መጽሐፍ ቅዱስ—አምላክ ለሰው ሁሉ መመሪያ እንዲሆን የሰጠው መጽሐፍ
1 መጽሐፍ ቅዱስ ከ2,100 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ተተርጉሞ አራት ቢልዮን በሚያህሉ ቅጂዎች ታትሟል ተብሎ ይገመታል። ይህ ደግሞ 90 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የምድራችን ነዋሪዎች የአምላክን ቃል እንዲያገኙ አስችሏል። ሆኖም “የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት” ጋር በተያያዘ በዓለም ላይ ረሐብ አለ። (አሞጽ 8:11) መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ብዙ ሰዎች ወይ አያነቡትም አሊያም በውስጡ ያለውን መልእክት አይረዱም። መጽሐፍ ቅዱስን ተግባራዊ የሆነ የሕይወታቸው መመሪያ አድርገው እንዲጠቀሙበት እንዴት ልናበረታታቸው እንችላለን?
2 በታኅሣሥ ወር መጽሐፌ ወይም ታላቁ ሰው (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ እናበረክታለን። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በምናገኝበት ጊዜ ላለፉት 47 ዓመታት ብዙ የጠቀመንን የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማበርከት እንችላለን። ግልጽና ዘመናዊ የሆነውን አገላለጹን በማብራራት ማበርከት እንችላለን። (“ቅዱሳን ጽሑፎች ሁሉ” (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 328 አንቀጽ 6ን ተመልከት) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ሁሉ የሰጠው መመሪያ መሆኑን ሌሎች እንዲቀበሉ በቅንዓት በመርዳት ከይሖዋ ላገኘነው ለዚህ ስጦታ ያለንን ልባዊ አድናቆት እናሳያለን።
3 “መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?” የተባለውን ትራክት በመጠቀም መግቢያ ማዘጋጀት ትችላለህ። እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ 90 ከመቶ በላይ ለሚሆነው የምድር ነዋሪ የሚዳረስ ቢሆንም አዘውትረው የሚያነቡት ጥቂት ሰዎች ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?” የትራክቱን የመጀመሪያ ሁለት አንቀጾች ከ2 ጢሞቴዎስ 3:16 ጋር አንብብ። መጽሐፌ ወይም ታላቁ ሰው (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ አበርክት። መጽሐፉን ከወሰደ የተለመደውን የአስተዋጽኦ ዋጋ እንዲከፍል አድርግ። መጽሐፉን መውሰድ ካልፈለገ የቀረውን የትራክቱን ክፍል እንዲያነብ ጠይቀው። “ወደፊት የሚሆነውን አስቀድሞ መናገር” የሚለውን የመጨረሻ ንዑስ ርዕስ አጉላ።
4 “መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?” የተባለውን ትራክት ላበረከትክላቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ ቀጥሎ የተጠቀሰውን አቀራረብ መጠቀም ትችላለህ:-
◼ በድጋሚ ራስህን ካስተዋወቅህ በኋላ የትራክቱን የመጨረሻ ሁለት አንቀጾች አንብብ። በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚቻል መሆኑን እስከዛሬ ድረስ አስቦበት እንደሆነ ጠይቀው። መልስ ከሰጠህ በኋላ እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን የብቃት ደረጃዎች ያሟሉ ሰዎች ሁሉ ስለሚያገኙት አስደሳች የወደፊት ጊዜ የሚገልጸውን ትንቢት ጨምሮ ሁሉም ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ የይሖዋ ምሥክሮች እርግጠኞች ናቸው።” አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር ገጽ 13 ላይ ያለውን ሥዕል ካሳየኸው በኋላ ትምህርት 5ን ገልጠህ በተዘረዘሩት የጥያቄዎቹ መልሶች ላይ ለመወያየት ሐሳብ አቅርብለት። በዚህ መንገድ ጥናት ጀምር።
5 ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች ባሉበት ክልል ውስጥ ይህን መግቢያ መጠቀም ትችላለህ:-
◼ “ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ አክብሮት እንዲኖራቸው እያበረታታን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቤተሰቦች ዘንድ ይገኛል ሆኖም ከባድ ችግሮች ሲገጥሟቸው መፍትሔ ለማግኘት ወደ እሱ ዞር አይሉም። ይህን ነገር አስተውለዋል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ምናልባትም መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት ነው ብለው ያምኑ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለው ይህ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንስ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ትክክለኛ እንደሆነና በአሁኑ ጊዜ ላሉት አስጨናቂ ችግሮች ተግባራዊ መፍትሔዎችን እንደሚሰጥ አሳማኝ ማስረጃዎች ያቀርባል።” በምዕራፍ 8 ወይም በምዕራፍ 12 ላይ የሚገኙ አንዳንድ ነጥቦችን ካጎላህ በኋላ መጽሐፉን አበርክትለት።
6 “የአምላክ ቃል” የተባለው መጽሐፍ የተበረከተላቸውን ተመልሰህ በምትጠይቅበት ጊዜ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ስንገናኝ በዛሬው ጊዜ ላሉት ውስብስብ ችግሮች መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት መፍትሔ እንደሚሰጥ ተወያይተን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው የተቀበሉት ሰዎች ደስታ ያለበትና አርኪ የሆነ ሕይወት እንዲመሩም አስችሏቸዋል። ባለፈው ጊዜ በሰጠሁዎት መጽሐፍ ውስጥ ከተብራሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱን ላሳይዎት እወዳለሁ።” በምዕራፍ 12 ከአንቀጽ 3-6 ላይ ከቀረቡት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱን አብራራና አንቀጽ 7ን አንብበህ ውይይቱን ደምድም። ሰውየው ፍላጎት ካሳየ በእውቀት መጽሐፍ ወይም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር አማካኝነት እንዲያጠና ሐሳብ አቅርብለት።
7 ቀጥሎ ያለው አቀራረብ በእድሜ የገፉ ሰዎችን ፍላጎት ሊቀሰቅስ ይችላል:-
◼ “መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቤቶች ውስጥ ይነበብ የነበረበትና ሰዎችም በውስጡ በሰፈሩት መመሪያዎች ይመሩ የነበረበት ጊዜ ነበር። በእርስዎ ቤተሰብ ውስጥ ሁኔታው እንደዚህ ነበር? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በዛሬው ጊዜ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ጊዜ እንዳይመድቡ ብዙ ነገሮች ይሻሟቸዋል ወይም የሥነ ምግባር መመሪያዎቹ ጊዜ ያለፈባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለው የዚህ መጽሐፍ 13ኛ ምዕራፍ መጽሐፍ ቅዱስን ካጠኑ በኋላ በሕይወታቸው በጎ ለውጥ ያሳዩ የሦስት ሰዎችን እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮ ይዟል። የአምላክ ቃል ያለው ኃይል እንዴት እንደረዳቸው ማንበብ ከፈለጉ ይህን መጽሐፍ ብሰጥዎ ደስ ይለኛል።”
8 ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው በተገናኘን ጊዜ ዛሬ ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ችላ እየተባሉ መሆናቸውን ተነጋግረን ነበር። ይህ የሰዎች ቸልተኝነት ሊያሳስበን ይገባል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘትን ከፍተኛ ግምት ሰጥቶታል።” ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። ቀጥሎም ከእውቀት መጽሐፍ ምዕራፍ 1 አንቀጽ 5ን አወያየው። መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንደምናስጠና ግለጽለትና እንዴት እንደሚካሄድ ለማሳየት ሐሳብ አቅርብለት።
9 አምላክ ለሰው ሁሉ መመሪያ እንዲሆን የሰጠውን መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች በትኩረት እንዲያነቡት ለማበረታታት የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ እንዲባርክልህ ጸልይ።