ሰሚ ጆሮ ለማግኘት ጣር
1 ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸው ብዙ ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች አያስቡም። ከቤተሰባቸው አባሎች ጋር ባላቸው ትስስር፣ በኤኮኖሚያዊ ችግሮች ወይም በግል ችግሮቻቸው አእምሮአቸው ተይዟል። ብዙውን ጊዜ ከሰዎቹ ጋር ውይይት ለመጀመር በአካባቢው ስላሉ የብዙዎችን ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮችን ማንሳቱ ጥሩ ነው። ጥያቄ መጠየቅ የቤቱ ባለቤትም ጭምር በውይይቱ ውስጥ እንዲገባ ስለሚያደርገው ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ በጥያቄዎች መጠቀም ይቻላል። ሰዎችን የማያሳፍሩ የአመለካከት ጥያቄዎችን መጠየቅ ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።
2 ባለፈው ወር ብሮሹሮችን ለማበርከት በሚረዱ አቀራረቦች ተጠቅመው ብዙዎች ሰሚ ጆሮ በማግኘት በጥሩ ሁኔታ ተሳክቶላቸዋል። በዚህም ወር ገለልተኛ በሆኑ እንዲሁም እምብዛም ባልተሠራባቸው የአገልግሎት ክልሎች በምናደርገው ዘመቻ ላይ እነዚያኑ አቀራረቦች እንደገና እንጠቀምባቸዋለን። እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “‘ሰዎች ስለሚደርስባቸው የፍትህ መጓደልና መከራ አምላክ በእርግጥ ያስባልን?’ ብለው አስበው ያውቃሉ?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። መዝሙር 72:12–14ን አንብብ። ከዚያም አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለውን ብሮሹር ገጽ 22 ገልጠህ ክፍል 10 ውስጥ ጎላ ተደርገው የተጻፉትን ርዕሶች እንዲሁም በገጽ 23 ላይ ያለውን ሥዕል ትርጉም አወያየው። ብሮሹሩን ለመውሰድ ፈቃደኛ ካልሆነ ለተጨነቁት የሚሆን መጽናኛ ወይም ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት ወይም እነዚህን ከመሳሰሉት ትራክቶች አንዱን ለምን አታበረክትለትም?
3 “እነሆ!” የተባለውን ብሮሹር ስታበረክት ቀጥሎ ያለውን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ፦
◼ “ሰው ሁሉ ሥራና ቤት እንዲያገኝ ለመርዳት ምን ሊደረግ እንደሚቻል ከጎረቤቶቻችን ጋር እየተነጋገርን ነበር። ሰዎች እንደዚህ ማድረግ ይችላሉ ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልዎታል? [የቤቱ ባለቤት መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እነዚህን ችግሮች እንዴት ማቃለል እንደሚቻል የሚያውቅ አለ። እስቲ በኢሳይያስ 65:21–23 ላይ ያለውን የሚያጽናና ተስፋ ይመልከቱ። [አንብብለት።] ፈጣሪያችን ይህንን የተስፋ ቃል ያስጻፈልን እኛን ለማበረታታት ነው። በዚህ አስጨናቂ ዘመን ሁላችንም ይህ ማበረታቻ ያስፈልገናል፤ አይደለም እንዴ?” — ምማ ፣ ገጽ 11። “እነሆ! ” የተባለውን ብሮሹር ስታበረክት በብሮሹሩ ፊትና ጀርባ ላይ ሁሉም ሰው ቤትና ሥራ እንደሚያገኝ የሚገልጸው ሐሳብ እንዴት በሥዕል እንደተገለጸ ለምን አታሳየውም? የቤቱ ባለቤት ሙሉውን ሥዕል በአንድ ጊዜ ሊያየው እንዲችል ብሮሹሩን ልትዘረጋው ትችላለህ።
4 በአካባቢው በወንጀል የተነሳ ፍራቻ ካለ ቀጥሎ ያለውን አቀራረብ መልሰህ ልትጠቀምበት ትችላለህ:-
◼ “ብዙ ሰዎች ‘አምላክ ፍቅር ከሆነ ክፋትን ለምን ፈቀደ?’ ብለው ያስባሉ። እርስዎስ እንደዚህ ብለው አስበው ያውቃሉ?” የቤቱ ባለቤት አስተያየቱን እንዲሰጥ ፍቀድለትና ከዚያም እንዲህ በል:- “ሰዎች ለሚሠሯቸው መጥፎ ነገሮች አምላክን እንዳንወቅስ ምሳሌ 19:3 እንደሚያስጠነቅቀን ልብ ይበሉ።” ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ “እነሆ! ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ ” በተባለው ብሮሹር በገጽ 15 ላይ እንዲያተኩር በማድረግ አንቀጽ 27ን አንብብ። ይህም ቀጥሎ ባሉት አንቀጾች ላይ ወደ መወያየት ሊመራ ይችላል።
5 ዓላማችን ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ያላቸው ፍላጎት እንዲቀሰቀስ ማድረግ መሆኑን አስታውስ። ሰሚ ጆሮ ለማግኘት በመጀመሪያ የቤቱን ባለቤት ትኩረት መሳብና አእምሮውን መቀስቀስ አለብን። ይህም በግ መሰል የሆኑ ሰዎች ‘ይሖዋ አምላክ’ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ‘የሚናገረውን ለመስማት’ እንዲፈልጉ ያደርጋቸዋል። — መዝ. 85:8