ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ዋጋማነት እንዲገነዘቡ እርዷቸው
1 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አድርጎላቸዋል። ሉቃስ 24:45 “በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው” በማለት ይናገራል። በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከፈለጉ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ማስተዋል እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። (መዝ. 1:1, 2) የእኛም የስብከት ሥራ ዓላማ ይኸው ነው። ግባችን ‘ሰዎች ኢየሱስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ለማስተማር’ እንድንችል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ነው። (ማቴ. 28:20) የሚከተሉት ጥቂት ሐሳቦች ይህንን ግብ በአእምሮህ ይዘህ ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ ሊረዱህ ይችላሉ።
2 ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ በሚከተለው መንገድ በቀላሉ ውይይት መጀመር ትችላለህ:-
◼ “የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ምን ያህል ዋጋማ እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ ነገር ላሳይዎ ፈልጌ ነበር። ብዙ ሰዎች ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መኖር ያስቸግራቸዋል። አብረውን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር የተሻለ ዝምድና ለማበጀት ምን ማድረግ እንችላለን? [መልስ ከሰጠህ በኋላ ማቴዎስ 7:12ን አሳየው። በተጨማሪም ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 236 አንቀጽ 17 ላይ የተገለጹትን ሐሳቦች አካፍለው።] ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር የያዘውን ጥበብ የሚያሳይ ሌላው ምሳሌ ነው። በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ ባልና ሚስት እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ከፍተኛ ደስታ ለማግኘት እንዲችሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር አሳይዎታለሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርባቸውን ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ ለመምራት የሚረዱ ምክሮች በሚገልጸው በምዕራፍ 29 ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
3 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት ያደረበት ሰው አነጋግረህ ከነበረ የሚከተለው አቀራረብ ጥናት ለማስጀመር ሊረዳ ይችላል:-
◼ “ሰላምና ደህንነት በሰፈነበት ዓለም ውስጥ መኖር የማይፈልግ ሰው እንደማይገኝ የታወቀ ነው። ሁሉም ሰው የሚፈልገው ይህንን ሆኖ ሳለ ዓለማችን በዓመፅ የተሞላውና መረጋጋት የማይታይበት ለምንድን ነው? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።]” 2 ቆሮንቶስ 4:4ን አንብብ። አምላክ ሰይጣንን አጥፍቶ ዘላቂ ሰላምና ደስታ የሰፈነበት ዓለም የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ ግለጽለት። ራእይ 21:3, 4ን እንብብ። ከዚያ “በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ ጭንቀት የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ ማድረግ የሚችሉት ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ጥቅሶች አሳይዎታለሁ” ማለት ትችላለህ።
4 ጥናት ለማስጀመር የሚያስችል ቀጥተኛ አቀራረብ ተጠቅመህ ጥሩ ምላሽ አግኝተህ ከነበረ ተመልሰህ ስትሄድ እንደሚከተለው ማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ውይይታችን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ለምን እንደሚጠቅም ተነጋግረን ነበር። ይበልጥ ለማጥናት ልባዊ ጥረት ማድረጋችን አምላክ ወደፊት ምን እንደሚያመጣልን ለማወቅ ያስችለናል። [ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።] በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ ምን ተስፋዎች እንደሰጠና እርሱን ማስደሰት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ እንዲችሉ የረዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም አለን።” ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ አሳይተህ የምዕራፎቹን ርዕሶች ከከለስህ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናው እንዴት እንደሆነ አሳየው።
5 ልበ ቅን ሰዎች የአምላክ ቃል ያለውን ከሁሉ የላቀ ዋጋ እንዲገነዘቡ ማድረግ ከቻልክ ከሁሉ የተሻለ እርዳታ አድርገህላቸዋል ማለት ነው። የአምላክን ቃል በማጥናት ሊያገኙ የሚችሉት ጥበብ ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝ “የሕይወት ዛፍ” ሊሆንላቸው ይችላል።— ምሳሌ 3:18