አርማጌዶን—አንዳንዶች እንዴት ይገልጹታል?
“በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።”—ራእይ 16:16 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
“አርማጌዶን” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ከፍተኛ ስለሆነ እልቂት ታስብ ይሆናል። “አርማጌዶን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆንም እንኳ የዜና ማሰራጫዎችና የሃይማኖት መሪዎች ቃሉን በተደጋጋሚ ሲጠቅሱት መስማት የተለመደ ነው።
ይሁንና ብዙዎች ስለ አርማጌዶን ያላቸው አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር ይስማማል? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቁ ጠቃሚ ነው። ለምን? ምክንያቱም ስለ አርማጌዶን እውነቱን ማወቅህ አላስፈላጊ ከሆነ ፍርሃት ነፃ የሚያወጣህ ከመሆኑም ሌላ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል፤ እንዲሁም ስለ አምላክ ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ያመጣል።
ብዙዎች ስለ አርማጌዶን ያላቸውን አመለካከት የሚያንጸባርቁ ሦስት ጥያቄዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፤ እነዚህን ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ሐሳብ ጋር እንድታወዳድር እንጋብዝሃለን።
1. አርማጌዶን ሰዎች የሚያመጡት ጥፋት ነው?
ጋዜጠኞችና ተመራማሪዎች፣ ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሚያስከትሏቸውን ጥፋቶች ለመግለጽ “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች አርማጌዶን ተብለው ተጠርተዋል። ከእነዚያ ጦርነቶች ወዲህም ዩናይትድ ስቴትስና ሶቪየት ኅብረት በአቶሚክ የጦር መሣሪያ እርስ በርስ ይዋጋሉ የሚል ስጋት ነበር። የመገናኛ ብዙኃን፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ግጭት “የኑክሌር አርማጌዶን” ብለው ጠርተውታል። በሌላ በኩል ደግሞ በዛሬው ጊዜ የምድር ብክለት በአየር ንብረት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከትላል ብለው የሚፈሩ ተመራማሪዎች በቅርቡ “የአየር ንብረት አርማጌዶን” ሊከሰት እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
አመለካከታቸው ያለው አንድምታ፦ ምድርና በላይዋ ያለው ሕይወት የወደፊት ዕጣ ሙሉ በሙሉ በሰዎች ቁጥጥር ሥር ነው። መንግሥታት ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ካልወሰዱ ምድር ዘላቂ ጉዳት ይደርስባታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ሰዎች ምድርን እንዲያጠፏት አምላክ አይፈቅድም። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋa ምድርን የፈጠራት “ለከንቱ” እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። ከዚህ ይልቅ ምድርን የፈጠራት ‘መኖሪያ እንድትሆን’ ነው። (ኢሳይያስ 45:18 የ1954 ትርጉም) አምላክ፣ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋቸዋል]” እንጂ ሰዎች ምድርን ጨርሶ እንዲያጠፏት አይፈቅድም።—ራእይ 11:18
2. አርማጌዶን የተፈጥሮ አደጋ ነው?
ጋዜጠኞች አንዳንድ ጊዜ ታላላቅ የተፈጥሮ አደጋዎችን “አርማጌዶን” ብለው ይሰይሟቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2010 የወጣ አንድ ዘገባ “በሄይቲ ስለደረሰው ‘አርማጌዶን’” ተናግሮ ነበር። ዘገባው ይህን ያለው ሄይቲን ያወደመው ኃይለኛ ርዕደ መሬት ያደረሰውን መከራ እንዲሁም በንብረትና በሕይወት ላይ ያስከተለውን ጥፋት ለመግለጽ ነበር። የዜና ዘጋቢዎችና የፊልም አዘጋጆች “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙበት እስከ አሁን የደረሱትን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ይደርሱ ይሆናል ብለው የሚያስቧቸውን ክስተቶች ለመግለጽ ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አነስተኛ የሆኑ የሰማይ አካላት ከምድር ጋር ሲላተሙ ሊፈጠር ይችላል ብለው ያሰቡትን ሁኔታ ለመግለጽ “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል።
አመለካከታቸው ያለው አንድምታ፦ አርማጌዶን እገሌ ከገሌ ሳይል ንጹሐን ሰዎችን በጅምላ የሚጨርስ ጥፋት ነው። ከአርማጌዶን ለማምለጥ ልታደርግ የምትችለው ነገር የለም።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? አርማጌዶን ሰዎችን በጅምላ የሚጨርስ ጥፋት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአርማጌዶን ተጠራርገው የሚጠፉት ክፉ ሰዎች ብቻ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም” የሚለው ትንቢት በቅርቡ እንደሚፈጸም ይገልጻል።—መዝሙር 37:10
3. አምላክ ምድርን በአርማጌዶን ያጠፋታል?
ብዙ ሃይማኖተኛ ሰዎች፣ በጥሩና በመጥፎ ኃይሎች መካከል የመጨረሻው ጦርነት ሲካሄድ ምድራችን እንደምትጠፋ ያምናሉ። ፕሪንስተን ሰርቬይ ሪሰርች አሶሲዬትስ የተባለው ተቋም በዩናይትድ ስቴትስ ባካሄደው ጥናት ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ዓለም “በአርማጌዶን ጦርነት” እንደምትጠፋ ያምናሉ።
አመለካከታቸው ያለው አንድምታ፦ ሰዎች የተፈጠሩት በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ አልነበረም፤ ምድርም ቢሆን ዘላለማዊ አይደለችም። አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በሆነ ወቅት ላይ ሁሉም እንደሚሞቱ አስቦ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገረው አምላክ “ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ [አጽንቷታል]።” (መዝሙር 104:5) የአምላክ ቃል በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን አስመልክቶ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።—መዝሙር 37:29
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አርማጌዶን የሚናገረው ነገር ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት ጋር ይጋጫል። ታዲያ ስለ አርማጌዶን እውነታው ምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።