የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ!
1 ብዙዎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖረን እንመኛለን፤ ይህም ትክክል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት አዳዲስ ደቀ መዛሙርት የማፍራት ግብ ላይ እንድንደርስ የሚያስችለን ሥራ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ሆኖም ብዙዎቻችን እውነትን ለአንድ ሰው በማስተማር የሚገኘውን ልዩ የሆነ ደስታ ሳንቀምስ ወራቶች እንዲያውም ዓመታት አስቆጥረን ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ በኅዳር ወር ምን ልናደርግ እንችላለን? በዚህ ወር ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ስናበረክት አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ልዩ ጥረት ልናደርግ እንችላለን።
2 አንድ ወይም ከዚያ የሚበልጡ ቅዳሜና እሁዶችን መድቡ፦ ሁሉም አስፋፊዎች በዚህ ወር አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የተወሰነ ጊዜ እንዲመድቡ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ እናበረታታለን። የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት መሪዎች ለዚህ ዓላማ አንድ (ወይም ከዚያ በላይ) ቅዳሜና እሁድ መርጠው ቡድናቸው ተመላልሶ መጠየቅ በማድረጉ ሥራ የተጠናከረ ዘመቻ እንዲያደርግ ያስተባብራሉ።
3 በእያንዳንዱ የመስክ ስምሪት ስብሰባ ላይ በምትገኙበት ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ የመዘገባችሁበትን ማስታወሻ ይዛችሁ ሂዱ። ከዚያም ፍላጎት ያሳዩትን፣ ጽሑፍ የወሰዱትን ወይም በስብሰባ ላይ የተገኙትን ሁሉ ሄዳችሁ አነጋግሩ። እያንዳንዱን ሰው ጥናት የማስጀመር ግብ በመያዝ አወያዩ።
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲጀመር የሚያሳይ ሠርቶ ማሳያ፦ በመስክ ስምሪት ስብሰባዎች ላይ፣ በተመላልሶ መጠየቅ ጊዜ ጥናት እንዴት ማስጀመር እንደሚቻል የሚያሳይ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ሠርቶ ማሳያ መቅረብ ይኖርበታል። እንዲህ ልትል ትችል ይሆናል:- “ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ቢሆንም ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ ለምናነሳቸው በጣም ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ እንደያዘ አይገነዘቡም። [በእውቀት መጽሐፍ ውስጥ ያለውን ማውጫ አሳየውና የምዕራፍ 3ን፣ 5ን፣ 6ን እና 9ን ርዕስ ወይም ከዘላለም መኖር መጽሐፍ ውስጥ ጥቂት ርዕሶችን አንብብለት።] በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት በየሳምንቱ ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ ብዙም ለማይበልጥ ጊዜ ቢያጠኑ በጥቂት ወራት ውስጥ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቶች ሊያገኙ ይችላሉ። ከእነዚህ ርዕሶች ውስጥ አንዱን ከመረጡ ፕሮግራሙ እንዴት እንደሚካሄድ ላሳይዎት እችላለሁ።” ግለሰቡ ካለው የተጣበበ ጊዜ የተነሣ ለማጥናት የሚያመነታ ከሆነ አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ የሚከናወን የጥናት ፕሮግራምም እንዳለን ግለጽለት። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር አስተዋውቀውና በሳምንት ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ብቻ በመውሰድ አንዱን ትምህርት መሸፈን እንደምትችሉ ንገረው።
5 ሁላችንም ጥናት ለማስጀመር የተባበረ ጥረት ካደረግንና ይሖዋም ጥረታችንን እንዲባርክልን ከለመንነው አዳዲስ ጥናቶች ማግኘታችን የማይቀር ነው! (1 ዮሐ. 5:14, 15) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖራችሁ የምትፈልጉ ከሆነ ይህ ጥናት የምታገኙበት ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንላችሁ ይችላል።