ተማሪዎችን ከስማችን በስተጀርባ ወዳለው ድርጅት መምራት
1 “ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚነገር መልእክት ነው። ከ210 በሚበልጡ አገሮች በመዳረስ ላይ ያለ መልእክት ነው። ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ለእያንዳንዱ በግል የሚቀርብ መልእክት ነው። ዓለም አይቶት የማያውቀው በጣም ሰፊ የስብከት ዘመቻ ሲሆን በምድር ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አንድ በማድረግ ላይ ያለ መልእክት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሥራ ወደ ፍጻሜው ለማድረስ ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት በተደራጀ መልክ ሲሠሩ ቆይተዋል!”
2 የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተሰኘው የቪዲዮ ፊልም ትረካውን የሚጀምረው በዚህ መንገድ ነው። ይህ ፊልም የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው? ሥራቸው የተደራጀው፣ የሚመራውና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው እንዴት ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። “በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንዲገነቡ ለመርዳት በተደራጀ መልክ ስልጠና ሲያገኙ መቆየታቸው” ቪዲዮውን በተመለከቱት ሁሉ ከፍተኛ አድናቆት አሳድሮባቸዋል። እንዲሁም ከስማችን በስተጀርባ የሚገኘውን ድርጅት ራሳቸው እንዲመለከቱ ያበረታታል። ታጠና የነበረች አንዲት ሴት ይህን ቪዲዮ ተመልክታ የደስታና የአድናቆት እንባ ካነባች በኋላ “ይህ የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ድርጅት መሆኑን ሰው ሊገነዘብ የማይችለው ለምንድን ነው?” በማለት ተናግራለች።— ከ1 ቆሮንቶስ 14:24, 25 ጋር አወዳድር።
3 አንዲት ሌላ ሴትም መጽሐፍ ቅዱስን ረዘም ላለ ጊዜ አልፎ አልፎ ብታጠናም ሥላሴ የሐሰት ትምህርት መሆኑን አምና ለመቀበል አልቻለችም ነበር። ከዚያ እርሷና ባለቤቷ የቪዲዮ ክራችንን ተመለከቱ። በአቀራረቡ በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ በዚያው ምሽት ሁለት ጊዜ ተመለከቱት። በቀጣዩ ጥናታቸው ወቅት ሚስትዬዋ የይሖዋ ምስክር ለመሆን ያላትን ምኞት ገለጸች። የሥላሴን እምነት የሙጥኝ በማለቷ ስለ ድርጅታችንና በውስጡ ስላሉት ሰዎች ግንዛቤ ሳታገኝ መቅረቷን ተናግራለች። ከተመለከተችው ቪዲዮ እውነተኛውን የአምላክ ድርጅት እንዳገኘች ተገነዘበች። ወዲያውም ከቤት ወደ ቤት እየሄደች ለመስበክ ፈለገች። ያልተጠመቁ አስፋፊ ለመሆን መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምን እንደሆኑ ከተብራራላት በኋላ “አሁኑኑ ተገቢ የሆኑ እርምጃዎች እወስዳለሁ” አለች። ቤተ ክርስቲያኗን ጥላ ወጥታ በመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ መካፈል ጀመረች። እንዲሁም ሥላሴ ሐሰት መሆኑን በማስረዳት ረገድ የተካነች ሆነች።
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የይሖዋን ድርጅት ለይተው ሲያውቁና ከድርጅቱ ጋር ሲተባበሩ የተሻለ መንፈሳዊ እድገት እንደሚያደርጉና በፍጥነት ወደ ጉልምስና እንደሚደርሱ በሚገባ ታውቋል። በጰንጠቆስጤ ዕለት የተጠመቁት 3, 000 ሰዎች ‘በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት . . . ይተጉ ነበር።’ (ሥራ 2:42) በአሁኑ ጊዜም ተማሪዎች እንዲሁ እንዲያደርጉ መርዳታችን የግድ አስፈላጊ ነው። እንዴት?
5 ኃላፊነቱ የአንተ ነው:- ደቀ መዝሙር የሚያደርግ እያንዳንዱ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ወደ አምላክ ድርጅት የመምራቱ ኃላፊነት የእሱ እንደሆነ መገንዘብ አለበት። (1 ጢሞ. 4:16) እያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ አዲሱ ሰው ለይሖዋ የሚያደርገውን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት ወደሚያሳይበት አስደሳች ቀን የሚያሸጋግር ድልድይ ሆኖ መታየት ይኖርበታል። የጥምቀት ሥርዓት በሚከናወንበት ጊዜ ከሚቀርቡለት ጥያቄዎች መካከል አንዱ “ራሳችሁን መወሰናችሁና መጠመቃችሁ በመንፈስ ከሚመራው የአምላክ ድርጅት ጋር ከሚተባበሩት የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ አድርጎ የሚያስቆጥራችሁ መሆኑ ገብቷችኋልን?” የሚለው ነው። ስለዚህ ከእውነተኛው የክርስትና ጉባኤ ጋር ንቁ ትብብር ሳያደርግ አምላክን ማገልገል እንደማይችል መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነው።— ማቴ. 24:45-47፤ ዮሐ. 6:68፤ 2 ቆሮ. 5:20
6 ስለ ጉባኤያችሁና ከይሖዋ ምሥክሮች በስተጀርባ ስላለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ለተማሪው ማስተማራችሁን ቀጥሉ። ይህንንም ከመጀመሪያው የጥናት ቀን ጀምሮ በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ንገሩት። ገና ከጅምሩ ተማሪው ስብሰባ እንዲገኝ ጋብዙት፤ እንዲሁም አዘውትራችሁ መጋበዛችሁን ቀጥሉ።— ራእይ 22:17
7 በቀረቡላችሁ መሣሪያዎች ተጠቀሙ:- የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት የምንጠቀምባቸው ከሁሉ የተሻሉት ጽሑፎች አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘው ብሮሹርና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተሰኘው መጽሐፍ ናቸው። ሁለቱም ጽሑፎች ከጉባኤው ጋር የመተባበርን አስፈላጊነት ያጎላሉ። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘው ብሮሹር በትምህርት 5 መደምደሚያ ላይ እንዲህ ይላል:- “ስለ ይሖዋ መማርህን መቀጠልና እርሱ የሚፈልግብህን ነገሮች መፈጸምህን መቀጠል ይገባሃል። በዚህ ረገድ በአቅራቢያህ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች መገኘት በጣም ይረዳሃል።” እውቀት የተሰኘው መጽሐፍም ተማሪው በስብሰባዎች እንዲገኝ ደጋግሞ ያበረታታል። ምዕራፍ 5 አንቀጽ 22 የሚከተለውን ግብዣ ያቀርባል:- “የይሖዋ ምሥክሮች . . . ከእነርሱ ጋር ተባብረህ አምላክን ‘በመንፈስና በእውነት’ እንድታመልክ ሞቅ ባለ መንፈስ ያሳስቡሃል። (ዮሐንስ 4:24)” ምዕራፍ 12 አንቀጽ 16 እንዲህ ይላል “ይህን ጥናትህን ስትቀጥልና በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ልማድህ ስታደርግ እምነትህ ከዚህ ይበልጥ እንደሚጎለብት አያጠራጥርም።” ምዕራፍ 16 አንቀጽ 20 “በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን” ይላል። በማከልም “ይህ ደግሞ የአምላክን እውቀት እንድታስተውልና በሕይወትህ ውስጥ ሥራ ላይ በማዋል ደስታ እንድታገኝ ያስችልሃል። ምድር አቀፍ የሆነው ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት አባል መሆንህ ከይሖዋ ጋር ተቀራርበህ እንድትኖር ይረዳሃል።” ምዕራፍ 17 አንድ ሰው በአምላክ ሕዝብ መካከል ተረጋግቶና ተማምኖ መኖር የሚችለው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ያብራራል። ሌሎችን ስናስጠና በእነዚህ ምዕራፎቸ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ክፍሎች ትኩረት የመስጠቱ ኃላፊነት የእኛ ነው።
8 ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም በአሁኑ ጊዜ እየተጠቀመበት ያለውን ብቸኛ ምድራዊ ድርጅት ለሰዎች ለማሳወቅ ጥሩ ሆኖ የተዘጋጀው መሣሪያ እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ብሮሹር ነው። አገልግሎታችንን፣ ስብሰባዎቻችንንና ድርጅታችንን አስመልክቶ የያዘው ዝርዝር ማብራሪያ አምላክን ለማገልገል ከእኛ ጋር እንዲተባበር አንባቢውን ያበረታታዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንድ ጊዜ ከተጀመረ በግሉ እንዲያነበው የዚህን ብሮሹር አንድ ቅጂ ለተማሪው መስጠት ጥሩ ነው። ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው ብሮሹሩን ማስጠናት አስፈላጊ አይደለም።
9 ማኅበሩ ያዘጋጃቸው አንዳንድ የቪዲዮ ካሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ከስማችን በስተጀርባ ወዳለው ድርጅት ለመምራት በጣም ጥሩ መሣሪያዎች ናቸው። የሚከተሉትን የቪዲዮ ካሴቶች ማየት ቢችሉ ጥሩ ይሆናል። (1) የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ በእንቅስቃሴ ላይ የተሰኘው ፊልም ያላንዳች መሠናክል፣ በተቀላጠፈ መንገድና የፍቅር መንፈስ በተንጸባረቀበት ሁኔታ የሚካሄደውን የይሖዋን ድርጅት አሠራር የሚያሳየው በ1954 የተቀረጸውን ፊልም ይዞ የወጣ የቪዲዮ ካሴት ነው። (2) በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን የተሰኘው ፊልም በምሥራቅ አውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪካና በእስያ በተደረጉት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የታየውን ሰላማዊ አንድነት የሚያሳይ ነው። (3) እስከ ምድር ዳር ድረስ የተሰኘው ፊልም የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤትን 50ኛ ዓመት የሚገልጽና በዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ላይ ሚስዮናውያን ያሳደሩትን በጎ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው። (4) የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል የተሰኘው ፊልም ሂትለር ጭካኔ የተሞላበት ስደት ባመጣባቸው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ስላሳዩት ድፍረትና ስለተቀዳጁት ድል የሚገልጽ እንዲሁም አስደሳች ታሪክ የያዘ ነው። (5) የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውም የቪዲዮ ካሴት አለ።
10 ለስብሰባዎች ቀጣይ የሆነ ግብ ማውጣት:- በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት በግል የሚሰጠው ትምህርትም ሆነ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበው ትምህርት አስፈላጊያችን እንደሆኑ ለተማሪዎች ማብራራት ይገባል። (ዮሐ. 6:45) አንድ አዲስ ሰው ስለ ቅዱሳን ጽሑፎችና ስለ ድርጅቱ ያለው ግንዛቤ እኩል ማደግ ይኖርበታል። ለዚህ በስብሰባዎች ላይ ከመገኘት የተሻለ ሌላ አማራጭ የለም። (ዕብ. 10:23-25) ሰውየው ጥናት እንደ ጀመረ ወዲያውኑ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ መጋበዝ ጀምሩ። አንዳንድ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው ማጥናት ከመጀመራቸው በፊት በስብሰባዎች ላይ መገኘት ይጀምራሉ። እርግጥ ነው እኛም አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ተገቢ የሆነ ምሳሌ ማሳየት እንፈልጋለን።— ሉቃስ 6:40፤ ፊልጵ. 3:17
11 ተማሪው ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ ሲገኝ ግር እንዳይለው ስለ ስብሰባዎቹና ስብሰባዎቹ እንዴት እንደሚመሩ በደንብ አስረዳው። አንዳንድ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ ቦታ ሲሄዱ የፍርሃት ስሜት ስለሚሰማቸው ተማሪው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስብሰባ ሲሄድ አብሮ ወደ መንግሥት አዳራሹ መሄድ ጠቃሚ ነው። ከጉባኤ አባላት ጋር ሰላምታ በሚለዋወጥበት ጊዜ አብረኸው ከሆንክ የበለጠ ሊረጋጋ ይችላል። ከሁሉም በላይ ወደ ስብሰባዎቻችን የሚመጣው ሰው የደስተኝነትና የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርበት ጥሩ እንግዳ ተቀባይ ሁን።— ማቴ. 7:12፤ ፊልጵ. 2:1-4
12 ተማሪው በቅርቡ በሚደረገው የልዩ ስብሰባ ቀን፣ በወረዳ ስብሰባና በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ አበረታታው። ምናልባትም በምትጠቀምበት ትራንስፖርት አብሮህ እንዲሄድ ማድረግ ትችል ይሆናል።
13 ከልብ የመነጨ አድናቆት መትከል:- አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የተባለው መጽሐፍ ገጽ 92 ላይ እንዲህ ይላል:- “ራስህ ለይሖዋ ድርጅት ያለህ የጠለቀ አድናቆት ከአዲሶች ጋር በምታደርገው ንግግር የሚንጸባረቅ ከሆነ እነርሱም አድናቆታቸውን ማሳደጉ ቀላል ይሆንላቸዋል፤ ይሖዋን በማወቅም በኩል የበለጠ ዕድገት እንዲያደርጉ ያነቃቃቸዋል።” ጉባኤህን በሚመለከት ሁልጊዜ ገንቢ እንጂ አፍራሽ ነገር አትናገር። (መዝ. 84:10፤ 133:1, 3) በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት በምታቀርበው ጸሎት ጉባኤውንና ተማሪው ከጉባኤው ጋር አዘውትሮ የመቀራረቡን አስፈላጊነት ጥቀስ።— ኤፌ. 1:15-17
14 አዲሶች በአምላክ ሕዝቦች መካከል ላለው አስደሳች ኅብረትና መንፈሳዊ ደህንነት ልባዊ የሆነ አድናቆት እንዲያሳድጉ እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (1 ጢሞ. 3:15፤ 1 ጴጥ. 2:17፤ 5:9) የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቃል ተማሪዎች የሆኑትን ከስማችን በስተጀርባ ወዳለው ድርጅት ለመምራት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።
[ከገጽ 4 የተቀነጨበ ሐሳብ ]
ተማሪዎች ድርጅቱን ራሳቸው በሚያዩበት ጊዜ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ያደርጋሉ
[ከገጽ 4 የተቀነጨበ ሐሳብ ]
ተማሪዎች በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ አትዘግዩ