በምሽት ምሥክርነት ለመካፈል ሞክርሃል?
1 ሁላችንም በሥራችን ውጤታማ ስንሆን እንደሰታለን። በሌላው በኩል ደግሞ መልካም ውጤቶች ማግኘት ሳንችል ስንቀር ሥራ አሰልቺና የማያስደስት ይሆንብናል። ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት በግለሰብ ደረጃ የሚክስና በረከት የሚያስገኝ ነው። (ከመክብብ 3:10-13 ጋር አወዳድር።) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በስብከቱ ሥራችን ላይም ይሠራል። ከቤት ወደ ቤት ሄደን ከሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከተወያየን በኋላ በመንፈሳዊ ታድሰን ወደ ቤታችን እንደምንመለስ እናውቃለን። አንድ ነገር እንዳከናወንን ይሰማናል።
2 በአንዳንድ አካባቢዎች በቀኑ ውስጥ በተወሰነ ሰዓት ላይ ሰዎችን እቤታቸው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። በአንዳንድ ቦታዎች በሥራ ሰዓት ወደ ሰዎች ቤት ስንሄድ ብዙዎቹ እቤታቸው እንደማይገኙ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ብዙ ጉባኤዎች እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ሲሉ የምሽት ምሥክርነት ለመስጠት ሁኔታዎችን በማመቻቸታቸው ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ብዙ አስፋፊዎች ከሥራ ሰዓት በኋላ ወደ ሰዎች ቤት ሲሄዱ ብዙ ሰዎችን እቤታቸው እንዳገኙና ይህ ሰዓት ሰዎች ዘና የሚሉበትና በይበልጥ የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ የሚሆኑበት ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ በምሽት ምሥክርነት ለመካፈል ሞክረሃልን?— ከማርቆስ 1:32-34 ጋር አወዳድር።
3 ሽማግሌዎች ለምሽት ምሥክርነት ዝግጅት አድርጉ፦ በአንዳንድ አካባቢዎች ከሰዓት በኋላና አመሻሹ ላይ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ማድረግ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። ከሰዓት በኋላ ከትምህርት ቤት ለሚመለሱ ወጣት አስፋፊዎችና ከሥራ ሰዓት በኋላ አገልግሎት ለሚወጡ ሠራተኞች አሳቢነት ማሳየት ይገባል። ቅዳሜና እሁድ በመስክ አገልግሎት መካፈል የማይችሉ አንዳንድ አስፋፊዎች በሳምንቱ መሃል አመሻሽ ላይ በሚደረገው ምሥክርነት መካፈላቸው በስብከቱ ሥራ ቋሚ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል።
4 በምሽት ምሥክርነት ወቅት ልትሳተፍባቸው የምትችላቸው የተለያዩ ሥራዎች አሉ። መጽሔቶችን ወይም በወሩ የሚበረከተውን ጽሑፍ በመጠቀም ከቤት ወደ ቤት መመሥከር ትችላለህ። አስፋፊዎች በቀኑ መሀል ወይም ቅዳሜና እሁድ እቤታቸው ያላገኟቸውን ሰዎች ቤታቸው ለማግኘት ምሽት አመቺ ወቅት ነው። ከሥራ ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ሰዎችን ለማግኘት ስለሚያስችል የአገልግሎት ክልሉ በመንገድ ላይ ለሚደረግ ምሥክርነት አመቺ ሊሆን ይችላል። ብዙዎች ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ምሽት ላይ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ከሁሉ የተሻለ አመቺ ጊዜ ሆኖ አግኝተውታል።
5 ጠንቃቃና ዘዴኛ ሁኑ፦ በአንዳንድ አካባቢዎች ጨለምለም በሚልበት ጊዜ ወይም ከመሸ በኋላ ወደ ውጪ መውጣት አደገኛ ሊሆን ይችላል። ጥሩ መብራት ባለባቸው መንገዶችና ለደህንነትህ ምንም ስጋት እንደማይፈጥሩ ወደምትተማመንባቸው ቤቶች ወይም የአፓርታማ ሕንፃዎች ስትሄድ ሁለት ሁለት ወይም በቡድን ሆኖ መሄዱ ጥበብ ነው። አንድ ቤት ስታንኳኳ በደንብ ልትታይ በምትችልበት ቦታ ላይ ቁም፤ እንዲሁም ማንነትህን በግልጽ አሳውቅ። አስተዋይ ሁን። የሄድከው እንደ ምግብ ሰዓት ባሉት አመቺ ባልሆኑ ጊዜያት እንደሆነ ከተገነዘብክ ሌላ ጊዜ ተመልሰህ እንደምትመጣ ግለጽላቸው። ምናልባት የቤተሰቡ አባላት ለመተኛት በሚዘጋጁባቸው ሰዓታት በጣም ሲመሽ ወደ ሰዎች ቤት ከመሄድ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ምሥክርነትህን በጊዜ በአመሻሹ ላይ ብታከናውን የተሻለ ይሆናል።
6 ‘ሌሊትና ቀን ቅዱስ አገልግሎት’ ስናቀርብለት ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን የተረጋገጠ ነው።— ራእይ 7:15