1 ክርስቲያን ቤተሰቦች በጉባኤ ስብሰባዎች አንድ ላይ እንድንሰበሰብ የተሰጠንን ትእዛዝ ማክበር አለባቸው። (ዕብ. 10:24, 25) ጥሩ ትብብር ካደረጉ ሁሉም ለስብሰባዎች በመዘጋጀት፣ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ተሳትፎ በማድረግ ረገድ ሊሳካላቸው ይችላል። አንድ ቤተሰብ ከሌላው የሚለይ ቢሆንም አንድ ክርስቲያን ባል፣ አማኝ የሆነች ሚስት ወይም አንድ ነጠላ ወላጅ ቤተሰቡ በመንፈሳዊ ጉዳዮች አንድነት እንዲኖረው ማድረግ የሚችሉት ነገር አለ። በዚህ ረገድ ቤት ውስጥ ያሉት ልጆች ብዛትና ዕድሜያቸው ምንም ለውጥ አያመጣም።—ምሳሌ 1:8
2 ለዝግጅት ጊዜ መድቡ፦ ሁሉም ለጉባኤ ስብሰባዎች በደንብ እንዲዘጋጁ የቤተሰብ አባላት መረዳዳት አለባቸው። ብዙዎች ሳምንታዊውን የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ አብረው ያጠናሉ። አንዳንዶች ለጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ይዘጋጃሉ አሊያም የሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በቤተሰብ መልክ ያነብባሉ። ይህን የሚያደርጉበት ዓላማ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘታቸው በፊት ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለመጨበጥ ነው። በዚህ መንገድ ሁሉም ከሚያዳምጡት ነገር ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን አጋጣሚ ሲኖር ደግሞ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ይሆናሉ።—1 ጢሞ. 4:15
3 ተሳትፎ ለማድረግ ግብ አውጡ፦ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት በሌሎች ፊት ተስፋውን የመግለጽ ግብ ሊኖረው ይገባል። (ዕብ. 10:23) ይህን ለማድረግ እርዳታ ወይም ማበረታቻ የሚያስፈልገው የቤተሰብ አባል አለ? እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለሚያቀርበው ክፍል ምን ድጋፍ ያስፈልገዋል? ሚስቶች ባሎቻቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሲሰጡና ምናልባትም ተስማሚ የሆነ ምሳሌ ወይም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መቼት ሲጠቁሟቸው ደስ ይላቸዋል። ወላጆች፣ የልጆቻቸውን ክፍል እነርሱ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ሊሰማቸው አይገባም። እንዲህ ማድረጋቸው ልጆቹ የራሳቸውን ሐሳብ እንዳያፈልቁ ሊገታቸው ይችላል። ሆኖም ወላጆች ልጆቻቸውን ሊረዷቸውና ጮክ ብለው ሲለማመዱ ሊያዳምጧቸው ይችላሉ።—ኤፌ. 6:4
4 በስብሰባ ላይ ለመገኘት መዘጋጀት፦ ልጆች ከትንሽነታቸው አንስቶ ሰዓቱ ሲደርስ ወደ ስብሰባ ለመሄድ እንዲለባብሱና እንዲዘጋጁ ማሰልጠን ይቻላል። የቤተሰብ አባላት ማንም እንዳያረፍድ በማሰብ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ መረዳዳት አለባቸው።—የቤተሰብ ደስታ ገጽ 112 እና ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ገጽ 316-17 ላይ ያሉትን ሐሳቦች ተመልከቱ።
5 ወላጆችም ሆኑ ልጆች በጥንት ዘመን የኖረው ኢያሱ “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” ሲል የተናገራቸውን ቃላት ሊያሰላስሉባቸው ይገባል። እንግዲያው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ቁርጥ ውሳኔያችሁ ይሁን።—ኢያሱ 24:15