‘ቤተሰባችሁን ገንቡ’
1 በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ባሕሎች በሙሉ የቤተሰብ ኑሮ እየፈራረሰ እንዳለ ግልጽ ነው። የሰይጣን ዓለም በማታለያና በመጥፎ ሥነ ምግባር ተጥለቅልቋል። (1 ዮሐ. 5:19) ይህም ‘ቤተሰባችንን መገንባቱና’ ሌሎችም እንዲሁ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማስተማሩ አጣዳፊ መሆኑን ያስገነዝበናል።— ምሳሌ 24:3, 27 NW
2 የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከለላ ናቸው:- እውነተኛ የቤተሰብ ደስታ ለማግኘት ቁልፉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ነው። እነዚህ የመለወጥ ኃይል ያላቸው እውነቶች በሁሉም የኑሮ ዘርፎች እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል የሚጠቅሙ ናቸው። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ላይ የሚያውል ቤተሰብ ደስታና አምላካዊ ሰላም ያገኛል።— ከኢሳይያስ 32:17, 18 ጋር አወዳድር።
3 ቤተሰባችንን ለመገንባት ሊረዱን የሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች እጥር ምጥን ባለ መንገድ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር በተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ውስጥ ተዘርዝረው ይገኛሉ። እያንዳንዱ ምዕራፍ የሚደመደመው እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ማስታወስ የሚኖርበትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጎላ አድርጎ በሚገልጽ የማስተማሪያ ሣጥን ነው። አብዛኞቹ ሣጥኖች “እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊጠቅሙ የሚችሉት እንዴት ነው . . .?” በሚለው ጥያቄ ይጀምራሉ። ይህም አምላክ ስለ ጉዳዩ ባለው ሐሳብ ላይ እንድናተኩር ስለሚረዳ ውይይት በሚደረግበት ርዕስ ላይ እርሱ ያለውን አመለካከት እናገኛለን።— ኢሳ. 48:17
4 እንግሊዝኛ ማንበብ የምትችል ከሆነ ከመጽሐፉ ጋር ተዋወቅ። የተለያዩ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ ሊረዱህ የሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የት ልታገኝ አንደምትችል ጠንቅቀህ እወቅ። መጽሐፉ እንደሚከተሉት ያሉትን ጉዳዮች ያብራራል:- አንድ ሰው የወደፊት የትዳር ጓደኛውን በሚመርጥበት ጊዜ ምን ነገሮችን መመልከት እንደሚኖርበት (ምዕራፍ 2)፣ ዘላቂ ደስታ የሰፈነበት ጋብቻ ለመመሥረት በጣም አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ (ምዕራፍ 3)፣ ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻቸውን እምነት የሚጣልባቸውና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አድርገው ሊያሳድጓቸው የሚችሉት እንዴት እንደሆነ (ምዕራፍ 6)፣ ቤተሰቡን ከአፍራሽ ተጽዕኖዎች መከላከል የሚቻለው እንዴት እንደሆነ (ምዕራፍ 8)፣ በነጠላ ወላጆች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የተሳካላቸው እንዲሆኑ ሊረዷቸው የሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች (ምዕራፍ 9)፣ በአልኮል ሱሰኝነትና በዓመፅ ለሚታመሱ ቤተሰቦች የሚሆን እርዳታ (ምዕራፍ 12)፣ የጋብቻ ሰንሰለት ሊበጠስ በሚቃረብበት ጊዜ ምን ሊደረግ እንደሚቻል (ምዕራፍ 13)፣ አረጋውያን ወላጆችን ለማክበር ምን ሊደረግ እንደሚቻል (ምዕራፍ 15) እና የአንድ ቤተሰብ የወደፊት ሁኔታ አስተማማኝ መሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ (ምዕራፍ 16)። ከእነዚህ ውስጥ በርካታዎቹ ነጥቦች የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው በተሰኘው የአማርኛ መጽሐፋችንም ውስጥ ተብራርቶ ይገኛል። በሕይወታችን ውስጥ አንድ አዲስ ሁኔታ በሚፈጠርበትና የቤተሰባችን ኑሮ በሚለወጥበት ጊዜ ይህን መጽሐፍ መለስ ብለን መመልከታችንን እንቀጥል። ወዳጆቻችንና እድገት የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ይህን መጽሐፍ እንዲያነቡት እናበረታታቸዋለን።
5 እንግሊዝኛ የምትችሉ ከሆነ የቤተሰብ ደስታ የተሰኘውን መጽሐፍ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ ለምን አታጠኑትም? እንዲሁም ቤተሰባችሁ አዳዲስ እክሎች ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት በማንኛውም ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩትን ምዕራፎች በመከለስ ምክሩን በተግባር ላይ እንዴት ልታውሉ እንደምትችሉ በጸሎት አስቡበት። በተጨማሪም በመጋቢት ለመስክ አገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ብትመድቡ በዚህ ወር ልዩ እንቅስቃሴ ልታደርጉ ትችላላችሁ። በተቻላችሁ መጠን ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ ጥረት አድርጉ። ምንም እንኳ ሁሉም ሰዎች ጽሑፎቻችንን ባይወስዱም የምታደርጉት ውይይት ደስታ ያስገኝላችኋል። መልእክታችንን ባይቀበሉም እንኳን ማስጠንቀቂያውን የማሰማት ተልእኳችንን እንፈጽማለን።— ሕዝ. 3:18, 19፤ 2 ጢሞ. 4:2
6 ለአምላክ የማደር መንፈስ ያላቸው ቤተሰቦች በመንፈሳዊ ጠንካሮች፣ አንድነት ያላቸውና የሰይጣንን ጥቃት ለመመከት የተዘጋጁ ይሆናሉ። (1 ጢሞ. 4:7, 8፤ 1 ጴጥ. 5:8, 9) የቤተሰብ መሥራች ከሆነው አምላክ መለኮታዊ መመሪያ በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን!