ቤተሰቦችን ደስተኛ ለማድረግ የሚረዱ ዝግጅቶች
1 መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በቤተሰብ ተቋም ላይ ጎጂ ውጤት እንደሚያስከትሉ ይጠቁማል። (2 ጢሞ. 3:1–4፤ ራእይ 12:12) ቲኦክራሲያዊ የሆኑ ቤተሰቦች እንኳ ልጆችን በእምነት ውስጥ ማሳደግ ብዙውን ጊዜ ፈታኝ ይሆንባቸዋል። ይህ እውነት አይደለምን? በዓለም ውስጥ ያሉ አያሌ ቤተሰቦች በጣም ግራ እንደተጋቡና እርዳታ እየፈለጉ እንዳሉ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። በሰኔ ወር “ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት ” እና “የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው ” የተባሉትን መጻሕፍት ስናበረክት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚቀርብላቸውን እርዳታ እንደሚያደንቁ አያጠራጥርም።
2 በር ስናንኳኳ ብዙውን ጊዜ የሚከፍቱልን ወጣቶች ናቸው። እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “ወጣት እንደመሆንህ መጠን ከአንተ ጋር ለመነጋገር አጋጣሚ ስላገኘሁ ተደስቼአለሁ። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ አንተ ያሉ ወጣቶችን በቀጥታ የሚመለከት ነገር ተናግሯል። (መክብብ 12:1ን አንብብ) ይህ ጥቅስ የወደፊቱ ሕይወታችን አስደሳች እንዲሆን ከፈለግን በወጣትነታችን አምላክን ልናስታውሰው እንደሚገባ ያሳያል። አንድ ወጣት ፈጣሪያችን ስለሆነው አምላክ ማሰብ እንዳለበት ይሰማሃልን? ይህ የሚያመጣልን ደስታ ይኖራልን? (መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።) እስቲ በዚህ መጽሐፍ ላይ የተሰጠ አንድ ሐሳብ ላሳይህ።” ገጽ 191ን ገልጠህ አንቀጽ 15 ላይ ያሉትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓረፍተ ነገሮች አንብብ። ከዚያም ወደ አርዕስት ማውጫው ተመለስና ከአርዕስቶቹ መካከል ጥቂቶቹን አሳየው።
3 አንዳንድ አስፋፊዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ ወጣትነትህ የተባለውን መጽሐፍ ለወጣቶች በማበርከት ረገድ ጥሩ ተሳክቶላቸዋል። ልክ እንደ መጽሔቶች በመንገድ ላይ ምሥክርነትም በሰፊው ሊበረከት ይችላል። በተጨማሪም አስተማሪዎችንና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የአስተዳደር ሠራተኞችን ቀርቦ ማነጋገር ይቻላል። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማር አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር በዴስኩ ላይ ወጣትነትህ የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ በማስቀመጥ በሁለት ወር ውስጥ ወጣትነትህ የተባለውን መጽሐፍ 75 ቅጂዎች ማበርከት ችሏል።
4 በሩን የከፈቱልን አዋቂዎች ወይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቢሆኑስ? አብዛኞቹ ሰዎች በጣም የሚያስቡላቸው ልጆች፣ የወንድም ወይም የእህት ልጆች አለዚያም የልጅ ልጆች አሏቸው። መጽሐፉን ራሳቸው እንዲያነቡት ሐሳብ ከማቅረብ በተጨማሪ ወጣት ለሆኑ ዘመዶቻቸው በስጦታነት ሊያበረክቱት እንደሚችሉም በዘዴ ልንጠቁማቸው እንችላለን።
5 ቤተሰብ በተባለው መጽሐፋችን ላይ ያሉትም አንዳንድ ክፍሎች የወጣቶችን ስሜት ይማርካሉ። ከእነዚህም መካከል በምዕራፍ 2 ላይ በተለይ “በመጀመሪያ ራስህን እወቅ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን አንቀጽ 7 ወይም “አቻነት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያሉት አንቀጽ 13, 15 እና ከ19–21 እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው።
6 አዋቂዎች በቤተሰብ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጠቃሚ ነጥቦች ያገኛሉ። የአርዕስት ማውጫውን አሳያቸው። ምዕራፍ 8 እና 10 ወላጆችን የሚረዱ ሐሳቦች ይዘዋል። ከምዕራፍ 4–6 ያሉት ምዕራፎች ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ያሳያሉ። እርግጥ ነው፣ ይህን ስናደርግ ዘዴኛ መሆን አለብን። ምናልባት የቤቱ ባለቤት የጋብቻ ችግሮችን በተመለከተ ለሌሎች ምክር እንዲሰጥ ተጠይቆ ምን ብሎ እንደሚናገር ግራ ገብቶት ሊሆን ይችላል። ቤተሰብ በተባለው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ግን አምላክ የጋብቻ መሥራች እንደመሆኑ መጠን ላገቡ ሰዎች የሰጠውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥበባዊ ምክር ሊያገኝ ይችላል። በተጨማሪም አዋቂዎች ስለ ጋብቻ ወይም ስለ ማግባት የሚያስቡ ወጣት ዘመዶቻቸውን ለመርዳት ከምዕራፍ 2–6 ባሉት ምዕራፎች ሊጠቀሙ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የራሳቸውን ልጆች ለማስተማር በምዕራፍ 12 መጠቀም ይችላሉ።
7 መግቢያ እንዲሆነን እንዲህ በማለት ልንናገር እንችላለን:- “በዚህ ወር በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋም አምላክ በሚሰጠው ጥበብ እንዴት መጠቀም እንደምንችል ከሰዎች ጋር እየተነጋገርን ነው። ሁላችንም የቻልነውን ያህል እንጥራለን፤ ሆኖም በዚህ ረገድ ይበልጥ እንዲሳካልን የሚረዳ ነገር ላሳይዎት።” ከዚያም መጽሐፎቹን አሳየውና በዚህ ወር የሚበረከቱበትን ቅናሽ ዋጋ ማለትም እያንዳንዳቸውን በ3 ብር መውሰድ እንደሚችል ንገረው። ሁኔታው አመቺ በሚሆንበት ጊዜ እንደ ቆላስይስ 3:12, 18–21 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንብብ። በሰኔ ወር ብዙ ሰዎች የቤተሰባቸውን ሕይወት አስደሳች እንዲያደርጉ እንደምንረዳቸው አያጠራጥርም።