አቀራረቤን በየጊዜው መለወጥ አለብኝን?
በእያንዳንዱ የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ላይ ምሥክርነት ስንሰጥ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ልዩ ልዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ አቀራረቦች ይወጣሉ። በስብከቱ ሥራ በንቃት የሚሳተፉ ብዙ አስፋፊዎች አዳዲስ የመግቢያ ሐሳቦችንና የተለያዩ አቀራረቦችን ለማግኘት በጉጉት ይጠባበቃሉ። የመንግሥት አገልግሎታችን በየወሩ በርከት ያሉ ሐሳቦችን በማቅረብ ይህን ፍላጎታቸውን ያረካላቸዋል።
ይሁን እንጂ ትጠቀምባቸው የነበሩትን መግቢያዎች በየጊዜው መለወጡ አላስፈላጊ ሆኖ ይታይህ ይሆናል። ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ የምትካፈለው በየወሩ ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ለእኔ ይስማሙኛል ባልካቸው በአንዳንድ የመግቢያ ሐሳቦች መጠቀምን አዳብረህና እነዚህን መግቢያዎች ተጠቅመህ ጥሩ ውጤት አግኝተህ ይሆናል። አዘውትሮ በሚሠራባቸው እንደ መዝሙር 37:9–11፣ 2 ጴጥሮስ 3:13፣ ራእይ 21:4 በመሳሰሉትና በሌሎችም ጥቅሶች ጭምር ትጠቀም ይሆናል። እንዲህ ከሆነ መግቢያዎችህን በየጊዜው የመለወጥ ግዴታ እንዳለብህ ሆኖ እንዲሰማህ አያስፈልግም። ዋናው ግባችን የመንግሥቱን ተስፋ ለሌሎች ማካፈልና የይሖዋን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ያውቁ ዘንድ ለመርዳት ነው። ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ወቅታዊና የመስማት ፍላጎትን የሚቀሰቅሱ መግቢያዎችን በመጠቀም ጥሩ ውጤት አግኝተህ ከሆነ እነዚህን መግቢያዎች ለመጠቀም አታመንታ።