መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ለእውነት የቆሙ መጽሔቶች
1 የጥር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ እትም በገጽ 22 ላይ መጽሔቶቻችን “ሰዎች በሚያስፈልጓቸውና ሕይወታቸውን በነኳቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ወቅታዊ ትምህርቶችን” አትመው የሚያወጡ መሆናቸውን አመልክቷል። እነዚህ መጽሔቶች በሰፊው እንዲሰራጩ እንፈልጋለን። በሚያዝያና በግንቦት ወራት የሚበረከቱ ጽሑፎች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ይሆናሉ።
2 ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው ሥራ እነዚህን መጽሔቶች ለማበርከት ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ ይሰጠናል። መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚሰጥ ውጤታማ ምሥክርነትና ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግም በየጊዜው መጽሔቶቹን ለማበርከት ያስችለናል። ከመንገድ ወደ መንገድ እየሄዱ መመሥከርና በክልላችን በሚገኙ የንግድ መደብሮች ሰዎችን ማነጋገርም የመጽሔቶቹን ስርጭት ከፍ ለማድረግ የሚረዱ ውጤታማ መንገዶች ናቸው።
3 ለመወያያ የሚሆኑ ርዕሶች፦ የሚያዝያ 1 መጠበቂያ ግንብ “የተሻለ ዓለም መምጣቱ ሕልም ነውን?” እና “በቅርቡ የተሻለ ዓለም ይመጣል!” የሚሉትን ርዕሶች ይመረምራል። ይህም መጽሔቱ የአምላክን መንግሥት ለማስታወቅ ካለው ዓላማ ጋር ይስማማል። ሁለተኛው ርዕስ በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ሥር ዘላለማዊ ገነት እንዴት እውን እንደሚሆን በማሳየት ይደመድማል።— ሉቃስ 23:43
4 በሚያዝያ 15 እትም ላይ “እምነት የሚጣልበት አመራር ከየት ልታገኝ ትችላለህ?” የሚለው ጥያቄ ይብራራል። የግንቦት እትሞች “የሚያስፈልግዎትን ሁሉ ሃይማኖት እያሟላልዎት ነውን?” እና “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለምን አስፈለገ?” በሚሉ ርዕሶች ሥር ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ይሰጣሉ። በእነዚህ ወቅታዊ ርዕሶች ላይ ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር አያስቸግረንም።
5 የምናበረክተውን የመጽሔት ቁጥር ከፍ ማድረግ፦ የጥር 1 መጠበቂያ ግንብ የምናበረክታቸውን መጽሔቶች ቁጥር ከፍ ለማድረግ የሚረዱ አራት ሐሳቦችን አቅርቦ ነበር። (1) መጽሔቶቹን በንቃት መከታተል። መጽሔቶቹን ስናነብ በአገልግሎት ክልላችን የሚገኙ ሰዎችን ይበልጥ የሚስቡ ርዕሶች የትኞቹ እንደሆኑ ጥቂት ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። በተጨማሪም ሁልጊዜ የመጽሔቶቹን ቅጂዎች የምንይዝ ከሆነ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ ለጎረቤቶቻችን፣ ለአስተማሪዎቻችን፣ አብረውን ለሚማሩ ተማሪዎች ወይም ለገበያተኞች ማበርከት እንችል ይሆናል።
6 እንዲሁም (2) አቀራረባችንን ቀላል ማድረግ እንዳለብን ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። አንድ የሚስብ ነጥብ ምረጥና በጥቂት ቃላት ለመግለጽ ተዘጋጅ። መጽሔቱ ወደ ሰውዬው ቤት አንዴ መግባት ከቻለ ለእርሱ ወይም በቤተሰቡ ውስጥ ላሉት ሰዎች ራሱ ‘ይናገራል’።
7 ሌላው አስፈላጊ ነገር ደግሞ (3) አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው መለዋወጥ ነው። ከወጣቶች፣ ከወንዶችና ከሴቶች ጋር ለመወያየት የሚያስችሉ የተለያዩ ርዕሶችን በአእምሮ መያዙ ጥሩ ነው።
8 በመጨረሻም (4) መጽሔት ለማበርከት የግል ግብ ማውጣት ያስፈልገናል። ጉባኤው ይህን ያህል አበርክቱ ብሎ አንድ የተወሰነ ቁጥር ሊመድብልን ስለማይችል እኛ በግላችን ምን ያህል እንደምናበረክት ግብ ማውጣት ይኖርብናል። ይህም መጽሔቶቹን ስናበረክት የጋለ ስሜት እንዲኖረን ተጨማሪ ማበረታቻ ይሰጠናል። መውሰድ የምንፈልጋቸውን መጽሔቶችን ብዛት ለጉባኤው አስታወቅን ከሆነ ተጨማሪ መጽሔቶችን ለማበርከት ልንገፋፋ እንችላለን።
9 ሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት እንዲያውቁ እንፈልጋለን። የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨቱ ሥራ መጽሔቶች የሚያደርጉትን እገዛ ሙሉ በሙሉ እንጠቀምበት። — ማቴ. 10:7