አርማጌዶን ድንገተኛ የዓለም ጥፋት ነው?
አርማጌዶን! ይህን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? የጅምላ እልቂት ወይም የጽንፈ ዓለም መጋየት? በብዙ አገሮች በጣም ከተለመዱት ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ አባባሎች መካከል “አርማጌዶን” አንዱ ነው። ይህ ቃል የሰው ልጅ ከፊቱ የሚጠብቀውን የጨለመ ተስፋ ለማመልከት በሰፊው ሲሠራበት ቆይቷል። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ስለ መጪው “አርማጌዶን” በሰዎች አእምሮ ውስጥ አሰቃቂ ትዕይንት ስሏል። ብዙውን ጊዜ ቃሉ ግልጽ ያልሆነና የተሳሳተ ትርጉም ይሰጠዋል። አርማጌዶንን በተመለከተ በርካታ አስተሳሰቦች ቢኖሩም ብዙዎቹ የቃሉ መገኛ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ከሚያስተምረው ጋር አይስማሙም።
መጽሐፍ ቅዱስ አርማጌዶንን ‘ከዓለም መጨረሻ’ ጋር ስለሚያያይዘው ስለ ቃሉ ትርጉም ትክክለኛ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል ቢባል አትስማማም? (ማቴዎስ 24:3) በተጨማሪም፣ የአርማጌዶንን ምንነትና በአንተም ሆነ በቤተሰብህ ላይ የሚኖረውን ውጤት አስመልክቶ ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከሁሉ የላቀ የእውነት ምንጭ ወደ ሆነው ወደ አምላክ ቃል ዞር ማለት ተገቢ አይሆንም?
የአምላክን ቃል መመርመራችን አርማጌዶን ድንገተኛና አሰቃቂ የዓለም ጥፋት ሳይሆን ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ በብልጽግና መኖር ለሚጓጉ ሰዎች አስደሳች ጅማሬ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ አርማጌዶን እውነታውን የሚያስጨብጥ ማብራሪያ ስታነብ ስለዚህ የላቀ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ግልጽ ግንዛቤ ታገኛለህ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በአንተ አመለካከት አርማጌዶን ምንድን ነው?
• የኑክሌር እልቂት?
• አካባቢን የሚያወድም የተፈጥሮ አደጋ?
• የሰማይ አካላት ከምድር ጋር መላተም?
• አምላክ በክፉዎች ላይ የሚያመጣው ጥፋት?