የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ክፍል 8፦ ተማሪዎችን ወደ ድርጅቱ መምራት
1. በእያንዳንዱ የጥናት ወቅት ስለ ይሖዋ ድርጅት አንዳንድ ነጥቦችን ለጥናቱ ማካፈሉ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
1 መጽሐፍ ቅዱስን ስናስጠና ግባችን መሠረተ ትምህርቶችን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ጥናቶቻችን የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንዲሆኑ መርዳትም ጭምር መሆን አለበት። (ዘካ. 8:23) ለዚህም እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ብሮሹር መጠቀም እንችላለን። አዲስ ለሆኑ ጥናቶች ይህን ብሮሹር ካበረከትክላቸው በኋላ እንዲያነቡት ልታበረታታቸው ትችላለህ። በተጨማሪም በእያንዳንዱ የጥናት ወቅት ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ ስለ ይሖዋ ድርጅት አንድ ሐሳብ አካፍላቸው።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ እንዴት ልታበረታታቸው ትችላለህ?
2 የጉባኤ ስብሰባዎች:- ጥናቶቻችን የይሖዋን ድርጅት እንዲያደንቁ የሚረዳቸው ዋናው ነገር ከእኛ ጋር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸው ነው። (1 ቆሮ. 14:24, 25) ስለሆነም በእያንዳንዱ የጥናት ወቅት አንዱን የጉባኤ ስብሰባ በማብራራት አምስቱንም ስብሰባዎች እንዲያውቁ ልትረዳቸው ትችላለህ። የሚቀጥለውን ሳምንት የሕዝብ ንግግር ርዕስ ንገራቸው። በመጠበቂያ ግንብ ጥናትና በመጽሐፍ ጥናት ወቅት የሚጠኑትን ጽሑፎች አሳያቸው። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ ምን እንደሆነ ግለጽላቸው። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል በሚኖርህ ጊዜ ከጥናቶችህ ጋር ልትለማመድ ትችላለህ። በስብሰባው ወቅት የቀረቡትን ጥሩ ጥሩ ነጥቦች አካፍላቸው። በጽሑፎቻችን ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች በማሳየት በስብሰባው ላይ ምን እንደሚካሄድ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እርዳቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመራችሁበት ጊዜ አንስቶ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው።
3. ድርጅቱን በተመለከተ ስለ የትኞቹ ጉዳዮች መወያየት እንችላለን?
3 የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል፣ ትልልቅ ስብሰባዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት በሚቃረብበት ጊዜ ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ ስለ ሁኔታው በማብራራት ለዝግጅቱ ጉጉት እንዲያድርባቸው አድርግ። እንደሚከተሉት ያሉ አንዳንድ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ልንመልስላቸው እንችላለን:- የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራው ለምንድን ነው? የምንሰበሰብበትን ቦታ የመንግሥት አዳራሽ የምንለውስ ለምንድን ነው? የሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ሥራ ምንድን ነው? የስብከቱ ሥራና ክልሎች የሚደራጁት እንዴት ነው? ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁት እንዴት ነው? ድርጅቱ ለሚያከናውነው ሥራ ገንዘብ የሚያገኘው ከየት ነው? ቅርንጫፍ ቢሮና የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ሥራውን በመምራት ረገድ ምን ሚና አላቸው?
4, 5. የቪዲዮ ፊልሞች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለድርጅቱ ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
4 ትምህርት ሰጪ የቪዲዮ ፊልሞች:- ጥናቶቻችን ግሩም የሆነውን የይሖዋን ድርጅት ማወቅ የሚችሉበት ሌላው መንገድ በቪዲዮ ፊልሞቻችን አማካኝነት ነው። በእነዚህ ፊልሞች አማካኝነት እስከ ምድር ዳር ድረስ ስለሚካሄደው የስብከት ሥራችንና በዓለም ዙሪያ ስለሚገኘው መላው የወንድማማች ማኅበር ማወቅ ይችላሉ፤ ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን እንደቻልን ይመለከታሉ። መጽሔቶቻችንንና ሌሎች ጽሑፎችን ለአምስት ዓመታት ትወስድ የነበረች አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውን የቪዲዮ ፊልም በምትመለከትበት ጊዜ ዓይኖቿ በእንባ ተሞሉ። እየተመላለሱ ይጠይቋት በነበሩት ምሥክሮች ላይ አመኔታ ነበራት፤ የቪዲዮ ፊልሙን ካየች በኋላ ግን በድርጅቱም ልትተማመን እንደምትችል ተገነዘበች። ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የተጀመረላት ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ መገኘት ጀመረች።
5 በየሳምንቱ ከጥናቶቻችን ጋር ጥቂት ደቂቃዎች በማሳለፍና በተዘጋጁልን መሣሪያዎች በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ወደሚጠቀምበት ድርጅት ቀስ በቀስ መምራት እንችላለን።