ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት የምንችለው እንዴት ነው?
በአንድ ታዳጊ አገር የሚኖር ፍራንሷ የሚባል የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ምርጫ በተካሄደ ማግስት በአገሪቱ የተነሳው ዓመፅ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸውን ጥለው እንዲሸሹ አስገደዳቸው። የምግብና የመድኃኒት እጥረት ተከስቶ የነበረ ሲሆን ዋጋውም በጣም ንሮ ነበር። ባንኮች ከመዘጋታቸውም ሌላ የገንዘብ ማሽኖች ባዶ ሆነው ነበር አሊያም አይሠሩም ነበር።”
ከቅርንጫፍ ቢሮው የተላኩ ወንድሞች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመንግሥት አዳራሾች ለተጠለሉት የይሖዋ ምሥክሮች ገንዘብና የእርዳታ ቁሳቁሶችን በአፋጣኝ ማድረስ ጀመሩ። ተቀናቃኝ አንጃዎቹ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ኬላዎች አቋቋሙ፤ ይሁን እንጂ ሁለቱም ወገኖች የይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅ የገለልተኝነት አቋም እንዳላቸው ስለሚያውቁ የቅርንጫፍ ቢሮው መኪኖች ብዙውን ጊዜ እንዲያልፉ ይፈቀድላቸው ነበር።
ፍራንሷ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ወደ አንድ የመንግሥት አዳራሽ እየተጓዝን ሳለ የደፈጣ ተዋጊዎች በመኪናችን ላይ ተኩስ ከፈቱ። ይሁን እንጂ ጥይቶቹ በመካከላችን አለፉ። አንድ ወታደር መሣሪያ ይዞ ወደ እኛ ሲሮጥ ስናይ መኪናውን አዙረን በፍጥነት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ተመለስን። ሕይወታችን በመትረፉ ይሖዋን አመሰገንነው። በቀጣዩ ቀን በዚያ የመንግሥት አዳራሽ የተጠለሉት 130 ወንድሞች የተረጋጋ ሁኔታ ወዳለበት ቦታ ተዛወሩ። አንዳንዶቹ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው የመጡ ሲሆን ረብሻው እስኪያበቃ ድረስ በመንፈሳዊም ሆነ በቁሳዊ አስፈላጊውን እንክብካቤ አደረግንላቸው።”
“ይህ ሁኔታ ካለፈ በኋላ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ወንድሞች የተሰማቸውን ጥልቅ የአድናቆት ስሜት በመግለጽ በርካታ ደብዳቤዎች ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ላኩ” በማለት ፍራንሷ ተናግሯል። አክሎም “በሌላ ስፍራ የሚኖሩ ወንድሞቻቸው በችግር ጊዜ እንዴት እንደደረሱላቸው ማየታቸው በይሖዋ ይበልጥ እንዲታመኑ አድርጓቸዋል” ብሏል።
የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን “ይሙቃችሁ፣ ጥገቡም” አንላቸውም። (ያዕ. 2:15, 16) ከዚህ ይልቅ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት ጥረት እናደርጋለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ደቀ መዛሙርት ረሀብ እንደሚመጣ ማስጠንቀቂያ በሰሙ ጊዜ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ ሲሆን “እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በመላክ በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች የእርዳታ አገልግሎት ለመስጠት [ወስነው ነበር]።”—ሥራ 11:28-30
የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ችግር ላይ የወደቁ ግለሰቦችን በቁሳዊ ለመርዳት ፈቃደኞች ነን። ይሁን እንጂ ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎትም አላቸው። (ማቴ. 5:3) ኢየሱስ ተከታዮቹ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል፤ ይህ ተልእኮ ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳላቸው እንዲገነዘቡና ይህን ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ መርዳት ይጠይቃል። (ማቴ. 28:19, 20) እኛም በግለሰብ ደረጃ አብዛኛውን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ጥሪታችንን ይህን ተልእኮ ለመፈጸም እናውላለን። ድርጅታችን ከተሰበሰበው የመዋጮ ገንዘብ ውስጥ የተወሰነውን ቁሳዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚጠቀምበት ቢሆንም መዋጮው በዋነኝነት የሚውለው ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወንና ምሥራቹን ለማስፋፋት ነው። በዚህ መንገድ ለአምላክም ሆነ ለሰዎች ያለንን ፍቅር እናሳያለን።—ማቴ. 22:37-39
ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ የሚደግፉ ሰዎች የለገሱት ገንዘብ በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ እንደሚውል እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞችህን ለመርዳት የሚያስችል አቅም አለህ? ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ መደገፍ ትፈልጋለህ? ከሆነ “ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ።”—ምሳሌ 3:27