የቀዘቀዙትን አትርሷቸው
1. የቀዘቀዙትን ልናበረታታቸው የሚገባን ለምንድን ነው?
1 የምታውቀው የቀዘቀዘ አስፋፊ አለ? ምናልባት ይህ ሰው ከጉባኤው ጋር የነበረውን ግንኙነት በማቋረጡ ከእውነት ርቆ ሊሆን ይችላል። ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል እንዲህ ዓይነት ሰው አጋጥሞህ ይሆናል። ይህ ግለሰብ መንፈሳዊ ወንድማችን ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም። አሁንም ቢሆን ለእርሱ ፍቅር እንዳለን ልናረጋግጥለት እንዲሁም ወደ ጉባኤው ብሎም ‘ወደ ነፍሳችን እረኛና ጠባቂ’ እንዲመለስ ልንረዳው እንፈልጋለን።—1 ጴጥ. 2:25
2. አንድን የቀዘቀዘ ሰው እንዴት ማበረታታት እንችላለን?
2 አሳቢነት አሳዩ:- ጥቂት ጊዜ ወስደን ስልክ መደወላችን ወይም ሄደን መጠየቃችን የቀዘቀዘውን ወንድም እንዳልረሳነው እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። ስናገኘው ምን ልንል እንችላለን? ስለ እርሱ እያሰብን እንደነበረ ማወቁ ብቻ እንኳ ሊያበረታታው ይችላል። ጭውውታችሁ በገንቢ ነገሮች ላይ ያተኮረና የሚያንጽ እንዲሆን አድርጉ። (ፊልጵ. 4:8) በቅርቡ ካደረግነው የጉባኤ ስብሰባ ያገኘነውን አስደሳች ነጥብ አንስተን ልንነግረው እንችላለን። በቀጣዩ የጉባኤ ወይም ትልቅ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ልንጋብዘው እንዲሁም ቦታ ብንይዝለት አሊያም ይዘነው ብንሄድ ደስ እንደሚለን ልንገልጽለት እንችላለን።
3. አንዲት እህት በድጋሚ አገልግሎት መጀመር የቻለችው እንዴት ነበር?
3 እህቶች በአንድ ክልል ውስጥ ሲያገለግሉ ከ20 ዓመት በላይ ከጉባኤ ርቃ የነበረች አንዲት እህት አገኙ። ይህች እህት መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኛ ባትሆንም ያገኘቻት እህት አዲስ የወጡ መጽሔቶችን ይዛ በመሄድ ትጠይቃት ነበር። ከአውራጃ ስብሰባ በኋላ ይህች አስፋፊ ከስብሰባው ያገኘቻቸውን አንዳንድ ነጥቦች ለቀዘቀዘችው እህት አካፈለቻት። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህች እህት በድጋሚ አገልግሎት ጀመረች።
4. በስብሰባ ላይ እንደገና መገኘት የጀመረን ሰው እንዴት ልንይዘው ይገባል?
4 አንድ የቀዘቀዘ ሰው ጉባኤ ሲመጣ:- አንድ የቀዘቀዘ ወንድም በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምር እንዴት ልንይዘው ይገባል? ኢየሱስ ለጊዜው ትተውት የነበሩትን ደቀ መዛሙርቱን የያዛቸው እንዴት ነበር? ከልብ በመነጨ ስሜት ‘ወንድሞቹ’ እንደሆኑ አድርጎ የገለጻቸው ከመሆኑም በላይ እንደሚተማመንባቸው አሳይቷል። እንዲያውም በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:10, 18, 19) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ደቀ መዛሙርቱ ምሥራቹን ‘ያለማሰለስ’ በማወጁ ሥራ ተጠምደው ነበር።—ሥራ 5:42 NW
5. ስለ አንድ የቀዘቀዘ አስፋፊ ለሽማግሌዎች ልናሳውቃቸው የሚገባን በየትኞቹ አጋጣሚዎች ነው?
5 አንድን የቀዘቀዘ ሰው ጥናት ከማስጀመራችን ወይም ለረጅም ጊዜ ከጉባኤ ጠፍቶ የቆየ ወንድም አብሮን እንዲያገለግል ከመጋበዛችን በፊት ሽማግሌዎችን ማማከር ይኖርብናል። በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ አንድ የቀዘቀዘ አስፋፊ ካገኘን ሽማግሌዎች አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርጉለት ልናሳውቃቸው ይገባል።
6. የቀዘቀዙትን መርዳት ምን ሊያስገኝልን ይችላል?
6 መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው የሚድኑት የሕይወትን ሩጫ እስከ መጨረሻው የሚሮጡ ብቻ ናቸው። (ማቴ. 24:13) ስለዚህ ተሰናክለው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ከጉባኤ የራቁ ሰዎችን አትርሷቸው። እንደነዚህ ላሉት ሰዎች ልባዊ አሳቢነት በማሳየት በትዕግሥት የይሖዋን ዓይነት ፍቅር የምናንጸባርቅ ከሆነ እነርሱም እንደ እኛ ቅዱስ አገልግሎት ሲያቀርቡ ማየት የሚያስገኘውን ደስታ ልንቀምስ እንችላለን።—ሉቃስ 15:4-10