ይሖዋ ኃይል ይሰጣል
1 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ‘በአሕዛብ መካከል መልካም’ ጠባይ እያሳየን ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ተሰጥቶናል። (1 ጴጥ. 2:12፤ ማቴ. 24:14) የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን በመሆኑና ድካምና ጉድለቶች ስላሉብን ይህንን ሥራ በራሳችን ጥረት ብቻ ማከናወን ፈጽሞ አንችልም። (2 ጢሞ. 3:1–5) እንደሚረዳን በመተማመን ይሖዋን ተስፋ ለማድረግ በመቻላችን ምንኛ ደስተኞች ነን!
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሟል። (2 ቆሮ. 11:23–27) እነዚህን ፈተናዎች መቋቋምና የተሰጠውን ሥራ አከናውኖ መጨረስ የቻለው እንዴት ነበር? ይሖዋ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ሰጥቶት ነበር። (2 ቆሮ. 4:7 አዓት) ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ምክንያት ሁሉን ነገር እችለዋለሁ” ብሎ በጻፈ ጊዜ ስላገኘው መለኮታዊ እርዳታ ገልጿል። (ፊል. 4:13 አዓት) ይሖዋ እኛንም በዚሁ ዓይነት መንገድ ይረዳናል። ይህንን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ሳናቋርጥ በመጸለይ:- ኢየሱስ ‘መለመናችንን፣ መፈለጋችንንና ማንኳኳታችንን እንድንቀጥል፤’ እንዲሁም ተስፋ እንዳንቆርጥ አጥብቆ አሳስቦናል። (ሉቃስ 11:5–10) በጸሎት መጽናታችን ነገሩ በጣም እንዳስጨነቀን፣ በኃይል እንደምንፈልገውና የተነሳንበት ዓላማ ልባዊ መሆኑን ይሖዋ እንዲመለከት ያስችለዋል። (መዝ. 55:17፤ 88:1, 13፤ ሮሜ 1:9–11) ጳውሎስ “ሳታቋርጡ ጸልዩ” ብሎ ባሳሰበን ጊዜ በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። (1 ተሰ. 5:17) ጸሎት የይሖዋን እርዳታ ከምናገኝባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ነው።
4 ቲኦክራሲያዊ መመሪያ በመከተል፦ “ቲኦክራሲ” ማለት አፍቃሪ በሆነ “አምላክ የሚመራ” ማለት ነው። ሥልጣኑን አምኖ በመቀበልና ከባድም ሆነ ቀላል ውሳኔ ስናደርግ የእርሱን መመሪያዎች በመከተል ከአገዛዙ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። “ታማኝና ልባም ባሪያ” የቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ምድራዊ ወኪል ነው። (ማቴ. 24:45–47) የይሖዋን በረከት ለማግኘት ‘ባሪያው’ ከሚጠቀምበት ድርጅቱ ጋር መተባበር የግድ አስፈላጊ ነው። (ከዕብራውያን 13:17 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ከጎኑ በታማኝነት ጸንተን ከቆምንና ሕጎቹን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ከሆንን የምንፈልገውን ኃይል በተገቢው ጊዜ በመስጠት ወሮታውን ይከፍለናል።— ዕብ. 4:16
5 ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ዝምድና እንዳይቋረጥ በማድረግ፦ ፍቅር የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መለያ ምልክት ነው። (ዮሐ. 13:34, 35) በጣም ብዙ ዓይነት ባሕርይዎች ስላሉ ባሉት የባሕርይ ልዩነቶች የተነሳ በመካከላችን ግጭት ሊከሰት ይችላል። ከአንጀት የምንራራና አንዳችን ሌላውን በነፃ ይቅር የምንል መሆን ያስፈልገናል። (ኤፌ. 4:32) ይህም ከወንድሞቻችን ጋር በእምነት እንደተቀራረብን ለመቆየትና መከራ ሲደርስባቸው በሚያሳዩት ጽናት እንድንበረታታ ያስችለናል። ‘በዓለም ሁሉ ያሉ ወንድሞቻችን ይህን ዓይነት መከራ እንደሚቀበሉ እናውቃለን፤’ በመሆኑም በእነርሱ ላይ የሚደርሱትን ዓይነት ተጽእኖዎች ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ከአምላክ እናገኛለን።— 1 ጴጥ. 5:9 የ1980 ትርጉም
6 ጥሩ የግል ጥናት ልማድ እንዲኖረን በማድረግ፦ አእምሯችንንና ልባችንን በመንፈሳዊ ማጠናከራችን የሰይጣንን ጥቃት ለመመከት ያስችለናል። (1 ጴጥ. 5:8) ጥሩ የሆነ የግል ጥናት ልማድ ያለንን የአምላካዊ እውቀት ትጥቅና ስንቅ ያጎለብትልናል። በየጊዜው ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ልንጠቀምበት እንችላለን። ለመዳን “ትክክለኛ እውቀት” ማግኘት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ጳውሎስ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (1 ጢሞ. 2:3, 4 አዓት) ስለዚህ መንፈሳዊ ምግብ ሳያሰልሱ መመገብ ወሳኝ ነው።
7 ጠንካራ ሆነን እንድንቀጥል እኛን ለመርዳት የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ሁሉ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ይቀርቡልናል። የጉባኤውን እንቅስቃሴዎች በሙሉ ልብ መደገፋችን ‘ያለድካም ለመጓዝ’ ዋስትና ይሆነናል።— ኢሳ. 40:29–31