እንደገና አገልግሎት እንዲጀምሩ እርዷቸው
1 ሐዋርያው ጳውሎስ መሰል ክርስቲያኖች ሊገጥማቸው የሚችለውን መንፈሳዊ አደጋ በመገንዘብ “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 13:11) ጳውሎስ በመንፈሳዊ ድብታ የተያዙት ወንድሞቹ ሁኔታ አሳስቦት ነበር። እንደገና በአዲስ መንፈስ እንዲያነቃቁ ለመርዳት ጓጉቶ ነበር።
2 በእውነትም የዚህ አሮጌ ዓለም ሌሊት ሊያልፍ ነው፤ የአዲሱ ዓለምም ንጋት ቀርቧል። (ሮሜ 13:12) በምሥራቹ የስብከት ሥራ ከእኛ ጋር መተባበራቸውን ስላቆሙት ወንድሞቻችን የምንጨነቅበት ጥሩ ምክንያት አለን። በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ከ60 የሚበልጡ አስፋፊዎች እንደገና አገልግሎት ጀምረዋል። አገልግሎት ያቆሙ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን እንደገና እንዲያገለግሉ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
3 የሽማግሌዎች ድርሻ፦ አብዛኞቹ አገልግሎት ያቆሙ ወንድሞችና እህቶች ተስፋ በመቁረጥ፣ በግል ችግር፣ በቁሳዊ አስተሳሰብ ወይም በሌሎች የኑሮ ጭንቀቶች ምክንያት መስበካቸውን አቆሙ እንጂ እውነትን እርግፍ አድርገው አልተውም። (ሉቃስ 21:34-36) የሚቻል ከሆነ አገልግሎት ከማቆማቸው በፊት መርዳቱ ይበልጥ የተሻለ ነው። አንድ የጉባኤ አስፋፊ የአገልግሎት እንቅስቃሴውን ሪፖርት በማድረግ በኩል አዘውታሪ ሳይሆን ሲቀር የጉባኤው ጸሐፊ ለመጽሐፍ ጥናት መሪው ሊያሳውቀው ይገባል። የእረኝነት ጉብኝት ለማድረግ ዝግጅቶች ሊደረጉ ይችላሉ። ሽማግሌዎች የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነና እንዴት እርዳታ መስጠት እንደሚቻል ለማወቅ መጣር ይኖርባቸዋል።— መስከረም 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-23ን ተመልከቱ።
4 ሌሎች እርዳታ ሊያበረክቱ የሚችሉበት መንገድ፦ አብዛኞቻችን አገልግሎት ያቆመ ሰው እናውቃለን። ቀደም ሲል በጣም እንቀርበው የነበረ ሰው ሊሆን ይችላል። እርሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? ቤቱ ጎራ ብለህ ለምን ጥቂት አታጫውተውም? እንደናፈቀህ ግለጽለት። ደስተኛና አዎንታዊ ሆነህ አነጋግረው። በመንፈሳዊ ስለመታመሙ ሳትጠቅስ ስለ እርሱ እንደምታስብ ግለጽለት። የሚያንጹ ተሞክሮዎችን ወይም በጉባኤው ውስጥ በመከናወን ላይ ያሉ ሌሎች መልካም ነገሮችን ንገረው። ስለ ስብሰባዎቻችን እና “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” ስለተባለው የአውራጃ ስብሰባ ሞቅ ባለ ስሜት ንገረውና በዚያ እንዲገኝ አበረታታው። ከጉባኤው ጋር እንደገና መሰብሰቡ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ሊረዳው ይችላል። አብሮህ ወደ ስብሰባ እንዲሄድ ጋብዘው። ያገኘኸውን ምላሽ ለሽማግሌዎች ንገራቸው።
5 አገልግሎት ያቆመ አንድ ሰው ወደ ስብሰባ ሲመጣ ቀደም ብሎ የሚያውቃቸውን ሰዎች በማግኘቱ የእፍረት ስሜት ሊያድርበት ይችላል። “የት ጠፍተህ ነበር?” ብለህ አትጠይቀው። ከዚያ ይልቅ ጥሩ አቀባበል እንደተደረገለት እንዲሰማው አድርግ። አጫውተው። ከማያውቃቸው ሰዎች ጋር አስተዋውቀው። የመዝሙር መጽሐፍና የሚጠናውን ጽሑፍ እንድታሳየው በስብሰባው ወቅት አብረኸው ተቀመጥ። ሌላ ጊዜም እንዲመጣ አበረታታው፤ የአንተ እርዳታ የሚያስፈልገው ከሆነም ልትረዳው እንደምትፈልግ ግለጽለት።
6 ይሖዋና ኢየሱስ ለባዘኑት ሰዎች ሞቅ ያለ ፍቅር ስላላቸው እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በመንፈሳዊ ሲያገግሙ ማየት ያስደስታቸዋል። (ሚል. 3:7፤ ማቴ. 18:12-14) ሌሎች እንደገና ይሖዋን ማገልገል እንዲጀምሩ በመርዳት ከተሳካልን እኛም ተመሳሳይ ደስታ ልናገኝ እንችላለን።