በዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌላቸውን መጽሔቶች አበርክት
1 መጠበቂያ ግንብ የሚታተምበት ዓላማ “የይሖዋን የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊነት ከፍ ከፍ ለማድረግ” እንደሆነ ተገልጿል። የንቁ! መጽሔትም የሚታተምበት ምከንያት “ለመላው ቤተሰብ የሚጠቅም እውቀት ይግኝበታል። . . . ይህ መጽሔት ሰዎች . . . ሰላም የሰፈነበትና አስተማማኝ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ፈጣሪ በሰጠው ተስፋ ላይ ያላቸውን እምነት” ለማሳደግ ነው ተብሎ ተገልጿል። እነዚህ ቃላት ከመጽሔቶቹ ከራሳቸው የተጠቀሱ ናቸው። ለእነዚህ ግቦች መሳካት የተደረገው ጥረት በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ አንባቢዎች የመጽናናት ምንጭ ሆኖላቸዋል።
2 በሚያዝያና በግንቦት ወራት በምናከናውነው አገልግሎት እነዚህን መጽሔቶች እናበረክታለን። በዚህ በኩል ጥሩ ውጤት ለማግኘት መጽሔቶቹ ከያዟቸው ትምህርቶች ጋር በሚገባ መተዋወቅ አለብን። የእያንዳንዱን መጽሔት እትም አንብብ። በምታነብበትም ጊዜ ስታበረክት ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ነጥቦች ምልክት አድርግባቸው። ሰዎች የሚያስጨንቋቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ አስብ። በአካባቢህ ያሉትን ሰዎች የሚያሳስቧቸው ማኅበራዊ፣ ቤተሰባዊና ስሜታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ልባቸውን የሚነካና የበለጠ ለማወቅ ፍላጎት የሚያሳድርባቸውን ነገር ለመናገር ሞክር።
3 በሚያዝያ 1 መጠበቂያ ግንብ ተጠቅሞ ሰዎችን ማነጋገር:- አብዛኞቹ ሰዎች አሁን ደስታቸውን እየነጠቋቸው ያሉት ብዙ ችግሮች ተወግደው የሚያዩበት የተሻለ ዓለም እንዲመጣ ይናፍቃሉ።
ራስህን ካስተዋውቅክ በኋላ እንዲህ ለማለት ትችላለህ፦
◼ “በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ‘የተሻለ ዓለም መምጣቱ ሕልም ነውን?’ ከሚለው ርዕስ አንድ ጥሩ ነጥብ ባሳይዎት ደስ ይለኛል። እንዲህ ይላል:- “ይህ የእኛ ዓለም ፍጹም አለመሆኑ የተረጋገጠ ነው። . . . የዘመናችንን ወዮታዎች ዘርዝሮ ለመጨረስ የሚቻል አይመስልም። ይህ ሁኔታ ስለ ወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ለመያዝ አስቸጋሪ ያድርግብናል። አይደለም እንዴ? ይሁን እንጂ መዝሙር 37:11 ስለወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚል ባሳይዎ ደስ ይለኛል።” ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ ሰውዬው ስለዚህ ተስፋ ምን እንደተሰማው ጠይቀው። አዎንታዊ መልስ ከሰጠ በገጽ 4 ላይ “የተሻለ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል!” ወደሚለው ርዕስ ሂድና እንዲህ በለው:- “ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሁን ያነበብነው መዝሙር 37:11 ጭምር ተጠቅሰዋል። የተጠቀሱትን ጥቅሶች በራስዎ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው እየተመለከቱ እነዚህን ርዕሶች ቢያነቡ እንደሚደሰቱ አምናለሁ።” መጽሔቶቹ ሳያቋርጡ በፖስታ ቤት ቢላኩለት የሚያገኘውን ጥቅም ጥቀስለትና ኮንትራት እንዲገባ ጠይቀው። ኮንትራት መግባት ካልፈለገ ሁለት መጽሔቶችንና አንድ ብሮሹር በመደበኛው ዋጋ ልታበረክትለት ትችላለህ።
4 በሚያዝያ 15 መጠበቂያ ግንብ ተጠቅሞ ሰዎችን ማነጋገር፦ በገጽ 4 ላይ ያለው ርዕስ “እምነት የሚጣልበት አመራር ከየት ልታገኝ ትችላለህ? የሚል ጥያቄ ያቀርባል።
ራስህን ካስተዋወቅክ በኋላ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “ዛሬ በዓለም ላይ ብዙ ችግሮች አሉ። [በአካባቢው የተደረገ ወይም በዜና የተነገረ አንድ ነገር ካለ ጥቀስ።] ይህም ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ማን ሊያወጣን ይችል ይሆን ብለን እንድናስብ ያደርገናል። ደግነቱ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 አስደሳችና አስተማማኝ ኑሮ ለማግኘት መመሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ያረጋግጥልናል።” የጥቅሱን ካነበብክለት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መመሪያ የሆነበት ምክንያት እንዲገባን መጠበቂያ ግንብ እንዴት እንደሚረዳን አሳየው።
5 በንቁ! መጽሔት ተጠቅመህ ለማወያየት ከፈለግህ “ለልጆች የሚሆን እውነተኛ ተስፋ?” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የወጣውን የግንቦት 8 እትም ልትጠቀም ትችላለህ። ወላጆች ልጆች ስለሚያጋጥሟቸው ችግሮችና እነዚህን ችግሮች ለመወጣት የሚረዳ ነገር ለማወቅ የሚፈልጉ ሆነው ታገኛቸው የሆናል።
6 በዓለም ውስጥ ተወዳደሪ ስለሌላቸው መጽሔቶቻችን የጋለ የአድናቆት ስሜት ካለን ሌሎችም የመንግሥቱን ተስፋ ተቀብለው የይሖዋን የአጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ከፍ ከፍ በማድረጉ ሥራ መካፈል ይችሉ ዘንድ መጽሔቶቹን ለማበርከት ጉጉት ያድርብናል።—መዝ. 83:18