የጊልያድ ተመራቂዎች የአምላክን “ታላቅ ሥራ” እንዲናገሩ ማበረታቻ ተሰጣቸው
መስከረም 13, 2003 በተካሄደው የጊልያድ የሚስዮናውያን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት 115ኛ ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከ52 አገሮች የመጡ 6, 635 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር።
ተሰብሳቢዎቹ ለ48ቱ ተማሪዎች አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ በተመደቡባቸው 17 አገሮች ውስጥ “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” ለሰዎች እንዲናገሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ማበረታቻ ሲሰጣቸው አዳምጠዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:11
የምረቃው ሥነ ሥርዓት ሊቀ መንበር የነበረውና የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ስቲቨን ሌት በመክፈቻ ንግግሩ ላይ ተማሪዎቹን “የተመደባችሁበት ቦታ የትም ይሁን የት፣ ምንም ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማችሁ ከእናንተ ጋር ያሉት ከሚቃወሟችሁ ይበልጣሉ” በማለት አበረታታቸው። ወንድም ሌት ሁለተኛ ነገሥት ምዕራፍ 6ን በመጥቀስ ተማሪዎቹ የአምላክን “ታላቅ ሥራ” ለሰዎች በሚናገሩበት ጊዜ የይሖዋ አምላክና የእልፍ አዕላፋት መላእክቱ ድጋፍ እንደማይለያቸው አሳሰባቸው። (2 ነገሥት 6:15, 16) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በስብከቱና በማስተማር ሥራቸው ላይ ተቃውሞና ግዴለሽነት አጋጥሟቸው እንደነበር ሁሉ በዛሬው ጊዜ በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ይሁን እንጂ ከሰማይም ሆነ ከይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ድጋፍ እንደሚያገኙ ሊተማመኑ ይችላሉ።—መዝሙር 34:7፤ ማቴዎስ 24:45
የአምላክን “ታላቅ ሥራ” ተናገሩ
የሊቀ መንበሩን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ሃሮልድ ኮርከርን “ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች ማውጣት አስደሳችና ስኬታማ አገልግሎት ለማከናወን ያስችላል” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። ወንድም ኮርከርን ምሳሌ 13:12 እንደሚለው ተስፋ ያደረጉት ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ እንደሚያሳዝን ጠቀሰ። ይሁን እንጂ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቅር የሚሰኙት መጀመሪያውኑ እውን ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን ጠብቀው ሳይፈጸሙ ሲቀሩ ነው። ተመራቂዎቹ ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ ሌሎች ሚዛናዊ የሆነና ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል። ስህተት ሊሠሩ እንደሚችሉ መጠበቅ ያለባቸው ሲሆን ሰዎች የአምላክን “ታላቅ ሥራ” እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥረት ሲያደርጉ በስህተቶቻቸው ከልክ በላይ ማዘን አይኖርባቸውም። ወንድም ኮርከርን አዲሶቹ ሚስዮናውያን ከልብ ‘ለሚፈልጉት ዋጋ በሚሰጠው’ በይሖዋ ላይ እንዲታመኑ አበረታታቸው።—ዕብራውያን 11:6
ቀጣዩ ተናጋሪ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ ሲሆን ጭብጡም “ክርስቲያናዊ ተስፋ ምንድን ነው?” የሚል ነበር። እንዲህ አለ:- “ተስፋ ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባ ጠቃሚ ባሕርይ ነው። አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርት የሚረዳው ትክክለኛ አቋም ነው። ክርስቲያን ያልሆነ ሰው እንደ እኛ ያለ ተስፋ ሊኖረው አይችልም።” ከዚያም ወንድም ሲድሊክ ሕይወት በውጣ ውረድ የተሞላ ቢሆንም ብሩህ አመለካከት እንዲኖረን የሚያደርገንን ክርስቲያናዊ ተስፋ የተለያዩ ገጽታዎች ዘረዘረ። “ተስፋ ካለን ሕይወትን በትጋትና በድል አድራጊነት መንፈስ መጋፈጥ እንችላለን።” ተስፋ አንድን ክርስቲያን ይሖዋ የዓላማ አምላክ መሆኑን እንዲገነዘብና እርሱን በማገልገሉ እንዲደሰት ይረዳዋል።—ሮሜ 12:12
የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጅስትራር የሆነው ዋላስ ሊቨራንስ “በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ” በማለት ተማሪዎቹን አበረታታቸው። (ገላትያ 5:16) የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ በመንፈስ መመላለሱን ለማቆም ተቃርቦ እንደነበር ጠቀሰ። ባሮክ በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ በመዳከሙ ለራሱ ታላቅ ነገርን ወደ መፈለግ አዘንብሎ ነበር። (ኤርምያስ 45:3, 5) ከዚያም ወንድም ሊቨራንስ አንዳንዶች ለመዳን አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊ እውነት አንቀበልም እንዳሉና ኢየሱስን መከተላቸውን እንዳቆሙ ተናገረ። ይህ የሆነው ትምህርቶቹን ስላልተረዱና ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸው በጊዜው ስላልተፈጸሙላቸው ቅር በመሰኘታቸው ነው። (ዮሐንስ 6:26, 27, 51, 66) ሰዎች ፈጣሪን እንዲያውቁና ዓላማውን እንዲገነዘቡ የመርዳት ኃላፊነት የተጣለባቸው ሚስዮናውያን ከእነዚህ ታሪኮች ምን ይማራሉ? ተማሪዎቹ ሥልጣን ወይም የሰዎችን እውቅና ስለማግኘት እንዳይጨነቁና ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ለግል ጥቅም ማራመጃ እንዳያውሉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።
“ሰጪ ትሆናላችሁ ወይስ ተቀባዮች?” የሚለውን ጥያቄ አዘል ጭብጥ ይዞ የቀረበው የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ማርክ ኑሜር ነው። ንግግሩ የተመሠረተው እስራኤላውያን በባርቅ ሠራዊት ውስጥ ለማገልገል በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረባቸው እንደተመሰገኑ በሚናገረው በመሳፍንት 5:2 ላይ ነበር። ታላቁ ባርቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊው ውጊያ ይበልጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ላቀረበላቸው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠታቸው ተማሪዎቹን አመሰገናቸው። የክርስቶስ ወታደሮች የሠራዊቱ አባል እንዲሆኑ የመለመላቸውን አካል ሞገስ የማግኘት ፍላጎት ሊያድርባቸው ይገባል። ወንድም ኑሜር ተማሪዎቹን እንደሚከተለው በማለት አሳሰባቸው:- “ራሳችንን በማስደሰት ላይ ማተኮር ስንጀምር ጠላትን መዋጋታችንን እናቆማለን። . . . የሚስዮናዊነት አገልግሎት ዋነኛ ዓላማ ከይሖዋ፣ ከሉዓላዊነቱና ከፈቃዱ መፈጸም ጋር የተያያዘ እንጂ የእናንተ ደስታ ማግኘት አይደለም። በሚስዮናዊነት የምናገለግለው ይሖዋ እንዲያስደስተን ስለምንፈልግ ሳይሆን ስለምንወደው ነው።”—2 ጢሞቴዎስ 2:4
“በእውነትህ ቀድሳቸው” የሚለውን ክፍል ያቀረበው የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ሎውረንስ ቦወን ነበር። (ዮሐንስ 17:17) የ115ኛው ክፍል ተማሪዎች የተቀደሱ የአምላክ አገልጋዮች መሆናቸውን ጠቀሰ። በትምህርት ቤት ቆይታቸው ወቅት ቅን ልብ ያላቸውን እውነት ወዳድ ሰዎች ለማግኘት በመስክ አገልግሎት ተካፍለዋል። እንደ ኢየሱስና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ የሚናገሩት ‘ከራሳቸው’ አልነበረም። (ዮሐንስ 12:49, 50) ከአምላክ የመጣውን ሕይወት ሰጪ የእውነት ቃል በቅንዓት አውጀዋል። ተማሪዎቹ ያቀረቧቸው ሠርቶ ማሳያዎችና ተሞክሮዎች መጽሐፍ ቅዱስ ባነጋገሯቸው ሰዎች ላይ ያስገኘውን ውጤት የሚያሳዩ ነበሩ።
አበረታች ምክሮችና ተሞክሮዎች
አንቶኒ ፔሬዝ እና አንቶኒ ግሪፈን የተባሉት የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የአገልግሎት ክፍል ባልደረቦች ከዓለም ዙሪያ ከመጡ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር። እነዚህ ወንድሞች አዳዲስ ሚስዮናውያን የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የዘረዘሩ ሲሆን ከግል ተሞክሯቸው በመነሳት ተግባራዊ ምክሮችን ለግሰዋል። ሚስዮናውያን ከሚያጋጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች መካከል የባሕል ልዩነት፣ ከዓመት እስከ ዓመት የሚዘልቅ ሞቃታማ የአየር ንብረት ወይም ካደጉበት አካባቢ የተለየ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚጠቀሱ ናቸው። አዳዲስ ሚስዮናውያን እነዚህን ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ ምን ሊረዳቸው ይችላል? ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር እንዲሁም ትተውት የመጡትን ሕይወት አለመናፈቅና የችኮላ እርምጃዎችን አለመውሰድ ሊረዳቸው ይችላል። አንድ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የተመደብንበትን አካባቢ፣ ሰዎች ከብዙ ዘመናት አንስቶ ኖረውበታል፤ እኛም እንደ እነርሱ ራሳችንን ከአካባቢው ጋር አላምደን በዚያ መኖር እንችላለን። ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ሁሉ ባሕርያችንን ለማሻሻል እንደሚያስችሉን አጋጣሚዎች አድርገን እንመለከታቸዋለን። በጸሎትና በይሖዋ መንፈስ ከተማመናችሁ ‘እኔ . . . ከእናንተ ጋር ነኝ’ የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት እውነተኝነት ትገነዘባላችሁ።”—ማቴዎስ 28:19, 20
በምረቃው ሥነ ሥርዓት መገባደጃ ላይ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሳሙኤል ኸርድ “የአምላክን ታላቅ ሥራ መናገራችሁን ቀጥሉ” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ የአምላክን “ታላቅ ሥራ” እንዲናገሩ ኃይል ሰጥቷቸዋል። በዛሬው ጊዜስ አዳዲስ ሚስዮናውያን ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት እንዲናገሩ ሊረዳቸው የሚችለው ምንድን ነው? ይኸው የአምላክ መንፈስ ነው። ወንድም ኸርድ ተመራቂዎቹ ተማሪዎች ‘በመንፈስ እንዲቃጠሉ፣’ የተመደቡበትን ቦታ እንዲወዱትና የተሰጣቸውን ሥልጠና ፈጽሞ እንዳይዘነጉ አበረታታቸው። (ሮሜ 12:11) “ከአምላክ ታላላቅ ሥራዎች ውስጥ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው” በማለት ተናገረ። “ያለውን ጠቀሜታ ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱት። መልእክቱ ሕያው ነው። ልብን ይመረምራል። በሕይወታችሁ ውስጥ ነገሮችን ለማቅናት ተጠቀሙበት። አስተሳሰባችሁን እንዲያስተካክለው ፍቀዱለት። ቅዱሳን ጽሑፎችን በማጥናት፣ በማንበብና በማሰላሰል የማሰብ ችሎታችሁን ጠብቁ። . . . በጊልያድ ያገኛችሁትን ሥልጠና ተጠቅማችሁ ‘የአምላክን ታላቅ ሥራ’ መናገራችሁን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።”
ከዓለም ዙሪያ የተላኩ ሰላምታዎች ከተነበቡና ለተማሪዎች ዲፕሎማ ከተሰጠ በኋላ አንድ ተማሪ የክፍሉ ተማሪዎች ላገኙት ሥልጠና የተሰማቸውን አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ አነበበ። ከዚያም ወንድም ሌት ስብሰባውን ሲደመድም 2 ዜና መዋዕል 32:7 እና ዘዳግም 20:1, 4ን ጠቀሰና በመግቢያው ላይ የተናገረውን ሐሳብ በማንሳት እንዲህ አለ:- “ስለሆነም ውድ ተመራቂዎች፣ በመንፈሳዊው ውጊያ ለመሳተፍ ወደ አዲሱ ምድባችሁ ስትዘምቱ ይሖዋ አብሯችሁ እንደሚሄድ አስታውሱ። ከእናንተ ጋር ያሉት ከሚቃወሟችሁ እንደሚበልጡ ፈጽሞ አትዘንጉ።”
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 7
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 17
የተማሪዎቹ ብዛት:- 48
አማካይ ዕድሜ:- 33.7
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 17.8
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13.5
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 115ኛ ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ብራውን ቴፍታ፣ ጎለር ሴሲቤል፣ ሆፍማን አንጂ፣ ብሩዚዚ ጀኔት፣ ትሬሃን ሶንያ (2) ስማርት ኒኪ፣ ካሽማን ፍራንሲን፣ ጋርሲያ ኪምበርሊ፣ ሎሃን ሜሊሳ፣ ሲፈርት ሲልቪያ፣ ግሬይ ካሪ (3) ቢኬት ሜረሊን፣ ኒከልዝ ሴራ፣ ስሚዝ ኪና፣ ጉልያራ አንቶኒዬታ፣ ራፕኔከር አንጀላ (4) ግሬይ ስኮት፣ ቫሴክ ካቲ፣ ፍሌሚንግ ሚስቲ፣ ቤቴል ሊንዳ፣ ኸርማንሰን ታቢታ፣ ኸርማንሰን ፒተር (5) ራፕኔከር ጋሪ፣ ሎሃን ዴቪድ፣ ዲኪ ሻ፣ ኪም ኮኒ፣ ትሬሃን አሮን፣ ዋሽንግተን አንድሬ፣ ስማርት ሾን (6) ጎለር ላንስ፣ በርግሆፈር ቲርዛ፣ ጉልያራ ዳንኤል፣ ኒከልዝ ራንዲ፣ ዋሽንግተን ሼሊ፣ ኪም ጁ ኦን (7) ቢኬት ሞሪስ፣ ዲኪ ጆን፣ ስሚዝ ራድኒ፣ ጋርሲያ ራሞን፣ ሆፍማን አሮን፣ ሲፈርት ራስል፣ ብራውን ሃሮልድ (8) ፍሌሚንግ ሼን፣ ብሩዚዚ ፒተር፣ በርግሆፈር ዌድ፣ ቤቴል ቲም፣ ካሽማን ጂሚ፣ ቫሴክ ኬሊ