋል። ሁሉም በፈቃደኝነት መንፈስ ያገለገሉ ሲሆን ያለ ምንም ክፍያ በሞያቸው እገዛ አድርገዋል። በዚህ መንገድ ይሖዋን ማገልገላቸውን እንደ መብት ይቆጥሩታል። የግንባታ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሥራው የተካፈሉት በመዝሙር 127:1 ላይ የሚገኙትን “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” የሚሉትን ቃላት አልዘነጉም።
ያጋጠሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች
በዓለም ዙሪያ የሚያገለግሉት እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከአገራቸው ውጪ በተመደቡበት ቦታ ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? ከሰጧቸው አስተያየቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡት ከርተስ እና ሳሊ የተባሉ ባልና ሚስት በሕንድ፣ በሜክሲኮ፣ በሩማኒያ፣ በሩሲያ፣ በሴኔጋል፣ በዛምቢያ፣ በጀርመንና በፓራጓይ በተካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ሠርተዋል። ከርተስ እንዲህ ይላል:- “መጀመሪያ ላይ ፈታኝ የሆነብን አቅኚ [የሙሉ ጊዜ አገልጋይ] የሆነችውን ልጃችንንና በሚኒሶታ የሚገኘውን ጉባኤያችንን ትቶ መሄዱ ነበር። እኔና ባለቤቴ በዚያ ጉባኤ ውስጥ ለ24 ዓመታት ቆይተናል፤ ልክ እንደ ቤታችን ነበር የምንቆጥረው።”
ሳሊ እንዲህ ትላለች:- “ባልለመዱት ሁኔታ መኖር ቀላል አይደለም፤ ይህ ደግሞ ከወንድ ይልቅ ለሴት የበለጠ የሚከብድ ይመስለኛል። ሆኖም ከሁኔታዎቹ ጋር መላመድ እንደሚቻል ተምሬያለሁ። ሌላው ቀርቶ ብዙ ተባይ በሚገኝበት አካባቢ እንኳ መኖር ለምጃለሁ!” አክላም እንዲህ ብላለች:- “በአንድ አገር ውስጥ አሥር የምንሆን ፈቃደኛ ሠራተኞች ወጥ ቤት በሌለውና ሁለት መታጠቢያ ቤቶች ብቻ ባሉት አንድ ፎቅ ላይ አብረን ኖረናል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ስንኖር ታጋሽነትን ይበልጥ አዳብሬያለሁ።”
አዲስ ቋንቋ መማር ጥረትና ትሕትና የሚጠይቅ ሌላው ፈታኝ ሁኔታ ነው። ከባለቤቷ ጋር በተለያዩ አገሮች በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተካፈለችው ሻረን እንዲህ ትላለች:- “በተመደባችሁበት አገር የሚነገረውን ቋንቋ አለማወቅ ፈታኝ ነው። መጀመሪያ ላይ ስሜታችሁን በደንብ መግለጽ ስለሚያስቸግራችሁ ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር መቀራረብ ይከብዳችኋል። ይህ ደግሞ ያስጨንቃችኋል። ይሁን እንጂ ተመድበን በሠራንባቸው አገሮች የምናገኛቸው ወንድሞች በጣም ይታገሱን የነበረ ሲሆን ለደህንነታችንም በጥልቅ ያስባሉ። ብዙም ሳይቆይ እንደምንም ብለን ሐሳባችንን መግለጽ ጀመርን።”
በአገልግሎት መካፈል ድፍረት ይጠይቃል
የራሳቸውን ጥቅም የሚሠዉ እንደነዚህ ያሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች ለግንባታው ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ቢሆንም በዋነኛነት ግን የአምላክ መንግሥት ምስራች ሰባኪዎች መሆናቸውን ይገነዘባሉ። በዚህም ምክንያት ከተመደቡበት ጉባኤ ጋር በመሆን ለስብከቱ ሥራ የተሟላ ድጋፍ ይሰጣሉ። ኦኬ እና ኢንጅሜሪ በማላዊ፣ በሜክሲኮ፣ በናይጄርያና በጓዴሎፕ በተካሄዱት የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሠሩ ሲሆን በሌላ ቋንቋ በመስክ አገልግሎት መካፈል ድፍረት እንደሚጠይቅ በግልጽ ተናግረዋል።
ኢንጅሜሪ እንዲህ ብላለች:- “መጀመሪያ ላይ አገልግሎት የምንወጣው የአገሩ ተወላጅ ከሆኑ ምሥክሮች ጋር ብቻ ነበር። ይህም ቋንቋውን በደንብ ባለመቻላችን ፍርሃት ይሰማን ስለነበረ ነው። በዚህም ምክንያት ተሳትፏችን በጣም ውስን ነበር። ይሁንና አንድ ቀን ጠዋት ብቻችንን ወደ መስክ አገልግሎት ለመውጣት ወሰንን። ወደ አገልግሎት ስንወጣ በጣም ፈርተንና ተጨንቀን ነበር። አንዲት ወጣት አገኘንና የተዘጋጀሁትን መግቢያ ተጠቅሜ ምሥራቹን ነገርኳት። ጥቅስ ካነበብኩላት በኋላ የተወሰኑ ጽሑፎች አበረከትኩላት። ከዚያም እንዲህ አለችኝ:- ‘እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅሽ። አንዲት ዘመዴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናች ነው። እኔስ የሚያስጠናኝ ሰው ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?’ በዚህ ጊዜ በጣም ከመገረሜ የተነሳ የምለው ጠፋኝ። ከዚያም ራሴን አረጋጋሁና መጽሐፍ ቅዱስን ላስጠናት እንደምችል ነገርኳት።”
ኢንጅሜሪ አክላ እንዲህ ብላለች:- “ይሖዋ ጥረታችንንና እውነትን ለሌሎች ለማካፈል ያለንን ፍላጎት ስለባረከልን የተሰማኝን ደስታና የአመስጋኝነት ስሜት መገመት ትችላላችሁ።” ይህች ሴት ጥሩ እድገት በማድረግ በሜክሲኮ ሲቲ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች። ኦኬ እና ኢንጅሜሪ ለአገልግሎት ያላቸውን አመለካከት እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “በተለያዩ ቦታዎች ተመድበን የምናከናውነውን የግንባታ ሥራ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ሆኖም አንድ ሰው እውነትን እንዲቀበል ከመርዳት የበለጠ ደስታና እርካታ የሚያስገኝ ነገር የለም።”
የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ
እውነት ነው፣ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ወንድሞቻቸውን ለማገልገል ሲሉ ቤተሰባቸውንና ወዳጆቻቸውን ትተው የሚሄዱ ፈቃደኛ ሠራተኞች መሥዋዕትነት የሚከፍሉ ቢሆንም ተወዳዳሪ የሌለው ደስታም ያገኛሉ። እንዴት?
በሜክሲኮ፣ በአንጎላ፣ በኢኳዶር፣ በኤል ሳልቫዶር፣ በኮሎምቢያ፣ በጉያና እና በፖርቶ ሪኮ ከባለቤቱ ከፓሜላ ጋር ያገለገለው ሃዋርድ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በተለያዩ አገሮች ከሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር መገናኘትና በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የሚንጸባረቀውን ፍቅር መመልከት የማይገኝ አጋጣሚ ነው። በመካከላችን ስላለው የወንድማማች ፍቅር ብዙ ጊዜ በጽሑፎች ላይ ያነበብን ቢሆንም የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ካላቸው ወንድሞች ጋር ስትኖርና ስትሠራ ውድ ለሆነው የወንድማማች ማኅበራችን ያለህ አድናቆት ከበፊቱ የበለጠ ይጨምራል።”
በሜክሲኮ፣ በኢኳዶር፣ በኮሎምቢያ፣ በኮስታ ሪካ እና በዛምቢያ በተካሄዱ የግንባታ ሥራዎች የተካፈለው ጋሪ ይህ ፕሮግራም በጣም እንደጠቀመው ይሰማዋል። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ባለፉት ዓመታት በተመደብኩባቸው አገሮች በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ከሚያገለግሉ የጎለመሱ ወንድሞች ጋር በነበረኝ ግንኙነት ያገኘሁት ሥልጠና ከሥራው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙኝን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም በተሻለ መንገድ አስታጥቆኛል። በዚህ መስክ መሠማራቴ ቋንቋ፣ ዘር ወይም ባሕል የማይገድበው የይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ተለይቶ የሚታወቅበትን አንድነት የማየት አጋጣሚ ስላስገኘልኝ እምነቴ ሊጠናከር ችሏል።”
በሜክሲኮ የተካሄደው የግንባታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ለቅርንጫፍ ቢሮው የተገነቡት ተጨማሪ ሕንፃዎችም በዚህ ዓመት ተወስነዋል። ዓለም አቀፍ አገልጋዮችና ፈቃደኛ ሠራተኞች ለአምላክ ባላቸው ፍቅር በመነሳሳት በሜክሲኮም ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ እውነተኛው አምልኮ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በመላው ዓለም የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ክርስቲያናዊውን የወንድማማች ማኅበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በማገልገል የሚያሳዩትን የፈቃደኝነትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በጣም ያደንቃሉ።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢኳዶር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮሎምቢያ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንጎላ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው የአትክልት ቦታ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ የአዲሶቹ ሕንፃዎች ግንባታ ሲጀመር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከታች:- የተወሰኑ የግንባታው ክፍል አባላት በአዲሶቹ ሕንፃዎች ፊት
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ከተመደቡበት ጉባኤ ጋር ሆነው በስብከቱ ሥራ መካፈል ያስደስታቸዋል