መጠበቂያ ግንብና ንቁ! ላለንበት አጣዳፊ ጊዜ የሚሆኑ መጽሔቶች!
1 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ዓለምን የሚያናጉ ክስተቶች በመከናወን ላይ ናቸው! በዙሪያችን ባለው ዓለም እንዲሁም በቲኦክራሲያዊው ድርጅት ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ በትኩረት ስናጤን የመንግሥቱን “ምሥራች” መስበካችን ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን። (ማር. 13:10 አዓት ) ይህ በዚህ በሚያዝያ ወር አገልግሎታችንን በቅንዓት ማከናወናችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።
2 የመልእክታችን አስፈላጊነት በዚህ ወር በምናከናውነው ልዩ አገልግሎት ጎልቶ ይታያል። በሚያዝያና በግንቦት የምናሰራጨውን የመንግሥት ዜና መውጣት በጉጉት እንጠብቃለን። ለዚህ ሥራ ያለንን ጉጉት ለመገንባትም ሆነ በክልላችን ውስጥ ያለውን ፍላጎት ለመቀስቀስ መጠበቂያ ግንብና ንቁ! ዓለምን እያናጉ ያሉት ክስተቶች ያላቸውን ትንቢታዊ ቁም ነገር የሚያጎሉ ርዕሶችን ይዘው ይወጣሉ። ለመጽሔቶቹ ያላቸውን ፍላጎት የሚቀሰቅስ አቀራረብ ልናዘጋጅ የምንችለው እንዴት ነው?
3 የሚከተሉትን ነጥቦች መሠረት በማድረግ ውጤታማ የሆኑ አቀራረቦችን ልታዘጋጅ ትችላለህ:- (1) በአካባቢህ ላሉት ሰዎች ይስማማል ብለህ የምታስበውን ከመጽሔቶቹ በአንዱ ውስጥ የሚገኝ አንድ ርዕስ ምረጥ (2) የሰውዬውን ፍላጎት ይቀሰቅሳል ብለህ የምታስበውን አንድ ዓረፍተ ነገር ወይም አንድ ጥቅስ ከርዕሱ ውስጥ ምረጥ (3) ወዳጃዊ ሰላምታን ጨምሮ አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ የሚያጎላ ጥያቄ ወይም ዓረፍተ ነገር ከዚያም መጽሔቱን እንዲወስድ መጋበዝን የሚያጠቃልል አጠር ያለ አቀራረብ አዘጋጅ። በግልጽ ማየት እንደምትችለው እነዚህ አቀራረቦች በጣም ቀላልና ያልተወሳሰቡ ናቸው። ምናልባት አንተም አብሮህ ከሚያገለግል አንድ አስፋፊ ጋር ተገናኝተህ አንድ አቀራረብ ልትዘጋጅ ትችላለህ።
4 የሚያዝያ 22 ንቁ! “እነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት ናቸውን?” የሚል ጥያቄ ስለሚጠይቅ አንተም “ማመራመር” በተባለው መጽሐፍ ገጽ 13 ላይ “የመጨረሻዎቹ ቀናት” የሚለውን ርዕስ ልትከልስ ትችላለህ። ከዚያም እንዲህ ብለህ ለመጀመር ትችላለህ:-
◼ “በዙሪያችን እየተፈጸመ ስላለው አስደንጋጭ ሁኔታ ከሰዎች ጋር እየተነጋገርን ነበር። ይህ መጽሔት ምን እንደሚል ልብ ይበሉ . . .”
5 የሚያዝያ 1 “መጠበቂያ ግንብ” “ሃይማኖት ሊወያዩበት የማይገባ ርዕስ ነውን?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይህን መጽሔት በምታበረክትበት ጊዜ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ልትወያይባቸው ከማይገቡ ርዕሶች መካከል አንዱ ሃይማኖት ነው ምክንያቱም በጣም አወዛጋቢ ጉዳይ ነው ይባላል። ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዎታል?” ከዚያም በመጽሔቱ ላይ የሚገኝ አንድ ዓረፍተ ነገር አሳየው።
6 ምናልባት “ሃይማኖታዊ እውነት ሊደረስበት ይችላልን?” የሚለውን የሚያዝያ 15 “መጠበቂያ ግንብ” ትጠቀም ይሆናል። በዚህ መግቢያ ብትጠቀም የተሻለ ምላሽ ታገኝ ይሆናል:-
◼ “በአሁኑ ጊዜ በጣም ብዙ ሃይማኖቶች ስላሉ አንዳንድ ሰዎች ሃይማኖታዊ እውነት ሊደረስበት ስለመቻሉ ያስባሉ። ይህ መጽሔት ለእኔና ለእርስዎ ጥያቄ የሚያረካ መልስ የምናገኝበትን መንገድ ግልጽ ያደርጋል . . .”
7 ወደ አገልግሎት ከመሰማራትህ በፊት ከአቀራረብህ ጋር በደንብ እንድትተዋወቅ ከሌላ አስፋፊ ጋር ሆነህ ለምን አትለማመድም? የተዋጣልህና የበለጠ የመተማመን መንፈስ ያለህ አንድትሆን የሚያደርግህን ጠቃሚ ሐሳብ እርስ በርሳችሁ ልትለዋወጡ እንደምትችሉ የታወቀ ነው።
8 የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየቀረበ በሄደ ቁጥር ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ሸሽተው እንዲወጡ ለመርዳት እንጣደፍ። (ራእይ 18:4) በዚህ በማይደገም ሥራ ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ዓቢይ ሚና ይጫወታሉ። ይሖዋ እነዚህን ግሩም መሣሪያዎች ለእኛ መጠቀሚያ ብሎ በማዘጋጀቱ አመስጋኞች ነን!