ሌሎች ሰዎች በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ እርዷቸው
1 “በስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚፈልግ . . . ማንኛውም ሰው ወደ ስብሰባዎቻችን እንዲመጣ በአክብሮት ተጋብዟል።” ይህ ማስታወቂያ በኅዳር 1880 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር አብረዋቸው እንዲሰበሰቡ ሲጋብዙ ቆይተዋል። (ራእይ 22:17) እንዲህ ማድረጉ የእውነተኛ አምልኮ አስፈላጊ ክፍል ነው።
2 በስብሰባዎች ላይ መገኘት ወሳኝ ነገር ነው:- በጉባኤ አንድ ላይ መሰብሰባችን በረከት ያስገኝልናል። ግሩም የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን ይበልጥ እናውቀዋለን። በጉባኤ አንድ ላይ የምንሰበሰበው ‘ከይሖዋ ለመማር’ ነው። (ኢሳ. 54:13) የይሖዋ ድርጅት ይበልጥ ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚያደርገንንና “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” በሥራ ላይ የምናውልበትን ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት የማያቋርጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ያዘጋጅልናል። (ሥራ 20:27፤ ሉቃስ 12:42) ስብሰባዎች የአምላክን ቃል በማስተማር ረገድ በግል ስልጠና እንድናገኝ ይረዱናል። ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኛቸው ማሳሰቢያዎች ከሌሎች ሰዎችና ከራሱ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንድንመሠርት ይረዱናል። አምላክን ከሚወድዱ ሰዎች ጋር መሰብሰብ እምነታችንን ያጠነክርልናል።—ሮሜ 1:11, 12
3 በቀጥታ ጋብዟቸው:- እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ጥናት ከጀመረበት ቀን አንስቶ ወደ ስብሰባዎች እንዲመጣ ጋብዙት። የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት ካለ ስጡት። ባለፈው ስብሰባ ላይ እናንተን ያበረታታችሁን አንድ ነጥብ በማካፈል እንዲሁም በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ ምን እንደሚብራራ በመንገር ፍላጎቱን ቀስቅሱ። የመንግሥት አዳራሹ ምን እንደሚመስል ንገሩት፤ እንዲሁም ቦታውን በትክክል የሚያውቅ መሆኑን አረጋግጡ።
4 ተማሪው ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋብዛችሁት ወዲያው መገኘት ባይጀምር እንኳ መጋበዛችሁን አታቋርጡ። በየሳምንቱ ጥቂት ደቂቃዎችን በመመደብ ድርጅታችን እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ንገሩት። ስለ እኛና ስለ ስብሰባዎቻችን ይበልጥ እንዲያውቅ ለመርዳት የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ የተባለውን ብሮሹርና የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለ ድርጅት የተባለውን ቪዲዮ ተጠቀሙ። ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር እንዲተዋወቅ ጥናቱ ላይ ጋብዟቸው። በጸሎትህ ላይ ይሖዋን ስለ ድርጅቱ አመስግነው እንዲሁም ተማሪው ከድርጅቱ ጋር የመተባበሩን አስፈላጊነት ጥቀሱ።
5 ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች አብረውን እንዲሰበሰቡ ለመርዳት አታመንቱ። ለይሖዋ ያላቸው አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ የተማሩትን ተግባራዊ ለማድረግና አንድነት ያለው የአምላክ ድርጀት ክፍል ለመሆን ይገፋፋሉ።—1 ቆሮ. 14:25